አገዛዞች በሚፈጥሩት የተዛባ አስተሳሰብ፤ ኢትዮጵያ ዜጎቿ በተናጠል እና በጋራ የሚያዝኑባት የመከራ ምንጭ ከሆነች ውላ አድራለች፡፡ የነገድ አገዛዝን ብቸኛ አማራጭ አድርገው የተከተሉ ገዥዎች ደግሞ አንዱን ዜጋ ነቅሎ ሌላውን ለመትከል እየባዘኑ ይገኛሉ፡፡ ይህ አስተሳሰብ ዜጎችን አጥፊና ጠፊ ከማድረግ ያለፈ አንዳች ፋይዳ እንደሌለው ባልደራስ አበክሮ ያስገነዝባል።
በአዲስ አበባ ከተማ ከ15 ዓመታት በላይ በስራ ላይ የነበሩ የታክሲ ተራ አስከባሪዎች ማህበራት ከስራ ውጪ መሆናቸውን ባልደራስ ከስራ ተፈናቃዮች በደረሰው መረጃ አረጋግጧል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ላለፉት 15 ዓመታት የታክሲ ተራ ማስከበር ስራ ላይ የነበሩ ቁጥራቸው እስከ 9ሺ የሚደርሱ ተራ አስከባሪዎች ከስራ ውጭ መሆናቸውን የተራ አስከባሪ አባላት ለባልደራስ አሳውቀዋል፡፡ የታክሲ ተራ አስከባሪ ማህበራቶች በከተማዋ በሚገኙ በስርዓቱ የወረዳ አደረጃጀቶች አማካኝነት በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ተደራጅተው በስራ ላይ የቆዩ ናቸው፡፡
ለአስራ አምስት ዓመታት የታክሲ ተራ አስከባሪዎች ሆነው ሲሰሩ የቆዩት የከተማዋ ተወላጆችና የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች መሆናቸውንም ቅሬታ አቅራቢዎቹ አስገንዝበዋል፡፡
ተራ አስከባሪዎቹ ስራ መልቀቅ የማይችሉበት ደረጃ ላይ መሆናቸውን ለብልፅግና ሹማምንት አቤት ቢሉም ሰሚ አካል ማግኘት አለመቻላቸውን ተናግረዋል። ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በታክሲ ተራ አስከባሪዎች ላይ የተፈፀመው የስራ ማፈናቀል አግባብነት የጎደለው መሆኑን ያምናል፡፡
ነባር የታክሲ ተራ አስከባሪዎች ሕይወታቸውን መምራት የሚያስችል ሁኔታ ባልተፈጠረበትና ወደ ተሻለ የኑሮ ደረጃ ባልተሸጋገሩበት ሁኔታ በአዲስ ተራ አስከባሪ መተካቱ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑን ባልደራስ ይገነዘባል፡፡
ዜጎች አምራች ሆነው በሚያተርፉበት ስራ ላይ እንዲሰማሩ ከማድረግ ይልቅ ሌላ ተጨማሪ ገንዘብ ጠያቂ በሚሆኑበትና ሕዝብ ላይ ጫና እንዲፈጠር በሚያደርግ አካሄድ፣ አንዱን አባሮ ሌላውን መተካት፣ የኢኮኖሚን መሠረተ ሀሳብ ካለ መረዳት እንደሆነ ባልደራስ ይገልፃል፡፡ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ፣ መንግሥት በተራ አስከባሪዎች ላይ የወሰደው እርምጃ ያልተጠና እና ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ ያላገናዘበ ውሳኔ መሆኑን በማስገንዘብ የሚከተሉትን ማሳሰቢያዎች ያቀርባል፦
I. ከስራ የተባረሩ የታክሲ ተራ አስከባሪዎች ሕይወታቸውን በዘላቂ ሁኔታ መምራት የሚያስችል ስራ በአፋጣኝ እንዲመቻችላቸው፣
II. የታክሲ ተራ አስከባሪዎች በስራው ላይ ረጅም ልምድ ያላቸው ስለሆነ በከፊል አልያም በሙሉ ወደ ቀድሞ ስራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲመቻች፣
III. መንግሥት በዜጎች ላይ እየፈጠረ ያለውን ስልታዊ ማፈናቀልና ችግርን የማባባስ አካሄድ እንዲያቆም ባልደራስ ያሳስባል።
በመጨረሻም ከታክሲ ተራ ማስከበር ስራ የተፈናቀላችሁ ዜጎች፣ መብታችሁን በህጋዊ መንገድ እንድትጠይቁ እያሳሰበ ፣የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ትብብር እንዲያደርጉላችሁ ባልደራስ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
