‹‹ልጃችሁን ውርዬን ለልጃችን ስጡን!›› በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር

Date:

ጋ – ብቻ፤ ‹‹አዳም ከሔዋን ጋ – ብቻ፤ ሔዋንም ከአዳም ጋ – ብቻ›› ይልሃል፤ ቆሞ ቀርነትን በብርቱ የሚፀየፍ፣ መልካም ጋብቻን አብዝቶ የሚሰብክ አንድ መጽሐፍ፡፡ ወቅቱ ታዲያ የመተጫጫም፤ ከዛም አልፎ የመጋቢያም አይደል!? ለጋ – ብቻ፤ ሩጫው ጦፏል፡፡

ድንገት አብሮ አደግህ፤ ወይም የሥራ ባልደረባህ፤ ወይም የምታውቀው፣ ግን ብዙም ካንተ ጋር ቀረቤታ የሌለው ሰው ይመጣና፣ ‹‹እባክህ ሽማግሌ ሁንልኝ?›› ይልህና ተነስተህ ትሄዳለህ፡፡ ለምን? ለሽምግልና፡፡ ለምን ዓይነት ሽምግልና? ‹‹ልጃችሁን ለልጃችን!?›› ለሚባልበት፡፡

ታዲያ አንተ ይኼኔ ባህሉን ማወቅ ይኖርብሃል፡፡ ወይም እንደኔ የሚደርስብህን ቅሌት የመቀበል ትልቅ ፀጋ ከላይ ሊሰጥህ ይገባል፡፡

የጀበና ቡና የሚጠጣበት ቤት ውስጥ ከወዳጆቼ ጋር ቁጭ ብያለሁ፡፡ ድንገት ምላስ የምታክል ከረቫት ያሰረ ወጣት እየተንቀዠቀዠ መጣ፡፡ በዐይን እንተዋወቃለን፤ የቤቱ የቡና ደንበኛ ነው፡፡ በጣም ቸኩሏል፡፡

‹‹አንድ ሽማግሌ ጎደለን፤ የሚከራይ ሽማግሌ ይኖራል?›› አለ ቀልድ በሚመስል ቅላፄ፡፡ ሁላችንም ሳቅን፡፡

‹‹እውነቴን ነው! አንድ ሽማግሌ ጎድሎን ነው!›› አለ ቀልዱን ወደ ምር ለመቀየር ኮስተር ብሎ፡፡

‹‹ጓደኛችን ሽማግሌ ልኮን አንድ ሰው ጎደለብን!›› ቤቱ ውስጥ ያለነውን ልጆች ሁሉ እያየ ነበር የሚናገረው፤ ‹‹እባካችሁ ከእናንተ መሃል አንድ ሰው!›› በሚል ዓይነት፡፡

‹‹ታዲያ ምን ችግር አለው?›› አለች ባለቡናዋ ወደ አንዱ ወዳጃችን እያየች፡፡

‹‹ኧረ እኔ…›› አለ ደንግጦ ወዳጃችን፤ ‹‹ቀጠሮ አለኝ፤ አንድ ቦታ…›› ሲልም ምክንያት ሰጠ፡፡ ሌላውም ተጠየቀ፤

‹‹ኧረ እኔ ሽማግሌ ሆኜ አላውቅም!›› አለ፡፡

‹‹አብሬያችሁ እሄዳለሁ!›› አልኩ እኔ ድንገት፡፡ ልጁ ደስ አለው፡፡ ጊዜም አልሰጠኝም፡፡ ‹‹በል ተነሳ ጎሽ!›› አለኝ ጭንቀቱ ከላዩ ላይ እየተገፈፈ፡፡ ተነሳሁ፡፡ የሆነች መኪና ውስጥ ገባን፡፡ ወደ እጩ ሙሽሪት ቤት ጉዞ ተጀመረ፡፡ በጉዟችን ወቅት እንወያይ የነበረው እጩ ሙሽሪት ቤት ማድረግ ስላለብን ነው፡፡

‹‹መጀመሪያ ሁላችንም እጃችንን ወደ ኋላ አድርገን በአክብሮት እንቆማለን!››

‹‹እሺ!››

‹‹ቁጭ በሉ ካሉን አንቀመጥም!››

‹‹ለምን?››

‹‹መጀመሪያ ለጠየቅነው የሽምግልና ጥያቄ መልስ መስጠት አለባቸው!››

‹‹እሺ!››

‹‹ተግባብተናል!?››

‹‹አዎ!››

ልጂቱ ቤት ደረስን፡፡ ሦስታችንም ፊት እና ኋላ ሆነን ገባን፡፡ የልጂቱ ቤተሰቦች ቤቱን ሞልተውታል፡፡ (ሲያስፈሩ!) እንደተባባልነው እንደገባን ተደርድረን ቆምን፡፡

