
በቅርቡ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ አካሒደዋል፡፡ ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላም ፓርቲው በተወያየባቸው አጀንዳዎች ዙሪያ የዐቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ዐቢይ አሕመድም ለአባላቱ ዘለግ ያለ መልዕክት ያስተላለፉበት ቪዲዮ በብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ተላልፎ ተከታትለናል፡፡ ብልጽግና በመግለጫውም ኾነ በፕሬዝዳንቱ በኩል ለሕዝብ ሊያስተላልፋቸው የወደዳቸው መልዕክቶች ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ሕዝብ፣ ሀገርም እንደ ሀገር ካለችበት እውነታ ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ ኾኖ አግኝተነዋል፡፡ ፓርቲውም ኾኑ የፓርቲው ሊቀ መንበር ሀገር እና ሕዝብ የገቡበትን የሰላም እና የደህንነት ቅርቃር ‹‹ነጻነትን በወጉ ማስተዳደር እንዳቃተው ሕዝብ እና ሀገር››፤ ዜጎች በልቶ ለማደር በእጅጉ የቸገራቸውን የኑሮ ውድነት ባላየ እና ባልሰማ ከማለፍ አልፎ፣ ዛሬም የተስፋ ዳቦ ‹‹ግመጡ›› ለማለት የሔዱበት ርቀት እጅግ አስደንጋጭ ነው፡፡
ከአንድም ሁለት ክልሎች የሲቪል ሰርቫንቱን ደሞዝ መክፈል አቅቷቸው የመንግሥት ሰራተኛው ወደ ጉልበት ሥራ እንደተሰማራ በሚነገርበት፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ራሳቸው በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ፊት ቀርበው 26 በመቶ የምርት ዕድገት መቀነሱን፣ ማዳበሪያ መግዢያ በጀት መጥፋቱን በተናገሩ ማግሥት፤ የትምህርት ሚኒስቴር የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን መመገብ ‹‹ዳገት ኾኖብኛል›› ካለ ሳምንታት እንኳን በወጉ ባልተቆጠሩበት ሁኔታ፣ የብልጽግና ፓርቲ እና የድርጅቱ መሪ ፍጹም አንገብጋቢ ለሚባሉት የሕዝብ ጥያቄዎች ‹‹ጆሮ ዳባ›› ያለ መግለጫ እና ሌክቸር በመሥጠት ምን ግዴነታቸውን ማሳየታቸው፣ ቢያንስ እንደ ሕዝብ ‹‹መሪው እና ተመሪው ይተዋወቃሉን?›› የሚል ቀሊል ጥያቄ ለመጠየቅ ያስገድዳል፡፡
ከሁሉ በላይ ደግሞ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱን በሰበሰቡበት ንግግራቸው ‹‹ሰው ሁሉ የደገፈን መደመር ገብቶት ሳይሆን የነበረውን ጠልቶ ነው›› በማለት ከሕዝብ የደረሰባቸውን የቅቡልነት እጦት እና ከፍተኛ የድጋፍ መሸርሸር በአመራር አቅም ማነስ የመጣ መኾኑን አምኖ በመቀበል ሕዝብን በይፋ ይቅርታ ጠይቆ ቢረፍድም ነገሮችን ለማስተካከል ጥረት ከማድረግ ይልቅ ‹‹[ሕዝብ] የነበረውን ስለሚጠላ እና ፍላጎትም ስላለው፣ ምንም ሐሳብ ቢመጣ፣ አብሮ ለከፍተኛ ወጀብ ይሰለፋል›› ብለው በማናናቅ፣ ምን ያህል አሁናዊው የኢትዮጵያ ምስቅልቅል ቁብ እንደማይሰጣቸው፣ ከሕዝብ ጥቅምና ጥያቄ በተጻራሪ መጓዝንም ‹‹መንገዴ›› ብለው መያዛቸውን አስረግጧል፡፡
ፓርቲያቸው ብልጽግናም ኾነ ቁልፍ አመራሮቹ ‹‹ቁማር መብላት/መበላትን›› እንደ ትልቅ የፖለቲካ መጫወቻ ሥልት አድርገው እንደሚጠቀሙ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከዚህ ቀደም የነገሩንን እውነታ ካስታወስን ደግሞ፣ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ለማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በሰጡት ሥልጠና የወረወሯት ሌላኛዋ ኃይለ ቃል ብዙ እንድናስብ መግፍኤ የምትኾነንም ናት፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሕዝብ ‹‹ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረገ ነው›› ያለው ርዕያቸውን ሲደግፍ መቆየቱን ‹‹ያኔ የተባለው እንዲህ ነው እንዴ? እኛ የመሠለን እኮ እንዲህ ነበረ? ሐሳቡ ተቀየረ እንዴ? የሚል ዲሉዥን ተፈጠረ እንጂ ሐሳባችን ተቀይሮ አይደለም፡፡ [ችግሩ] አንተ የፈታህበት መንገድ እና የሐሳቡ ጥራት ደረጃ አለመገናኘቱ ነው›› በማለት ለደጋፊያቸው የተለመደውን የ‹‹ቁማር›› ፖለቲካ መበላቱን መርዶ አርድተዋል፡፡
በአጠቃላይ ከቀናቶች በፊት ብልጽግና ፓርቲ በሥራ አስፈጻሚም ኾነ በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ያደረጋቸው ውይይቶችም ኾኑ፣ እርሱን ተከትሎ በፓርቲውም ኾነ በፕሬዝዳንቱ በኩል የተሰጡት መግለጫዎች፣ ሕዝብ በተለያየ መንገድ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎችም ኾነ የገዛ ሚኒስትሮቻቸው ሳይቀር በዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸሞቻቸው ዙሪያ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ላቀረቧቸው ሪፖርቶች ዋጋ የማይሰጥ፣ ራስን ብቻ እያደመጡ በደንታ ቢስነት ‹‹ወደፊት›› መጓዝን የአመራር ፍኖት አድርጎ የወሰደ አካሔድ ነውና ‹‹ሕዝብ ከዚህ በላይ በመንግሥት ተስፋ ለመቁረጥ ምን ይጠብቃል?›› የሚለውን ጥያቄ ጎልቶ አውጥቶታል የሚል ዕምነት አሳድሮብናል፡፡