መረጃን ለምግብ ያዋለችው ሳራ መንክር

Date:

ሳራ መንክር ኢትዮጵያ ተወልዳ አብዛኛውን ዕድሜዋን በውጭ ሀገራት አሳልፋለች፡፡ “ግሮ ኢንተለጀንስ” የተሰኘ መቀመጫውን ኒውዮርክና ናይሮቢ ያደረገን ዓለም አቀፍ ተቋም መሥርታ በበላይነት እያስተዳደረች የምትገኘው ሳራ፣ የምግብ አቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን እንቅልፍ የሚነሳት ሴት ናት፡፡ በኢኮኖሚክስና በአፍሪካ ጥናት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከማውንት ሆሊኦክ ኮሌጅ ያገኘች ሲሆን፣ ለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስን ተቀላቅላ ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪዋን በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን አግኝታለች፡፡

ሳራ መንክር በዋናነት ከምታስተዳድረው ግሮ ኢንተለጀንስ በተጨማሪ፣ የማንዴላ ኢንስቲትዩት ፎር ዴቨሎፕመንት “ባላደራ” (trustee) በመሆን ታገለግላለች፡፡ እስከ አሁን ባበረከተችው አስተዋጽኦም የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም የወጣት መሪዎች ዝርዝር ውስጥ ተካታለች፡፡

በግል ዘርፉ የሥራ ፈጣሪ ሆና ፍላጎቷን ማሳካት ከመጀመሯ በፊት በኒውዮርክ የዋል ስትሪት የሸቀጦች መሻሻጫ ውስጥ ትሰራ ነበር፡፡ በዝነኛው የሞርጋን ስታንሊ ግሩፕ ውስጥ ያለ የሸቀጦች ቡድን ምክትል ፕሬዝዳንት ሆና ስታገለግል ነበር፡፡ በግብይት መስክ ውስጥ በነበራት ቆይታ የእርሻ መሬት ላይ የሚፈሱ መዋዕለ ንዋዮች ይስቧት ስለነበር፣ ሥራዋን እርግፍ አድርጋ የራሷን ተቋም ለመመሥረት ተነሳሳች፡፡ የዋል ስትሪት እውቀቷን ይዛ በመረጃ ትንተና እና አሰባሰብ ላይ ለመሥራት አትራፊነትን የሚሰብከውን የንግድ አስተሳሰብ ትታ ወደ በጎ አድራጎቱ አዘንብላለች፡፡

በየጊዜው እየተባባሰ የሚመጣው የምግብ እጥረት እያሳሰባት ጥናት ማድረግ ጀመረች፡፡ ከዓለም የምግብ አቅርቦት አኳያ አፍሪካን መርጣ አህጉሩ የዓለማችንን የምግብ ፍላጎት መጨመር እንዴት መቀነስ ይቻለዋል? ስትል ምርምር ማድረግ ቀጠለች፡፡ ነገሮች እንደተለመደው ከቀጠሉ በፈረንጆቹ 2030 ዓ.ም ዓለማችን ገጥሟት የማያውቅ የምግብ እጥረት ይከሰታል ብላ በመረጃ አስደግፋ ተነበየች፡፡ በትንበያዋ መሠረት፣ እጥረቱ ከባለፈው የምጣኔ ሀብት ውድቀት (financial crisis) የባሰ ችግር ያስከትላል፡፡ በጥናቷም፣ ከ214 ትሪሊዮን በላይ የካሎሪ ዕጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል ጠቁማለች፡፡ ይህ የቁልቁለት ጉዞ ያሳሰባት ሳራ ዝም ብሎ ማየቱ ስላላስቻላት አፍሪካ እየተመላለሰች ይጠቅማል ብላ ያሰበችውን ተቋም መሥርታለች፡፡ በፈረንጆቹ 2014 ኬንያ በመግባት “ግሮ ኢንተለጀንስ” የተሰኘውን ድርጅት መሥርታ እስካሁን እያስተዳደረችው ትገኛለች፡፡

