ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ለኮንግረስ ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት ተቃውሞ ያሰሙትን የምክር ቤት አባላት ኢልሃን ኦማር እና ራሺዳ ትላቢን “ወደ መጡበት መልሰን መላክ አለብን” አሉ።
ፕሬዝዳንቱ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ንግግር ያደረጉበት ‘ስቴት ኦፍ ዘ ዩኒየን’ የተባለው የምክር ቤት ንግግራቸው ሲካሄድ ዴሞክራቶች በተለያየ መልኩ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ነበር።
ትራምፕ ስለ ስደተኞች እና ሚኒሶታ ውስጥ በሚገኙ የሶማሊ አሜሪካ ማኅበረሰብ አባላት ይፈጸማል ስላሉት የማጭበርበር ተግባር በሚናገሩበት ወቅት የግዛቱ ተወካይ የሆኑት ኢልሃን ኦማር በተደጋጋሚ ፕሬዝዳንቱ ላይ ሲጮኹ ታይተዋል።
የኮንግረስ አባሏ “ይሄ ውሸት ነው፣ ውሸታም ነዎት” ሲሉ እርሳቸውን በተመለከተ ሲናገሩ ለነበሩት ትራምፕ ምላሽ ሰጥተዋል።
ከኢልሃን አጠገብ ተቀምጠው የነበሩት የሚቺጋን ግዛት ተወካይዋ ራሺዳም ኢልሃንን ተቀላቅለው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ትሩዝ በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ ሁለቱን የምክር ቤት አባላትን “ዝቅተኛ የማገናዘብ ብቃት ያላቸው” ሲሉ ዘልፈዋል። በስብሰባው ላይ “ከቁጥጥር ውጪ ሆነው ሲጮሁ” ነበርም ብለዋል።
ሁለቱ ፖለቲከኞች “ልክ እንደ እብዶች፣ አእምሮአቸው እንደተቃወሰ እና የታመሙ ሰዎች የፈጠጠ እና የደፈረሰ ዐይን ነበራቸው፤ በእውነቱ ከሆነ የሕክምና ተቋም ውስጥ መገባት ያለባቸው ነው የሚመስሉት” ብለዋል።
አክለውም “በተቻለ ፍጥነት ወደ መጡበት መልሰን መላክ አለብን” በማለት ጽፈዋል። “አሜሪካን ለመጉዳት እንጂ ለመርዳት ማድረግ የሚችሉት ነገር የለም” ብለዋል።
ትራምፕ ይህንን ቢሉም ሁለቱም የምክር ቤት አባላት ዜግነታቸው አሜሪካዊ ነው።
