ሦስተኛ ሳምንቱ ላይ በሚገኘው እና አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር በሚያደርጉት ጦርነት የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶች ቀጥለዋል። በኢራን እና በአጋሮቿ የሚሊሻ ቡድኖች የሚሰነዘሩ የአጸፋ ጥቃቶች ሌሊቱን ሙሉ የቀጠሉ ሲሆን፣ የሰዎች ሞትም ተመዝግቧል።
- የኢራን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተጽዕኖ ፈጣሪው የኢራን ጠቅላይ ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት ጸሐፊ አሊ ላሪጃኒ በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደላቸውን አረጋግጠዋል ። ላሪጃኒ ከጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ ሞት ወዲህ ከተገደሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል አንዱ ናቸው።
- የእስራኤል ጦር በሊባኖስ ውስጥ የሔዝቦላህ ዒላማዎችን መደብደቡን ቀጥሏል። የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር በማዕከላዊ ቤይሩት በተፈጸሙ የእስራኤል ሁለት ጥቃቶች ቢያንስ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች 24 ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጿል።
- የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንድ ተተኳሽ የኢራንን የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ቢመታም ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳልደረሰበት አስታውቋል።
- የአሜሪካ ጦር በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ አቅራቢያ የሚገኙ የኢራን የሚሳኤል ጣቢያዎችን መምታቱን አስታውቋል።
- ዶናልድ ትራምፕ የኔቶን እና ሌሎች አጋሮችን ተችተዋል፤ ፕሬዚዳንቱ ቀደም ሲል ድጋፍ ጠይቀው የነበረ ቢሆንም አሜሪካ በኢራን ጦርነት ላይ “ከእንግዲህ ወዲህ እርዳታ አትሻም ወይም አትፈልግም” ብለዋል።
- በቴል አቪቭ የኢራን የሚሳዔል ጥቃትን ተከትሎ በ 70ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ተገድለዋል።
- የኢራን የጦር አዛዥ የላሪጃኒን ግድያ በመበቀል “ወሳኝ፣ የሚያሽመደምድ እና ጸጸት ላይ የሚጥል” ምላሽ እንደሚሰጡ ዝተዋል። ከጦሩ የተለየ ወታደራዊ አካል የሆነው የኢራን አብዮታዊ ዘብ የላሪጃኒን ሞት “ለመበቀል” ወደ ማዕከላዊ እስራኤል ሚሳዔሎችን ማስወንጨፉን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
