ወደ ርዕሰ ጉዳዩ ከመግባቴ በፊት ሁለት ነገሮችን ለማስገንዘብ ወደድኩ፡፡ አንደኛው ይህ ርዕሰ ጉዳይ በመጀመሪያው የመጽሐፌ ህትመት ላይ ያለመኖሩ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ በዚህ ሁለተኛው ህትመት ላይ የተጨመረ ነው ሊባል ይቻላል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ለመግለጽ የምወደው ደግሞ፡- “የመሪዎች ሴራ በኢትዮጵያ” በተሰኘው መጽሐፌ የተካተቱት ርዕሰ ጉዳዮች ድምዳሜዎችና ፖለቲካዊ ትንታኔዎች በአጠቃላይ የእኔ የቀለብ ስዩም የግል እይታና አመለካከቶች መሆናቸውን ለአንባቢያን መግለጽ እወዳለሁ፡፡ አበው፡- “የማይተማመን ጓደኛ በመንገዱ ይማማላል” እንደሚሉት መሆኑ ነው፡፡ በቅኔ ተወልዶ በሰምና ወርቅ ለተራቀቀ ሕዝብ ከዚህ በላይ ተጉዞ ለማብራራት መሞከር ትርፉ ድካም ይመስለኛልና ይበቃል፡፡
ወደ ዋነኛው ርዕሰ ጉዳይ እንግባ፡- ህወሐት በአዲስ መልክ ያደራጃቸው ናቸው የሚባሉና የተወሰኑ አማጽያንን የወከሉ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ውስን ሰዎች በሀገር አሜሪካ ተሰብስበው “ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት” መመስረት አስመልክቶ አዲስ አዲስ መወያያ ሰነድ በማርቀቅ ላይ ስለመሆናቸው ወይም ደግሞ እንዳረቀቁ ወሬው በስፋት ሲራገብ ይስተዋላል፡፡
በበኩሌ በንድፍ ሀሳብ ደረጃ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግሥት ቢቋቋምና አዲስ የዚህ ዐይነቱን ሰነድ ቢረቀቅ ደስተኛ ነኝ፤ እደግፋለሁም፡፡ ይሁን እንጅ እነዚህ በሀገር አሜሪካ ተሰብስበው ህገ-መንግስቱን በማረቀቅ ላይ ናቸው የሚባሉ ሰዎች የኢትዮጵን ህዝብ ውክልና አላቸው ወይ? ህዝባዊ ተቀባይነታቸውስ ምን ያህል ነው?፤ የሚባለውን በቅንነት እንቀበል ቢባል እንኳ የሀገሪቱን ነባራዊና ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታ ይፈቅዳል ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ከባድና አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ ህወሕትና በአዲስ መልክ አደራጃቸው የሚባሉት አማፂዎች ጦርነቱን በአሸናፊነት ቢወጡ ኑሮ እቅዳቸውን ተግባራዊ ሊያደርጉ እንደሚችሉ መገመት ይቻል ነበር፡፡ ወይም ደግሞ ሀገሪቱን በመንግሥትነት ከሚመራት የብልጽግና ፓርቲ ጋር በሚኖር ድርድር ተግባራዊ ሊደረግ እንደማይችል ማሰብ ይቻላል፡፡
ይሁን እንጅ እነዚህን መልካም ምኞቶችን ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ምክንያቶች ሊሆኑ የሚችሉ አማራጮች እጅግ በጣም ጠባብ ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ለምሳሌ ህወሐት በፈጸማቸው የሕይወትና የንብረት ውድመቶች እንዲሁም በደረሱት የሞራልና የአካል ስብራቶች ምክንያት አብዛኛውን የሀገሪቱን ህዝብ ስሜቱ ተነክቷል፡፡ ተቆጥቷል፤ አቂሟልም፡፡ በሁሉም አቅጣጫ ያሉት የፖለቲካ ሃይሎች ሲስማሙ እንኳ ጤናማ የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነቶችን ለማምጣት ለዓመታት ያለመታከት መስራትን ይፈልጋል፡፡ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ የሲቪክ ተቋማት፣ ሕዝባዊ ማህበራትና መገናኛ ብዙኃን የጋራ አንድነት ፈጥረው ሳያሰልሱ ማስተማርም ይጠበቅባቸዋል፡፡
አንድ ነገር እርግጠኛ ሆኜ መናገር እችላለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጦርነቱን በአሸናፊነት ይወጣል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሉአላዊነቷን ጠብቃ እንደምትኖር ሀገር ጸንታ በሁለት እግሮቿና በሙሉ ሃይሏ ጸንታ ትቆማለች፡፡ ዘለቄታዊ መፍትሔ ለማምጣትና ዘለቄታዊ ሰላም ለማስፈን ግን ጦርነቱን በአሸናፊነት መወጣት ብቻ በራሱ በቂ እንዳልሆነ እገነዘባለሁ፡፡
