
ዳግማዊ ሲሳይ ከሲዊድን
ብልፅግና እንደ ሃይማኖት የበቀለው በ19ኛው ክፍለ ዘመን ነው። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጅማሮ ገደማ ከፔንጤ ቆስጤ (ፕሮቴስታንት) ከሆነው የሀይማኖት ጎራ ራሱን ነጥሎ የወጣ ነው። ኦራል ሮበርትስ በ1947 እ.ኤ.አ. የብልፅግና ወንጌል ሀይማኖትን አስተምህሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰበከና የብልፅግና “ሀይማኖትን” መርህ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀ እንደሆነ መረጃዎች ይናገራሉ። ስለ “በፈጣሪ ማመን” ሲሰብክ “ለአምላክ የሰጠ በሰባት ዕጥፍ ጥቅል ተመልሶ እንደሚሰጠው፤ ለሰጪው የሚሰጠው ምንጩ ያልታወቀ የመልስ ስጦታ ከአምላኩ እንደተቸረው እንደሚቆጠር ይኽ ሰው ተናግሯል።
የብልፅግና ወንጌል የሀይማኖት መርሆ ድንጋጌ በዋናነት “እግዜአብሔር የሰው ልጆች እንዲበልፅጉ እንደሚፈልግ በተለይም ደግሞ በምድራዊው ህይወታቸው የገንዘብ ባለፀጋ እንዲሆኑ ፅኑ እምነቱ እንደሆነ ይተነትናል።እንደ ብልፅግና ወንጌል እምነት “ሀብታሞች ሀብታም የሆኑት በፈጣሪያቸው ትልቅ ዕምነት ስላላቸው በመሆኑ፤ ድሆች ደግሞ ድሃ የሆኑት በፈጣሪያቸው ላይ ዕምነት ስለሌላቸው እንደሆነ ኦራል ሮበርትስ በድፍረት ሲሰብክ ኖሯል።
የብልፅግና ወንጌል ዋነኛ ግብ የሰው ልጆች ምድራዊ ፍላጎታቸውንና እቅዳቸውን አሳክተው ማየት እንዲችሉ ማድረግ ነው። ብልፅግና በዋናነት የሚመነጨው የራስን ግብ፣ፍላጎትና ምኞት በራስ ምልከታ ውስጥ ቀንብቦ፤ በራስ እሳቤ ውስጥ ውጦ ፣ተመስጦና ሀይል ሰብስቦ ወደ ተግባር መቀየርን በደንብ ይሰብካል።
ከዚህ ሁሉ በፊት የመጀመሪያው የአለም ጦርነት ወቅት ዩ ኤስ አሜሪካ ውስጥ “የማህበራዊ ብልፅግና ወንጌል” /Social Prosperity Gospel/ የሚባል ሀይማኖት ተፈጥሮ ነበር። ይህ ሀይማኖት በአሜሪካ ውስጥ በወቅቱ በብልፅግና ምትክ፤ ውድቀትና ድህነትን በማህበረሰቡ ላይ በማስከተሉ። በተለይም በከተሞች አካባቢ ተቀባይነትን በማጣቱ ከስሞ ቀረ።
የካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ “የብልፅና ወንጌል በዘርና በፖለቲካ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ በዘመነ ትራምፕ” በሚል በየካቲት 11/2022 እ.ኤ.አ. ባሳተመው አንድ ፅሁፍ የብልፅግና ወንጌል በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ጠልቆ በመግባት በዘር (ጥቁሮች) ላይ እያሳደረ ያለው መጥፎ ተፅዕኖ አይሎ ተገኝቷል ብሏል።ይህ ሀይማኖት የአሜሪካ ፖለቲካ ዋነኛ ዘዋሪ እስከመሆንም ደርሷል። ሌሎች ተደጋጋሚ ጥናቶችም እንዳመለከቱት የብልፅግና ወንጌል በጥቁር አሜሪካውያን አናሳዎችና በተለይም ጥቁር ተቃዋሚዎች ፤ በተቃራኒው የከሰመውን የማህበራዊ ብልፅግና ወንጌልን ለማንሳት በሚንደፋደፉት መካከል ትልቅ ውጥረትን ፈጥሯል። የማህበራዊ ብልፅግና ወንጌል ዋነኛ ማዕከል የሆኑት ጥቁር የሀይማኖቱ መሪዎችና ጥቁር ተከታዮቹን ነው።
ይህ ጥናት እንደሚናገረው የብልፅግና ወንጌል ማንነቶችና ዕምነቶች ማጠንጠኛ በዋናነት በዘርና በሀይማኖቶች መካከል ንፅፅሮሽ በማስቀመጥ የፖለቲካው ውጤት ላይ የራሱን ተፅዕኖ በማድረግ በዘር በዕምነት ፍልስፍናና በሀይማኖታዊ ማንነት ላይ መወሰንን ግቡ በማድረጉ ስጋት ፈጥሯል።
በየካቲት 04/2021 እ.ኤ.አ. /The Politics and Problems Of Prosperity Party Gospel/ በሚል ርዕስ ሙሉብርሃን ባልኸኝ ያስነበበው ፅሁፍ ነገሩን በደንብ እንድናጤነውና እንድናስብበት የሚያስገድደን ነው። የብልፅግና ፖለቲካ ፓርቲ መሪ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ የዚህ ሀሳብ አቀንቃኝ፣ ጠንሳሽና መሪ ሲሆኑ በተደጋጋሚ በተለያዩ መድረኮች ላይ የሚያሰሟቸው ንግግሮች መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ዕውነት የሸመጠጡ ባዶ ተስፋን ያዘሉ ይመስላሉ። በ2 አመት የትግራይ የዕርስ በዕርስ ጦርነት 25 ቢሊየን ብር እንዳወጣች የተናገረችው ሀገሬ ኢትዮጵያ፣ በሀገሪቱ አራቱም ማዕዘናት፣ በጦርነት፣የሰው ዕገታ፣ማንነት ላይ ያነጣጠረ ግድያና መፈናቀሎች ወጥረው ይዘዋት፤ ከ15 ቀን የማያልፍ የውጭ ምንዛሬ እጦት፣ በብድር የመንግስት ሰራተኞችን ደሞዝ መክፈልና የሙስናው መንሰራፋት ሰቅዞ የያዛት ሀገሬ ኢትዮጵያ አሁንም በቅዠት ላይ ያለው የብልፅግና መንግስት ሀገሪቷን ወደ ብልፅግና እየወሰዳት እንደሆነ ሲናገር ማፈርም፣ መፍራትም መሸማቀቅም እንኳን አላሳየም።
የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 11 ንዑስ ቁጥር
- መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸው፣
- መንግስታዊ ሃይማኖት የሌለ መሆኑን እና
- መንግስት በሀይማኖታዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ እንደማይገባው ሁሉ መንግስትም በሀይማኖታዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ እንደማይገባ ቢደነግግም፤
የኦርቶዶክስ ክርስትናን ተቋማዊ በሆነ መንገድ የማዳከምና አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የመንግስታ የፀጥታ አካላት ጥበቃ (መከላከያና ፖሊስ) የሚያደርጉላቸው የብልፅግና ወንጌል ሰባኪያንን በየቀኑ መመልከት ሰርክ ተግባራችን ሆኗል።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!