መሲሁን ያጣው አየር መንገዳችን! ሳሙኤል የተሻወርቅ

Date:

ለውጥ ስንል እድገት ለማለት ይመስለኛል። ለውጥ ከሌለ እድገት አይታሰብም። የሰው ሳይሆን የአሰራር ለውጥ። የፖሊሲ ለውጥ፣ የአስተሳሰብ ለውጥ። ወንበሩን ብቻ ይዘህ እንደ ሰልጣኝ ሰራዊት ባለህበት እየተራመድክ ተለወጫለሁ ካልከኝ ግን ሕዝብን ሳይሆን ራስህን እያሞኘህ መሆኑን አትዘንጋ። ወትሮም “ብዙ እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን” ከምንልበት አስፈሪ ዘመን ሻገር ብለናልና በጽልመት የሚከወኑ ብልሹ ተግባራት ላይ ጥቂትም ብትሆን የብርሃን ፍንጣቂ ማኖሩ ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ ያመዝናል።

ጋን በጠጠር ይደገፋልና፣ በ “አዲሱ የአየር መንገድ ማኔጅመንት” ዙርያ እየተከወኑ ያሉ እጅግ አሳሳቢ ጉዳዮችን ችላ ማለቱን አልፈቀድኩም። የቀድሞ አመራሩን ኮቴ ባይከተልም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት ስምንት ወራት የመጣበት ጎዳና በእጅጉ የሚያስፈራ ሆኗል። ጓዳውን የጎበኙ የአቪየሽን ኤክስፐርቶች የአቶ መስፍን ጣሰው ማኔጅመንት ፍኖተ-ካርታ ከአይተ ተወልደ ገ/ማርያም የተቀዳ ነው ለማለት እሰኪደፍሩ ድረስ መሆኑ ደግሞ ዙሩን ሳያከረዉ አልቀረም።

አነስተኛና ጥቃቅኑን ጉድፍ ለግዜዉ በማቀዝቀዣ ውስጥ እናኑረዉና አስቸኳይ ትኩረትን ከሚሹ ግዙፍ ችግሮች ጥቂቶቹን ላንሳ። ለማሳያ ይሆኑ ዘንድም በመረጃ እና በማስረጃ የተደገፉ ሦስቱን አደጋዎች ፀሐይ ላይ ሳሰጣ፣ እናንተም እጃችሁን ባፋችሁ ላይ ለመጫን ተዘጋጁ።

በቦይንግ የታፈነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን!

ቦሌ አየር ማረፊያ ላይ እንደ ጣልያኑ “ሲሲሊ” በአፈና ለ14 ቀናት ታግቶ በሰነበተዉ “ድሪም ላይነር” ጉድ ልጀምር።

እንዲህ ነው የሆነው። አውሮፕላኑ እ.ኤ.አ ሕዳር 24/2022 ባጋጠመው ብልሽት ምክንያት በጥገና መስጫ ጋራጅ ዉስጥ ከቆመበት ዕለት አንስቶ ሁለት ሳምንት እንደ ጅብራ ተገትሮ ሰንብቷል። 

ይህ ድሪም ላይነር መበላሸቱ የታወቀው፣ የኮምፒዩተር ስክሪኑ “በመጨረሻው የአውሮፕላኑ ክፍል ላይ አደጋ ስላለ መብረር አይችልም” የሚል መልእክት በማሳየቱ ነበር፡፡

ችግሩን ለመፍታት ቴክኒሻኖቹ ቀን ከሌሊት እየሰሩ ነው። በሁሉም አቅጣጫ ወጡ፣ ወረዱ። ግን ትርፉ ድካም ብቻ ነበር። በጣም ውድ የተባሉ ተለዋጭ እቃዎች ቢቀየሩለትም፣ ምልክቱ ፍንክች አልል አለ። የቦይንግ ኩባንያን ወክለው አዲስ አበባ የተቀመጡ ሁለት አሜሪካውያን ቴክኒሻኖች እንዲጠግኑት ለማድረግ ተሞከረ። እነሱም አልቻሉትም። በብልሽቱ ምክንያት የአውሮፕላኑ የቀን ገቢ በመቋረጡ ኪሳራው እየናረ መምጣቱም ሌላ ሐሳብ ነው። እንደሚታወቀው፣ አብዛኞቹ አውሮፕላኖች በባንክ እዳ የተገዙ በመሆናቸው፣ እንኳንና ቆመው እየበረሩም እንኳ ወለዳቸው የመርግ ያህል የከበዱ ናቸው።

