አሜሪካ እና ኢራን ስምምነት ላይ ከመድረሳቸው በፊት በርካታ የማያግባቧቸውን ጉዳዮች መፍታት እንዳለባቸው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስምምነት ለመፈረም ተቃርበው እንደሆነ ከቢቢሲ የተጠየቁት ጄዲ ቫንስ፤ አሁን ላይ መናገር እንደማይቻል ገልጸዋል።
ሁለቱ አገራት ስምምነት ላይ ከደረሱ የተኩስ አቁሙ በ60 ቀናት ይራዘማል። ስለ ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብርም ንግግር ይጀመራል።
ኢራን እና አሜሪካ የስምምነት ማዕቀፍ ላይ ከስምምነት መድረሳቸውን የዋሽንግንተን ባለሥልጣናት ትናንት ሐሙስ ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።
ሆኖም የኢራኑ ታስኒም የዜና ወኪል ስምምነቱ እንዳልተጠናቀቀ እና እንዳልተረጋገጠ ገልጿል።
የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ “ዩራኒየም የማበልጸግ ጉዳይን ጨምሮ በአንዳንድ ነጥቦች ዙርያ” ድርድሮች እየተካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል።
ስምምነት ላይ ተደርሶ እንደሆነ ተጠይቀውም “እዚያ ነጥብ ላይ አልደረስንም፤ ግን ተቃርበናል። አሁንም ሥራችንን እንቀጥላለን” ብለው መልሰዋል።
ኢራን ዩራኒየም ማበልጸግ እንድታቆም እና እስካሁን ያከማቸችውን እንድታስወግድም አሜሪካ ጠይቃለች።
ሁለቱ አገራት የተኩስ አቁም ካደረጉ ወዲህ ውይይታቸው በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ እንደሆነ ትራምፕ ሲናገሩ ተደምጧል።
BBC
