የዳሸን ባንክን 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው የዳሸን ኤክስፖ የባንኩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች በተገኙበት በዋናው መሥሪያ ቤት በዛሬው እለት ተከፍቷል፡፡
ከሚያዚያ 15 እስከ ሚያዚያ 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለዘጠኝ ቀናት በሚቆየው በዚህ ኤክስፖ የዳሸን ባንክን አመሰራረትና የሶስት አስርት ዓመታት ጉዞ የሚገልፁ አውደ ርዕዮችና ከዳሽን ባንክ ጋር አብረው የሚሰሩ የተለያዩ ተቋማት ምርትና አገልግሎቶች እንደሚቀርቡበት ተገልጿል፡፡
የዳሸን ኤክስፖ በየዕለቱ የተለያዩ ስያሜዎችን በመወከል የሚከናወን ኹነት እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን፣ ባንኩ ከደንበኞች የአገልግሎት ተሞክሮና ባህል ጋር በማዛመድ የተገበራቸውን አሰራሮች፣ ከቁልፍ አጋር ተቋማት ጋር ያለውን መስተጋብር ፣ ባንኩ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ በተለይም ከዲጂታል አገልግሎት ስርፀት ቀዳሚነት ጋር በተገናኘ ያከናወናቸውን አበርክቶዎች ያስተዋውቃል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ዳሽን ባንክ ሴቶችን በሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ የማብቃት መርህን በመከተል እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራትን፣ ስምንተኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የዳሸን ባንክ የወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት (ሸሪክ) ተጨባጭ ስኬቶች እንዲሁም የፋይናንስ ልህቀትንና አካታችነትን በተመለከተ የባንኩን ጉልህ ሚና የሚያሳዩ ስራዎች በኤክስፖው ላይ እንደሚቀርቡ ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም ከሚያዚያ 15 እስከ ሚያዚያ 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለዘጠኝ ቀናት በሚቆየው በዳሸን ኤክስፖ “ ደም በመለገስ ህይወትን ያድኑ!” በሚል ስያሜ የደም ልገሳ መርሐ ግብር ተዘጋጅቷል፡፡
ዳሸን ባንክ የተመሰረተበትን 30ኛ ዓመት ከጥር 2018 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ መርሃ-ግብሮች እያከበረ ይገኛል፡፡ከ30 ዓመት በፊት በ11 ባለ ራዕይ መሥራቾች የተቋቋመው ዳሸን በአሁኑ ወቅት በመላው አገሪቱ ከ900 በላይ ቅርንጫፎች፣ ከ8 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች፣ ከ2.2 ሚሊዮን በላይ የሱፐር አፕ ተጠቃሚ ደንበኞች፣ ከ19 ሺህ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞች ያሉት የግል ባንክ ነው::
