የእንግሊዝ መንግሥት ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትና ታዳጊዎች ማኅበራዊ ሚዲያዎችን እንዳይጠቀሙ የሚከለክል እገዳ ይፋ አደረገ። ይህ አዲስ መመሪያ እ.ኤ.አ. በ2027 መተግበር እንደሚጀምርም አስታውቋል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኬር ስታርመር ሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ይህንን አዲስ ፖሊሲ ይፋ ባደረጉበት ወቅት፤ ውሳኔው ሕፃናትን ከበይነ-መረብ (online) ጉዳቶች ለመጠበቅ እና «ሊኖራቸው የሚገባውን የልጅነት ጊዜ» እንዲያሳልፉ የተጣለ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ውሳኔ የተወሰነው መንግሥት «በኦንላይን ዓለም ውስጥ ማደግ» በሚል መሪ ቃል ካካሄደውና ከ116 ሺህ በላይ ምላሾች ከተሰበሰቡበት ሰፊ ምክክር በኋላ ሲሆን፤ በጥናቱም ከዐሥር ወላጆች መካከል ዘጠኙ (90 በመቶው) ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎች የሶሻል ሚዲያ የዕድሜ ገደብ እንዲቀመጥ መደገፋቸውን አረጋግጧል።
በአዲሱ ሕግ መሠረት በተጠቃሚዎች እርስ በርስ ግንኙነት እና በአልጎሪዝም በሚመሩ ይዘቶች ላይ የሚሰሩት እንደ ቲክቶክ፣ ኢንስታግራም፣ ስናፕቻት፣ ፌስቡክ፣ የዩቲዩብ ማኅበራዊ አገልግሎቶች እና ኤክስ (X) ያሉ ዋና ዋና የሶሻል ሚዲያ መድረኮች ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ተጠቃሚዎችን የማገድ ግዴታ ይኖርባቸዋል።
ይሁን እንጂ ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ እንደ ዋትስአፕ (WhatsApp) ያሉ የመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች ከዚህ እገዳ ውጭ ተደርገዋል።
የእንግሊዝ መንግሥት ከዚህ በተጨማሪ የቀጥታ ሥርጭቶችን (livestreaming) መገደብ፣ ከአዋቂ እንግዶች ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶችን መቆጣጠር እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የሚሰሩ የፍቅር አጋዥ የውይይት መተግበሪያዎችን መከልከልን ጨምሮ ሰፊ የደኅንነት ጥበቃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ አቅዷል።
እንዲሁም የሰዓት ገደቦችን መጣል እና ሰዎችን ሱስ የሚያስይዙ እንደ «ማለቂያ የሌለው ሰክሮሊንግ» (infinite scrolling) ያሉ የአጠቃቀም ይዘቶች ላይ ገደብ ማድረግን የመሰሉ ተጨማሪ እርምጃዎችን እያጠና ይገኛል።
የሶሻል ሚዲያ ኩባንያዎቹ ጥብቅ የሆነ የዕድሜ ማረጋገጫ ሥርዓት እንዲዘረጉ የሚጠየቁ ሲሆን፤ ረቂቅ ሕጉም ከመጪው የፈረንጆቹ ገና በዓል በፊት ለፓርላማ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
ቢቢሲ (BBC) እንደዘገበው ከሆነ ይህ እገዳ ቀደም ሲል እንግሊዝ ካጸደቀችው የኦንላይን ደኅንነት አዋጅ (Online Safety Act) የቀጠለ ሲሆን፤ ውሳኔው የወጣው የሕክምና ባለሙያዎች፣ የሕግ አስከባሪዎች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና በጉዳዩ የተጎዱ ቤተሰቦች ከልክ ያለፈ የሶሻል ሚዲያ አጠቃቀም በታዳጊዎች የአእምሮና የአካል ደኅንነት ላይ እያደረሰ ስላለው ተፅዕኖ ያላቸው ስጋት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመጣበት ወቅት ነው።
ምንም እንኳ የተላለፈው የዕገዳ ውሳኔ በብዙ ወላጆች እና በሕፃናት መብት ተሟጋቾች ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ ያገኘ ቢሆንም፤ እንደ ሜታ (Meta)፣ ዩቲዩብ እና ስናፕቻት ያሉ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ግን ይህ ገደብ ታዳጊዎችን ቁጥጥር ወደ ማይደረግባቸው ሌሎች የበይነ-መረብ ክፍሎች እንዲሸሹ ሊያደርጋቸው እንደሚችልና ሕጉን በተግባር ለማዋልም አስቸጋሪ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።
አንዳንድ ተቺዎችም አጠቃላይ እገዳ ከመጣል ይልቅ በኩባንያዎቹ ጎጂ ይዘቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ይበልጥ ውጤታማ መሆኑን በመጥቀስ የውሳኔውን አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ አስገብተውታል።
