መጋቢት 16 ቀን 2018 አ.ም በኢትዮጵያ በሰብአዊ መብትና በልማት ስራዎች ላይ የተሰማሩት አክሽን ፎር ዘ ኒዲ ኢትዮጵያ እና ሀቢታት ፎር ሂውማኒቲ ኢትዮጵያ በጋራ ለመስራት የአጋርነት ስምምነት ተፈራርመዋል::
ስምምነቱ በተለይ የመኖሪያ ቤት ችግር ላለባቸውና ለተጋላጭ ማህበረሰቦች ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ተገልጿል።
በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተገለጸው፥ ይህ ስምምነት በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ያሳድገዋል።
አክሽን ፎር ዘ ኒዲ በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እና በመስክ ስራ ያለውን ልምድ፣ ሀቢታት ፎር ሂውማኒቲ ደግሞ በቤት ግንባታ እና በማህበረሰብ ልማት ካለው ዓለም አቀፍ እውቀት ጋር በማቀናጀት ለውጥ ለማምጣት ማለማቸውን ገልፀዋል።
ሁለቱ ተቋማት ደረጃውን የጠበቀ የመኖሪያ ቤት እና የመጠለያ አቅርቦት ለመስጠት፣የንጹህ መጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን አገልግሎት ለማቅረብ ፣የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችሉ የልማት ስራዎች ለመስራት እና የሴቶችና የዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ ለመስራት ማቀዳቸውን አስታውቀዋል።
የአክሽን ፎር ዘ ኒዲ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳሊሁ ሱልጣን በንግግራቸው፥ ይህ ስምምነት በተግባር ወደ ሚለካ ውጤት ተቀይሮ የማህበረሰባችንን ክብርና ጽናት እንደሚያረጋግጥ እናምናለን ብለዋል።
በተጨማሪም በስምምነቱ ወቅት ንግግር ያደረጉት የሀቢታት ፎር ሂውማኒቲ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይጥና ተካለኝ፥ ስምምነቱ ዓለም አቀፍ የቴክኒክ ዕውቀትን ከሀገር በቀል የመስክ ተሞክሮ ጋር በማቀናጀት ለተጋላጭ ወገኖች የሚደረገውን ድጋፍ ወደ ላቀ ደረጃ ይሸጋገራል ብለዋል።
አክለውም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች፣ ሴቶችና ወጣቶች የቤትና የመጠለያ ችግሮቻቸው በተግባር እንዲፈቱ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አስረድተዋል።
