አሜሪካ እና ኢራን የአስቸኳይ ተኩስ አቁም ዕቅድ እንደቀረበላቸው ተዘገበ

Date:

አሜሪካ እና ኢራን ከዛሬ ጀምሮ ተኩስ እንዲቆም እና የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት የሚጠይቅ የስምምነት ዕቅድ በአሸማጋዮች እንደቀረበላቸው የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘገበ።

የዜና ወኪሉ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበ፤ ሌሊት ላይ ለኢራን እና ለአሜሪካ ደረሰው ግጭቶችን ለማቆም የሚያስችል ማዕቀፍ የተዘጋጀው በፓኪስታን ነው።

ሁለት ደረጃ ያለው ይህ የስምምነት ማዕቀፍ በመጀመሪያው የተኩስ አቁም ተግባራዊ እንዲሆን በመቀጠል ደግሞ ወደ አጠቃላይ ስምምነት እንዲያድግ ያደርጋል ተብሏል።

አሸማጋይ አገራት ስምምነት ላይ እንዲደረስ ጥረት እያደረጉ ያሉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን የኤነርጂ መሠረተ ልማት እንደሚያወድሙ በመዛት እስከ ማክሰኞ ድረስ የሰጡት ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ሰዓት ነው።

ኢራንም በሲቪል መሠረተ ልማቶቿ ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ “እጅግ የከፋ” የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ዝታለች። አደራዳሪዎች ግጭቱ በድጋሚ ጡዘት ላይ ከመድረሱ አስቀድሞ ውጥረቱን የሚያረግብ መፍትሔ ለማግኘት ላይ ታች እያሉ መሆኑ ተዘግቧል።

ሮይተርስ ያነጋገራቸው ምንጭ “ሁሉም [የዕቅዱ] ክፍሎች ዛሬ ስምምነት ላይ ሊደረስባቸው ይገባል” ማለታቸው ተዘግቧል። ዕቅዱ መጀመሪያው ላይ በፓኪስታን በኩል በኤሌክትሮኒክ መንገድ በመግባቢያ ስምምነትነት እንዲጠናቀቅ የማድረግ ሀሳብ እንዳለም ተገልጿል።

አሸማጋዮች የ45 ቀናት ተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ለማድረግ እየጣሩ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ የዘገበው የአሜሪካው ዜና ምንጭ አክሲዮስ ነው። እንደ ዘገባው ይህንን ጥረት እያደረጉ ያሉት የፓኪስታን፣ የግብፅ እና የቱርክ አደራዳሪዎች ናቸው።

የትራምፕ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺም የጽሑፍ መልዕክት እንደተለዋወጡ ዘገባው ጠቅሷል። አክሲዮስ ዕሁድ ዕለት ያነጋገራቸው ምንጮች በሚቀጥሉት 48 ሰዓታት ውስጥ ስምምነት ላይ የመደረስ ዕድሉ ጠባብ እንደሆነ ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በበኩላቸው ከኢራን ጋር “ጥልቅ ድርድር” እያደረጉ መሆኑን እና የማክሰኞው ቀነ ገደብ ከመጠናቀቁ አስቀድሞ ስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚችል ለዜና ምንጩ ተናግረዋል።

“[ስምምነት ላይ ለመድረስ] ጥሩ ዕድል አለ፤ ነገር ግን ስምምነት የማይፈጽሙ ከሆነ ግን እዚያ ያለውን ሁሉንም ነገር አጋያለሁ” ብለዋል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አቶ ዳውድ ኢብሳ ከምርጫው ራሳቸውን አገለሉ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በኦሮሚያ...

ኢራን ከአሜሪካ ጋር ‹‹ሁሉን አቀፍ ስምምነት›› እንደምትፈልግ ገለጸች

ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ጦርነት ለማቆም ከአሜሪካ ጋር በምታደርገው...

የሪል እስቴት ዘርፍ ዘመናዊ የክፍያ ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት አዲስ አጋርነት ፈጠረ

በኢትዮጵያ የሪል እስቴት ዘርፍ ግንባር ቀደም ከሆኑት ድርጅቶች አንዱ...

የአርቲስት ጥላሁን ገሠሠ መታሰቢያ ሐውልት ተመረቀ

ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ዕድገት ወደር የሌለው አስተዋጽኦ ላበረከተውና የሙዚቃው...