የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ እንደተናገሩት፤ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሰላም ስምምነት ቢደረግም የእስራኤል ጦር በደቡብ ሊባኖስ፣ በሶሪያ እና በጋዛ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ቆይታውን ይቀጥላል።
እስራኤል ‹‹ምንም ዓይነት የአሁኑም ሆነ የወደፊት ጫናዎች ቢኖሩም›› ጦሯን ከሊባኖስ የማስወጣት እቅድ እንደሌላት በሚኒስትሩ መግለጫ ተመላክቷል።
ካትዝ አክለውም የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ይህንን አቋም ለአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ለሌሎች ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣናት በግልፅ ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።
‹‹እኔም ይህንኑ ጉዳይ ለአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴዝ በግልፅ አሳውቄያለሁ›› ብለዋል ካትዝ።
ሚኒስትሩ በሊባኖስ ካለው ሁኔታ ጋር ተያይዞ ቴህራን በእስራኤል ላይ ጥቃት የምትሰነዝር ከሆነ፤ እስራኤል ‹‹ባላት አቅም ሁሉ›› በኢራን ላይ ጥቃት እንደምትሰነዝር አስጠንቅቀዋል።
የእስራኤል የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን-ጊቪር በበኩላቸው የአሜሪካ-ኢራንን ስምምነት በመንቀፍ ‹‹የትራምፕ ስምምነት ቴል አቪቭን አያስገድዳትም›› ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እሁድ እለት ከኢራን ጋር የሰላም ስምምነት መጠናቀቁን በይፋ አስታውቀዋል።
ስምምነቱ የሊባኖስን ግንባር ጨምሮ በሁሉም አቅጣጫዎች ጦርነት እንዲቆም፣ የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ እንዲከፈት እና በኢራን ላይ የተጣለው የአሜሪካ የባህር ኃይል እገዳ እንዲነሳ የሚሉ ነጥቦችን የያዘ ነው።
ሆኖም ይህ በተባለ ማግስት የእስራኤል ጦር በደቡብ ሊባኖስ ላይ የአየር ጥቃቱን ቀጥሏል።
እንደ ሊባኖስ ባለስልጣናት መረጃ ከሆነ፤ካለፈው መጋቢት ጀምሮ በእስራኤል ጥቃት ከ3 ሺህ 7መቶ በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ወደ 11 ሺህ 5መቶ የሚጠጉ ቆስለዋል እንዲሁም ከ1.5 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ያለዉ አናዶሉ ነዉ።
