በጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ (ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል)
እነ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴን ከሠውበት የነበረው ሀገር አቀፍ የስፖርት ማህበራት ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ ለመወሠን ተሻሽሎ የወጣው መመሪያ ክስ በፍ/ቤት ውድቅ ሆነ።
ከትናንት በስቲያ በዋለው ችሎት በዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴን ያስደሠተ የፍርድ ውሳኔ እንዳገኙ ነው ታማኝ የመረጃ ምንጮቻችን የገለፁልን።
እንደእነዚሁ የመረጃ ምንጮቻችን አገላለፅ ከሆነ እነ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴን ከሠውበት የነበረው ሀገር አቀፍ የስፖርት ማህበራት ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ ለመወሠን ተሻሽሎ የወጣው መመሪያ ቁጥር 50/2014 ን አስመልክቶ ጉዳዩን ሲመረምር የነበረው ፍ/ቤት መመሪያው ከአለም አቀፍ ህግ በተለይም ደግሞ ከኦሎምፒክ ቻርተር ጋር የሚጋጭ ነው በሚል ክሱ ውድቅ መደረጉን የፍ/ቤት ምንጮቻችን በተለይ ለሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል ገልፀዋል።
ሁለቱን ወገኖች ግራና ቀኝ ሲያከራክር የቆየው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ የፌዴራል አስተዳደር ስነ-ስርዓት በዋለው ችሎት በእነ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ የቀረበው ክስ “ሀገር አቀፍ የስፖርት ማህበራት ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ ለመወሠን ተሻሽሎ የወጣው መመሪያ ቁጥር 50/2014″አለም አቀፍ ህጉን በተለይም ከኦሎምፒክ ቻርተር ጋር የሚጋጭ ነው በማለት ክሱን ውድቅ ማድረጉን የፍ/ቤት ምንጮቻችን ገልፀውልናል።
በዕለቱ ጉዳዩን ሲመረምር የዋለው ችሎት መመሪያው ሊከለስ ይገባል በማለት ክሱን በፌዴራል አስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ ቁጥር 1182/2013 አንቀፅ 16(2) መሠረት ከመረመረ በኃላ ለእነ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ክስ መነሻ የሆነው መመሪያ ውድቅ ተደርጎ የይግባኝ መብትም ተጠብቆ መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት እንዲመለስ ውሳኔ ማሳለፉን ምንጮቻችን ካደረሡን ዜና ለማወቅ ተችሏል።