ግሮ ኢንተለጀንስ በአሜሪካ ኒውዮርክ ቢሮ ያለው ሲሆን፣ ዋና ትኩረቱ በግብርና መስክ ያሉ መረጃዎችን በማጠናከር ለፈላጊዎች ይፋ ማድረግ ነው፡፡ የዓለማችንን የምግብ ገበያ መረጃ በአንድ ቋት በማስገባት ነጋዴዎችና ሕብረተሰቡ፣ አምራች ኩባንያዎችም በቀላሉ መረጃው ኖሯቸው በአነስተኛ ወጪ ያለብክነት ምርት እንዲለዋወጡ የሚያስችል ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የሜክሲኮ ገበሬ የሚያመርተውን አቦካዶ ወይም ቡና ነጋዴዎች በስንት መግዛት እንደሚችሉና፣ እሱም በተራው ሌሎች በስንት እንደሚሸጡም ሆነ እንደሚገዙ የሚያውቅበት ነው፡፡

ይህ ዐይነት መረጃ የእህል ዋጋን ለመተንበይ ከማገዙ ባሻገር መረጃዎችን አጠራቅሞ ባስፈለገ መልክ ጥቅም ላይ ለማዋል ይረዳል፡፡ አርቴፊሻል ቴክኖሎጂን በመጠቀምና ሶፍትዌሮችን አገልግሎት ላይ በማዋል በግብርና መስክ ያለውን የመረጃ ፍላጎት በሟሟላት ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ሳራ በእጅጉ ታምናለች፡፡ የዓለም የአየር ጠባይንና የአየር ንብረትን መረጃ ከግብርና አሠራሮች ጋር በማቀናጀት ለአምራቾችም ሆነ ለተጠቃሚዎች ትንበያም ሆነ ጥቅም፣ በቀጥታ የሚያገለግል መረጃን የሚያሰራጭ ተቋምን ሳራ መንክር ትመራለች፡፡ ለማንኛውም ዐይነት ተጠቃሚ ምቹ የሆነው ይህ በፎቶ መልክ የሚገኝን የሳተላይት መረጃን (ኢትዮጵያ እንደላከቻት የመጀመሪያዋን ሳተላይት ዐይነት) በመጠቀም የሚሰላ ስሌትን በመመርኮዝ ይፋ ያደርጋል፡፡ ተቋሙ ባዘጋጀው ሶፍትዌር አማካኝነት በየቀኑ የሚታይ የአየር መረጃን በመውሰድ በቀን ውስጥ እስከ 1 ሺህ ሞዴሎችን በማውጣት ለተጠቃሚዎች ያቀርባል፡፡

ሳራ በግሮ ኢንተለጀንስ ባለሙያዎች በመታገዝ፣ የተፈጥሮ አደጋዎች በምግብ ምርትና አቅርቦት ላይ የሚያስከትሉትን ተጽዕኖ እያጠናች በመመዘን መንግሥታትም ኾኑ ዓለም አቀፍ ተቋሞች እንዲሁም አምራች ኩባንያዎች እንዲጠቀሙበት ታቀርባለች፡፡ በተለይ ድርቅን የመሳሰለ ድንገት የማይከሰት የተፈጥሮ አደጋ መንስኤንና ተጽዕኖን ለይቶ በማጥናት፣ በዓለም አቀፍ የምግብ ገበያው አቅርቦት ላይ አስቀድሞ መደረግ ያለበትን ይጠቁማል፡፡ ከእህል ገበያ ጋር በተያያዘም የምትሰጠው ትንበያ ለነጋዴዎች ሆነ ለኢንቨስተሮች ከፍተኛ ግብዓት በመሆኑ ትልቅ ምሥጋናን አግኝታለች፡፡ ከምሥጋናም አልፎ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የገንዘብ ድጋፍ ሥራዋን የሚጠቀሙና የሚገለገሉበት ይሠጡዋታል፡፡ በተለይ፣ በአሜሪካ ያሉ የምግብ አምራች ኩባንያዎች በግልም ሆነ በማህበር በተደጋጋሚ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ሠሞኑን ዜና የሆነውና ባለፈው ሳምንት ዕትማችን ላይ የተዘገበው የ85 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አንዱ ነው፡፡ ይህን ገንዘብ ባለሀብቶቹ ኢንቨስት ያደረጉት በ7 ዓመት ቆይታዋ ሳራ የደረሰችበትን ስኬት ተመልክተው ነው፡፡

ኩባንያዎቹ፣ የሳራ መንክር ኩባንያ የሚያወጣውን መረጃ ተጠቅመው ምርታቸውን የትና በምን ያህል ገንዘብ መሸጥ እንዳለባቸው ከማወቃቸው ባሻገር፣ ለቀጣይ ተፈላጊ የሚሆንን እህል ከተሻለ ማምረቻ፣ ቦታና መንገድ ጋር ለማወቅ ይጠቅማቸዋል፡፡ ግብዓታቸውን ለመግዛት የሚፈልጉ የግብርና ምርት ተጠቃሚ ፋብሪካዎችም በተመሳሳይ አቅደው ለመሥራትና የእህል ዋጋ እንዳይዋዥቅ ለማድረግ ያስችላቸዋል፡፡