‹‹ደህና ዋላችሁ!?›› ከወገባችን ሰበር ብለን ሠላምታ አደረስን፡፡

‹‹ደህና!›› አሉ ነገረኛ የሚመስሉ ከእጩ ሙሽሪት ቤተሰቦች መካከል አንዱ አዛውንት ፊታቸውን ቅጭም አድርገው፡፡ (በኋላ ስጠይቅ አጎት ናቸው አሉ፡፡)

‹‹ልጃችሁን ለልጃችን ለመጠየቅ ነው የመጣነው!›› አለ በመቅለስለስ እኔን ይዞኝ የመጣው የቡድናችን መሪ፡፡

‹‹የትኛዋን ልጃችንን?›› አሉ እኛው አዛውንት፡፡ ዘወር ብዬ በቆረጣ አብረውኝ የቆሙትን ልጆች ተመለከትኩ፡፡ እነሱም እርስ በእርስ እየተያዩ ነበር፡፡

‹‹አንደኛዋን!›› አለ የቡድን መሪያችን፡፡

‹‹እኮ የትኛዋን? …ያሉን ልጆች ሦስት ናቸው፡፡››

‹‹ውርዬን!›› አለ የቡድን መሪያችን እፍረት ባቀዘቀዘው ድምፅ፡፡ …ደነገጥኩ፡፡

‹‹ምን? አዛውንቱ በድንጋጤ ጮኹ፤ ሌሎቹ የቤተሰቡ አባላት ሳቅ አፈናቸው፡፡ አንገቱን ሰብሮ ድምፁን ዝግ አድርጎ የሳቀም ነበረ፡፡

‹‹ውርዬ? …የምን ውርዬ? ማለት… የማን ውርዬ?›› ሰውየው እንደተበሳጩ ያስታውቃል፤ ‹‹ምንድን ነው የሚሉት እነዚህ ሰዎች? …ገብቷችኋል?›› ዘወር ብለው የቤተሰባቸው አባላትን ቃኙ፡፡ ሁሉም እየሳቁ ነው፡፡ እኛ ግን በእፍረት ፊት ለፊታቸው ቆመናል፡፡

‹‹ይቅርታ አባት፤ እርስዎ አያውቁኝ ይሆናል፡፡ እኔ ተወልጄ ያደግኩት እዚሁ ነው፡፡›› አለ ተናጋሪው የእኛ የቡድን መሪ የምንተእፍረቱን፤ ‹‹ማዘርም ያውቁኛል፤ ፋዘርም ያውቁኛል፤ እህቶቿም ያውቁኛል! …እኔ የማውቃት በሰፈር ስሟ በውርዬ ስለሆነ ነው!››

‹‹እኛ ግን ውርዬ የምትባል ልጅ የለንም!›› አሉ አዛውንቱ ፊታቸውን ቅጭም እንዳደረጉ፡፡

ሥራችን እርስ በእርስ መፋጠጥ ሆነ፡፡ ‹‹በጎደለ ሙላ›› የመጣሁት እኔ ምንም በማላውቀው ቅሌት ላይ በመጣዴ በሽቄያለሁ፡፡

‹‹እኮ ውርዬን ነው የፈለጋችሁት?›› አዛውንቱ በስላቅ ጠየቁን፡፡ ይኼኔ ቤተሰቡ በሙሉ ድምፁን ከፍ አድርጎ ሳቁን ለቀቀው፡፡

‹‹ይቅርታ አንድ ሁለት ደቂቃ ይሰጠን!?›› አለ እስካሁን ያልተናገረው ልጅ ከመሃላችን፡፡

‹‹እሺ!››

ወደ ውጪ ወጣ፡፡ የሙሽሪትን እህት ግቢ ውስጥ አገኘና ጠይቆ ዋና ስሟን ይዞ መጣ፡፡ …ተናገረ፡፡

‹‹ያሳዝናል! የልጂቱን ሙሉ ስም ይዛችሁ መምጣት ነበረባችሁ!›› አሉ አዛውንቱ፡፡

ሦስታችንም ከወገባችን ሰበር ብለን ይቅርታ ጠየቅን፡፡

‹‹እሺ! ምንድነው የሚሠራው!?›› ጠያቂው ሌላ የቤተሰብ አባል ናቸው፡፡

‹‹ማን?››

‹‹የላካችሁ፤ …ልጃችንን የፈለጋት!››

‹‹የራሱ መተዳደሪያ አለው፡፡››

‹‹እኮ ምንድነው የሚሠራው?››

አሁንም አብረውኝ የቆሙት ሰዎች እርስ በእርስ ተያዩ፡፡ (‹‹የጉድ ቀን አይመሽም!›› አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ዛሬ…›› አልኩ ለራሴ፡፡)