በመጨረሻ ግን አንድ ሐሳብ ብልጭ አለና የቦይንግ ቴክኒሻኖች ከአሜሪካ እንዲመጡ ተደረገ፡፡ ባለሙያዎች ታህሳስ 7/2022 (እ.ኤ.አ.) ጋራጅ ወደ ቆመው አውሮፕላን አቅንተው ፓይለቶቹ በሚቀመጡበት የበረራ መቆጣጠሪያ (Cockpit) ውስጥ ገቡ። ምሥጢራዊዉ ድራማ የጀመረውም ያለቀውም እዚህ ላይ በዚያች ቅፅበት ነበር።

ባለሙያዎች ከበረራ መቆጣጠሪያ ክፍል ከገቡ በኋላ፤ ‹መረበሽ አንፈልግም› በሚል ሰበብ የአየር መንገዱ ቴክኒሻኖችን እና ኃላፊዎች በሙሉ አስውጥው በሩን ዘጉት፡፡ እናም የሚበራውን የአደጋ ምልክት አጥፍተው አውሮፕላኑን በቅፅበት ፈወሱት።

ኦፐሬሽኑ የወሰደባቸው ግዜ 15 ደቂቃ ብቻ ነበር። የድራማውን ፍፃሜ አጓጊ የሚያደረገው፣ አሜሪካውያኑ ቴክኒሻኖች የተፈጠረውን ችግር እና የሰጡትን መፍትሔ ለመናገር ፍቃደኛ ያለመሆናቸው ብቻ አይደለም። ጥገናውን እንደጨረሱ በማታው በረራ ወደ መጡበት መንካታቸውም እንጂ።

አውሮፕላኑን የሸጠው የቦይንግ ኩባንያ ብልሽት ሲያጋጥም የመጠገን ግዴታ አለበት። አውሮፕላኑ ለሳምንታት ያለሥራ የቆመበትንና ለመለዋወጫ ዕቃ የወጣውን ወጪ የመክፈልም ግዴታ በውሉ ላይ ተቀምጧል።

‹ዐዲሱ ማኔጅመንት፣ ቦይንግን ከስሶ ኪሳራውን እንዲሸፍን ያደርጋል ወይስ በዝምታ ያልፈዋል?› የሚለዉን ጥያቄ ለነሱ እንተው። ምክንያቱም የዚህ ጉዳይ እዳው ገብስ ነው። ዋናው ችግር ይህ አይደለም። የችግሩም ሆነ የመፍትሔው ምሥጢር በሁለቱ ባእዳን ላይ ብቻ በመቅረቱ፣ ይህ ችግር ዳግም ሊፈጠር የማይችልበት አንዳች ዋስትና የለም። ይህ በእጅጉ ያሳስባል። ምክንያቱም እንደ ዘጠና ደቂቃ በኢንተቤ ሚሽኑን የፈጸሙት የቦይንግ ባለሙያዎች በሽታዉንም ሆነ መድኃኒቱን ከእኛ ከባለቤቶቹ  ደብቀውታል። ይህ የሆነው ደግሞ በማነጅመንቱ ድክመት መሆኑን ለመረዳት ኤክስፐርት መሆንን አይጠይቅም። ታዲያ ጉዳዩ በደንብ እስኪጣራ ድረስ በድሪም ላይን ቢያንስ ከፍተኛ የመንግሥት ሓላፊዎች በቦይንግ 787 ባይበሩ ይመከራል። ያንኪዎቹ በውድ ዋጋ የሸጡትን አውሮፕላን በሪሞት ኮንትሮል መቆጣጠር ከታንጎ ዳንስ የሚቀልላቸው መሆኑን አንዘንጋ።

ከወደ ግሪክ የተሰማው የሚያስቅ ሳይሆን የሚያሳቅቅ ታሪክ ደግሞ አንገት የሚያስደፋ ብቻ አይደለም። ነገሩን በደንብ ለሚረዳው ይህን ለአህጉሪቱ ኩራት የሆነ ተቋም ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥልም ነው።

በግሪክ አየር ኃይል የተጠለፈው የኢትዮጵያ አየርመንገድ አውሮፕላን!

