የሩሲያ ክርስቲያኖች ከኢራን ሙስሊም ማህበረሰብ ጋር መልካም ግንኙነት አላቸው ሲሉ የሞስኮው ፓትርያርክ ኪሪል ገለጹ።
የሞስኮው ፓትርያርክ ኪሪል ይህን ያሉት የእስላማዊ አብዮት መሪ አያቶላ ሰይድ ሙዥታባ ኻሜኒ ለላኩላቸው መልእክት ምስጋናቸውን ባቀረቡበት ወቅት መሆኑን የኢራኑ ታስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።
ፓትርያርኩ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና የኢራን ሙስሊሞች በሥነ-ምግባር ጉዳዮች፣ በሃይማኖት ሚና እና በቤተሰብ እሴቶች አስፈላጊነት ላይ ተመሳሳይ አመለካከት እንዳላቸው ጠቁመው፤ በአንዳንድ አገሮች የሥነ-ምግባር እና የቤተሰብ ተቋም መሸርሸሩን በማንሳት ገስጸዋል።
በተጨማሪም በኢራንና በሩሲያ መካከል ያለውን የሃይማኖት፣ የአካዳሚክ እና የሳይንስ ትብብር ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል ሲል ዘገባው አክሏል።
የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በእነአሜሪካ ጥቃት ለተገደሉት ለቀድሞው መሪ አያቶላ ሰይድ አሊ ኻሜኒ ሽኝትና የቀብር ሥነ-ሥርዓት ስለላከችው ልዑክ የጠቀሱት ፓትርያርኩ፣ የልዑኩ አባላት ከኢራን ባለሥልጣናትና ተርታው ሕዝብ ሞቅ ያለ አቀባበል እንደተደረገላቸው ተናግረዋል።
ይህም በኢራንና በሩሲያ መካከል፣ እንዲሁም በእስልምና እና በክርስትና ተከታዮች መካከል ያለውን የቀረበ ግንኙነት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
የሩሲያው ፓትርያርክ ከዚህ በፊት ስለቀድሞው የእስላማዊ አብዮት መሪ አያቶላ ሰይድ አሊ ኻሜኒ የሃዘን መግለጫ ማስተላለፋቸውንና አዲሱ መሪ በመመረጣቸው የእንኳን ደስ አለዎት መልእክት መላካቸውን ዘገባው አስታውሷል