በእኔ እምነትና አመለካከት የነገ ሕይወታችንን የምናሳምረው የትላንት ጉድለቶቻችንን ነቅሰን በማውጣት የእርምት እርምጃዎችን የወሰድን እንደሆነ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የዛሬው ችግራችን የሚመዘዘው የትላንት እኩያን ቡድኖች አርቅቀው በአዘጋጁትና ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ካነገበው ሕገ-መንግሥት የፈለቀ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ መዘዘኛ ገንጣይ ሕገ-መንግሥት ከኢትዮጵያ ሕዝብ እውቅናና ስምምነት ውጪ በሃይልና ጉልበት በሕዝብ ላይ የተጫነ እርግማን ነበር ቢባልም ስህተት አይደለም፡፡ ዛሬ ዳግም ትናንሽ ጉጥጥ ጉጠኞችን በኮንፌድሬሽን ቀጫጭን ክሮች ደረት ምናባዊ ኢትዮጵያን ማምጣት ነው የተፈለገው፡፡ ይህ ደግሞ የሕሰዝቡን ፍላጎት አይደለም፡፡ ዘለቄታዊ መፍተሔ አያመጣም፡፡ በእኔ አመለካከትና ድምዳሜ ዘለቄታዊ ሰላምና መፍትሔም ማምጣት የሚቻለው በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ሲመሰረትና ሲሰራበት ብቻ ነው ባይ ነኝ፡፡ እንደ አብነት የሚሆኑትንም ለመጥቀስ ያህል፡-
- እያንዳንዱ በግለሰብም ሆነ በቡድን ደረጃ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣትና ለሕሊና መኖር ገንዘቡ ማድርግ ይኖርበታል፡፡
- የሀገሪቱን ሉአላዊ አንድነትና ሕዝባዊ ጠቀሜታ መሰረት አድርጎ መቀራረብ፣ መወያየትና መደራደርም የግድ ነው፡፡
- ብሔራዊ እርቅ ማካሄድ፣ አሁን ያለው ሕገ-መንግስት ለሀገርና ለሕሰዝብ የማይበጅ በመሆኑ ተወግዶ በአዲስ እይታ፣ በአዲስ መንፈስ አዲስ ህገ-መንግስት ማዘጋጀትም ወሳኝነት አለው፡፡ ይህም ሲባል የተወሰኑ ቡድኖች የራሳቸውን ፍላጎት በሕዝብ ላይ በሚጭኑበት ከላይ ወደ ታች በሚወርዱ አስራር ሳይሆን ሕዝቡን ቀጥተኛ ተሳታፊ በሚሆንበት መልኩ መከናወን ይኖርበታል፡፡
- የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃይማኖትና ጎጠኝነትን መሰረት አድርገው መመስረታቸው ቀርቶ ሀገርና ህዝብን በሚጠቅሙ ህዝባዊ ፋይዳዎች ማስገኘት የሚችሉ የአመለካከት ልዩነቶችን ያማከሉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ የሀገሪቱን አከላለልን በጎሳና በቋንቋ መሆኑ ቀርቶ ለአስተዳደር በሚያመቹ መልካም ምድራዊ አወቃቀሮችን መከተል ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም የዘር ፖለቲካ በኢትዮጵያ ህግ ሊታገድ ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡
- የኢትዮጵያን መፃኢ ዘመን ብሩህና የተሻለ ለማድረግ የትምህርት ስርአቱን ማሻሻል ወሳኝነት አለው፡፡ ኢትዮጵያዊ አንድነት ለሀገርና ለህዝብ መታመንን፣ ሰውን በሰውነቱ ብቻ የማክበር አስፈላጊነት፣ ስለፍቅርና ሰላም ስራ ወዳድነትን፣ መተሳሰብና መተማመንን፣ በመልካም ስነ-ምግባርና በፈርሀ እግዚአብሔር ስለመታነጽና፣ አድሎና ሙሰኛነትን የሚጸየፍ ትውልድ የሚያፈራ፣ በአጠቃላይ መልካም እሴቶችን የሚያጎላብቱ ትምህርቶች በስርዓተ ትምህርቱ ማካተት ያስፈልጋል፡፡
የሕግ ሥርዓቱን ማዘመን ለእውነትና ለህሊናቸው ብቻ ያደሩ ዳኞችን በመመልመልና በማፍራት የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይበጃል፡፡ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ወሳኝና ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ እንዲቻል ሰዎች የአመለካከት ልዩነት በመያዛቸው ብቻ መታሰር፣ መሰደድና መንገላታትም የለባቸውም፡፡ በአመለካከት ልዩነታቸው የታሰሩም ካሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈታት የዘለቄታዊው ሰላም መገኛ ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