ባሳለፍነው ወር በግሪክ አየር ኃይል የተጠለፈው አውሮፕላናችን ጉዳይ ከመዘርዘሬ በፊት በጥቂቱ ስለ አቪየሽን አሰራር መጥቀሱ ለግንዛቤ ይረዳ ይሆናል።

በአቪየሽን ደንብ መሠረት ማንኛውም አውሮፕላን የሌላ አገር የአየር ክልል ውስጥ ከመግባቱ 20 ደቂቃ በፊት የአየር ክልሉ (Air space) ጣብያውን በሬዲዮ ማነጋገር ግዴታ አለበት።

ይህ ካልሆነ ደግሞ በአውሮፕላኑ ላይ የሚገጠም Datalink በሚባል ቴክኖሎጂ በአየር ላይ ያለውን አውሮፕላን አብራሪዎችን ምድር ላይ ካሉት Air space ተቆጣጣሪዎች በሳተላይት መልእክት ማሳወቅ አለባቸው፡፡

በነገራችን ላይ በአውሮፓ 17000 (ዐሥራ ሰባት ሺህ) አካባቢ የስፔስ ኮንትሮል ጣቢያዎች ሲኖሩ እነኚህን ጣቢያዎች የሚመራው የአውሮፓ Air space ማእከል ደግሞ በቤልጄም ዋና ከተማ ብራስልስ ይገኛል፡፡

ይህ ጣቢያ በጣም ዘመናዊና ውስብስብ ያልሆነው Datalink ሲስተም ይጠቀማል። አውሮፕላኖች ከብራስልስ Air space ሴንተር ጋር የበረራውን መስመርና የአውሮፕላኑን ሙሉ ኢንፎርሜሽን፤ የመነሻ ሰዓታቸውን ደቂቃ ተለዋውጠው ነው በረራቸውን ለመጀመር የሚንደረደሩት። አውሮፕላኑ መንሳፈፍ ሲጀምር በሬዲዮ ንግግር ባያደርግም፤ Datalink ሲስተም መልእክት መላክና ግንኙነቱን መፈፀም ይችላል፡፡ አውሮፕላኑ የአገሪቱን ክልል ጨርሶ ሊወጣ ሲልም ፓይለቶቹ የአየር ጣቢውን ተቆጣጣሪ ማሳወቅ አለባቸው።

አብራሪው በበረራ ሰዓት አደጋ ከደረሰበት በአየር ለሚያልፍበት ጣብያ በተለየ ኮድ ማሳወቂያ አለው። አውሮፕላኑ ከተጠለፈም አንድ ኮድ ይጫናል።

በቅድሚያ የማስነብበው እ.ኤ.አ. ጥቅምት 15/2022 ከቤልጄሟ ሌጅ (Liege) ከተማ ወደ አዲስ አበባ እየበረረ በነበረ ET-3717 ቦይንግ 767-300 አውሮፕላን ላይ የተፈጠረ ክስተት በመሆኑ፣ በእዝነ-ልቦናችሁ ሠላሳ ሺህ ጫማ አብራችሁኝ ትበሩ ዘንድ እጠይቃለሁ፡፡

“ክቡራትና ክቡራን መንገደኞቻችን የመቀመጫ ቀበቷችሁን ማሰራችሁን እንድታረጋግጡ ትመከራላችሁ፡፡” ሲል ድራማዊ በረራዉን ይጀምራል። ኮሜዲ ሳይሆን ትራጀዲ።