‹‹ልጁ የውጪ ዜጋ ነው፡፡ የራሱ መተዳደሪያ አለው!›› አለ የቡድን መሪያችን፡፡

‹‹ለማወቅ ያህል ምን እደሚሠራ ብትነግሩን፡፡ ልጃችንን ብንሰጠው ሊያስተዳድራት ይችላል ወይ? የራሱ ቋሚ ንብረት አለው ወይ? እዚህስ የት ነው ያረፈው?›› አሉ የመጀመሪያው አዛውንት፡፡

ግራ ገባን፡፡ በተለይ እኔ፡፡ ልጁ አንድ ሽማግሌ ጎደለን ብሎ ይዞኝ ሲመጣ ይህን ሁሉ የሚያውቅ መስሎኝ ነበር፡፡ (…ሲጨንቅ!)

‹‹ልጁ የወንድሜ ጓደኛ ነው፡፡ ወንድሜ እንድተባበረው ስለነገረኝ ነው ሰብሰብ ብለን ከጓደኞቼ ጋር የመጣነው፡፡ ባህሉን ለማክበር ያህል… !›› አለ እኔን ይዞ የመጣው ልጅ እየተቅለሰለሰ፡፡

‹‹ባህልን ማክበር ማለት እኮ ጥንቅቅ አድርጎ አውቆ ነው፡፡ የማታውቁትን ባህል እንዴት ነው የምታከብሩት?›› የሰውየው የስላቅ አነጋገር ይበልጥ አንገታችንን አሰበረን፤ ‹‹ምንም ሳትዘጋጁ መጥታችሁ ‹ባህል ለማክበር ነው› ስትሉ አታፍሩም!?!››

‹‹ይቅርታ እንግዲህ፡፡ ያው ዘመኑ ተለውጧል ብለን…›› አለ ልጁ እየተቅለሰለሰ ለመቀለድ ሞከረ፡፡

እኛ ዳኛ ፊት እንደቆመ ተከሣሽ እጃችንን ወደኋላ አድርገን ቆመናል፡፡ የልጂት ቤተሰቦች ከሳቃቸው ተመልሰው በመከፋት ዓይነት ፊታቸውን ቅጭም አድርገው እያዩን ነው፡፡ ( …ወይ ጣጣ!)

‹‹እሺ! አሁን ቁጭ በሉ ልጃችንን ለልጃችሁ ሰጥተናል!›› አሉ አዛውንቱ፤ ‹‹ዘንድሮ ልጆቹ ጨርሰው ለወጉ ሽማግሌ ባይልኩና እንደቀደመው ባህል ቢሆን ኖሮ ልጃችንን አንሰጣችሁም ነበር፡፡››

ሦስታችንም አመስግነን፣ የተመደበልን ቦታ ላይ ሄደን ቁጭ አልን፡፡ …እፎይ! ከዚህ የቅሌት ካባ ካለበሰኝ ገጠመኝ አእምሮዬ ላይ የቀረው የአዛውንቱ መራራ ንግግር ነው፤ እውነት የማናውቀውን ባህል እንዴት ማክበር ይቻለናል!?

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የጣሊያን የመከላከያ ስምምነቶችና የፖለቲካዊ ድጋፎች

በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ የመጣውን የጸጥታ ስጋት ተከትሎ፣ ጣሊያን ለባህረ...

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ”ንዋይ” የተሰኘ መተግበሪያን ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች...

የነዳጅ እጥረት አሽከርካሪዎችን ለከፋ እንግልት እየዳረገ ነው

በአዲስ አበባ እና በልዩ ልዩ የክልል ከተሞች የሚስተዋለው የነዳጅ...

ሼክ ኢብራሂም ቱፋ በኢራን ኤምባሲ በመገኘት ሀዘናቸውን ገለጹ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼክ ኢብራሂም...