እንደ ሳራ እምነት ይህ የመረጃ ቋት ከግለሰብ ተጠቃሚዎች ይልቅ መንግሥትን የመርዳት አቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡ ፖሊሲ አውጪዎች አስቀድመው ስለመጪው ጊዜ እንዲዘጋጁና ከአደጋ ሕዝባቸውን እንዲጠብቁ የሚያስችል የተደራጀን መረጃ ያገኛሉ፡፡ ከመንግሥታት ባሻገር የኢንሹራንስ መድን ሰጪዎች የአየር ሁኔታውን ከግምት ያስገባ ትንበያን መሠረት በማድረግ በተለይ በድሃ ሀገር ሕይወታቸው በግብርና ላይ ለተመሠረተ አርሶ አደሮች ዋስትና መስጠት እንደሚችሉ በተግባር የታየ ጥቅም አስገኝቷል፡፡

እንደ ሳራ ግምት፣ እንደ ግሮ ዐይነት ተቋሞች ከባለሀብትና መንግሥታት ጋር አብረው ካልሰሩ በ10 ዓመት ውስጥ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ይከሰታል፡፡ ይህ ትንቢያዋን በ2017 ይፋ ያደረገች ሲሆን፣ በቴድቶክ ላይ የነበረው ቪዲዮ ከ1.5 ሚሊየን በላይ ተመልካች አግኝቷል፡፡ ከዚህ ንግግሯ በኋላ መወያያ የነበረችው ሳራ፣ የሄነሪ ሲ ጋርዲነር ግሎባል ፉድ ሲስተም አስተማሪ መሆን ችላለች፡፡ በሥራዋ ዝናን በማትረፏም ኒውዮርክ ታይምስን በመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ ቀርባለች፡፡ ሥራዋንም ሮክ ፌለር ፋውንዴሽንን በመሳሰሉ ተቋሞች ለማቅረብ በቅታለች፡፡ በምትሰራበት መስክ አንቱታን በአጭር ዓመታት በማትረፏ በርካታ ከግብርናና ከኢኮኖሚ ጋር የተገናኙ ተቋሞች ባለአደራ የበላይ ጠባቂ ሆና እያገለገለች ትገኛለች፡፡ ዘ አስፔን ኢንስቲቲዩት ውስጥ የአፍሪካ ሊደርሺፕ ኢንሺየቲቭ አባል በመሆንም አፍሪካውያንን ለማብቃት እየሰራች ትገኛለች፡፡ በተለምዶ “ራስን በምግብ ለመቻል” የሚባለውን ጥቅስ በተግባር ለማዋል ለሀገራት ብቻ ሳይሆን ለዓለም እየጣረች ነው፡፡ የምግብ እጥረት እንዳይከሰት ከማድረግ በተጨማሪ፣ እህል አምራች ኩባንያዎችና ነጋዴዎች በዘርፉ ላይ ትልቅ ለውጥ እንዲያመጡ መረጃዎቿ ግብአት እንዲሆኑ እየጣረች ትገኛለች፡፡ በአንድ ወቅትም በአፍሪካ ከ1 ትሪሊየን ዶላር በላይ በግብርና መስክ ሠፊ እድሎች አሉ ተብሎ ነበር፡፡ እነዚህን እድሎች በመጠቀም የምግብ ፍላጎት ከምርት አንፃር ዝቅተኛ እንዲሆንና የእህል ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆን የማድረግ ሕልሟን ለማሳካት እየተጣጣረች ትገኛለች፡፡ አሁን ካለው ባይሻሻል እንኳን፣ ለወደፊት ተባብሶ ብዙዎች በምግብ እጥረት እንዳይጎዱና በሰዎች መካከል አላስፈላጊ ጦርነት በምግብ እጥረት ምክንያት እንዳይከሰት የሳራ ተግባር ይከላከላል ተብሏል፡፡ እኛም እንደ ሀገር መሠል መረጃዎችን በመጠቀም፣ ምን ዓይነት እህልን የት አካባቢ በምን መንገድና ጊዜ ብናመርት ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን እንችላለን፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...