…አሁን አውሮፕላኑ ከባዱን የአውሮፓ ዳመና እየሰነጠቀ መክነፍ ጀመረ። ከዚያም ፍጥነቱን እየጨመረ መጣና፣ የክሮሺያ፣ ቦስኒያ፣ ሞንቴኔግሮ እና አልባኒያን የአየር ክልል ማለፍ ቻለ።

ከጥቂት ሰኮንዶች በኋላ ግን አንድ ያልተለመደ ክስተት ተፈጠረ። የአራቱም አገራት የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ከፓይለቶቹ ጋር ለመገናኘት ላደረጉት ጥረት አንዳችም ምላሽ ሊያገኙ አልቻሉም። ግን ተስፋ ሳይቆርጡ ሙከራቸውን እንደቀጠሉ ነው። 

‹ሃሎ፣ ሃሎ ካፒቴን…›

ከአብራሪው አቅጣጫ ግን ወፍ የለም፡፡

አዉሮፕላናችን ልሳኑ እንደተዘጋ የግሪክ አየር ክልል ውሰጥ እንደ ጆባ ምስክር ዘዉ ብሎ ገባ። እዚያ ከገባ በኋላም፣ ለአየር ክልል ተቆጣጣሪዎች ጥሪ ”መስሚያዬ ጥጥ” ብሏል። አፉ እንደተለጎመ የአቴንስ ሰማይ ሰንጥቆ የግብጽ ድንበር ላይ ለመደረሰ ሚዲትራሊያን ለማቋረጥ ግስጋሴውን ቀጠለ፡፡

በነገሩ ግራ የተጋቡት የተለያዩ ዓለም አቀፍ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችም ከአብራሪው ጋር ግንኙነት ለማድረግ ከመሞከር አልቦዘኑም።

ከዚህ በኋላ ነበር የአውሮፓው Air space ጣብያው ለግሪክ አየር ጣቢያ ያሳወቀው። አውሮፕላኑ በግሪክ አየር ክልል የመጨረሻው ጥሪ ቢያደረግለት መልስ ሲጠፋ ወዳልተፈለገ እርምጃ መግባቱ ግድ ሆነ። እናም ለግሪኩ አየር ኃይል ለHellenic Air Force ዋና አዛዥ ሌ/ጀ Themistoklis Bourolis አጭር ማብራሪያ ተደረገላቸው፡፡

ልብ በሉ ይህ ጉዳይ ኋላ ላይ ብዙ ውዝግብ የሚያስነሳ መሆኑ ይታወቃል። አዛውንቱ ጀነራል ለአፍታ ካሰቡበት በኋላ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ምናልባት በአሸባሪዎች ተጠልፎ ሊሆን እንደሚችል ገመቱ። ለመፍትሄው ግን ሁለት አማራጭ ብቻ ነበራቸው። አደጋ ከማድረሱ በፊት አውሮፕላኑ ተገድዶ ወደ መሬት እንዲያርፍ ማድረግ። ይህ ካልሆነ ግን በሜዲትራኒያን ባሕር ላይ የሚበተንበትን መራር ጽዋ እንዲጎነጭ ማድረግን ወሰኑ፡፡

ለግዳጅ ተዘጋጅተው ይጠብቁ የነበሩት “F-16” ተዋጊ ጄቶች በቅጽበት በተራራማዋ የግሪክ Kythira ደሴት ላይ ደርሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላንን መሃል በማስገባት እንደ ሙሽራ አጀቡት። በጦር አውሮፕላን መከበባቸውን ያወቁት አብራሪዎችም፣ በአስደናቂ ፍጥነት ለግሪኩ የአየር ክልል ተቆጣጣሪ የመገናኛ ሬዲዮ መልስ በመስጠት ከተቃጣባቸው አደገኛ ጥቃት ሊተርፉ ችለዋል።

እ.ኤ.አ 2018 በጀርመን ተፈጥሮ የነበረው መሰል ኹነት ለዚህ ድክመት ዐይነተኛ አስረጂ ይመስለኛል፡፡ በወቅቱ፣ የቀድሞዋ ቻንስለር አንጄሊካ ሜርክል በጂ-20 አገራት ስብሰባ ለመሳተፍ ወደ አርጀንቲናዋ ቦይነስ አይረስ ለመሄድ በረራ ጀመሩ። ገና ሆላንድ ድንበር አካባቢ ሲደርሱ ካፒቴኑ የመገናኛ ሬዲዮ መበላሸቱን በማወቁ፣ ወደ ኮለን አውሮፕላን ማረፍያ ለመመለስ ተገድዷል፡፡

ይህን በረራ የመራው ኅላፊ ‹የጀርመን አየር ኃይል ደባ አለበት› የሚል ጥርጣሬውን በመግለጹ ምክንያት ትልቅ ትርምስ ፈጥሮ እንደነበር አስታውሳለሁ። ክስተቱ የጀርመንንም ሆነ የአየር ኃይሉን ገጽታ ያበላሸና ሃፍረት ያከናነበም ነበር።

የኛዎቹ ግን አምስት አገራትን አቋርጠው እስኪያልፉ ድረስ ያወቁት ነገር ያለመኖሩን ነዉ የምነግራችሁ። የግሪክ አየር ኃይል ምስጋና ይግባዉና አውሮፕላናችን የግብጽን አየር ክልል ጥሶ ቢገባ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ መገመቱ ቀላል ነው፡፡

በመገናኛ ብዙኃን ያልተዘገበው ይህ ክስተት በአዲሱ አመራር ላይ በርካታ ጥያቄ መጫሩ አልቀረም። ይህ ክስተት በምን ምክንያት ነው የተፈጠረው? ስህተቱስ የማን ነው? ካፒቴኖቹ በተዋጊ ጄቶች መከበባቸውን ባወቁ ፍጥነት እንዴት የመገናኛ ሬዲዮው ሊሠራ ቻለ? ቸልተኝነት ነው ወይንስ  የብቃት ማነስ? የተቋሙን ስም ለማጠልሸት የተጠነሰሰ ሴራ ስለመሆኑስ ምን ዐይነት ምርመራ ተደርጎ ይሆን?

አንድ አውሮፕላን ያለ ሬዲዮ ንግግር አንድ አገርን አቋርጦ ካለፈ፣ የተዋጊ ሚግ እንዲከተለው፤ ካስፈለገም እርምጃ እንዲወሰድበት፤ የተወሰነው ከአሜሪካኑ ሴፕቴምበር 11 ጥቃት በኋላ ነበር፡፡

በዚህ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ድርጊት የሚቀጣው በአውሮፓው  Air space ብቻ አያቆምም፤ ለግሪክ  አየር ኃይል “F-16” ተዋጊ ጄቶች ወጪና ትርፍ፤ የሚከፈለውን በዶላር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግዴታው ነው፡፡

አወዛጋቢዉና ቅጥ ያጣው የአየር መንገዱ ቅጥር!

“Fiona Cuper” ትባላለች፡፡ ትውልድና እድገቷ አየርላንድ ቢሆንም፣ ዜግነቷ እንግሊዛዊ ነው፡፡ የትምህርት ዝግጅቷ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ከመሆኑ በቀር፤ በሕይወት ዘመኗ በበረራ ካቢን ክሩ ሠርታ አለማወቋን የገዛ ማስረጃዎቿ ጮኸው ይናገራሉ፡፡ ወይዘሮዋ አዲስ አበባን የረገጠችው እ.ኤ.አ ጥቅምት 4/2021 ከእንግሊዙ ማንቸስተር ከተማ በድንገት ተነስታ ነው፡፡ ለተጠቀሰው የሥራ መደብ ዳይሬክተርነት እና ለቫይስ ፕሬዚዳንቱ ምክትልነት የተቀጠረችው፣ በቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ በነበሩት አቶ ተወልደ እና አቶ ሚካኤል ውሳኔ ነበር፡፡

ልብ በሉ። ተቋሙ ያለ ምንም መስፈርት ለፈረንጇ በሰጠው የኃላፊነት ቦታ ላይ የማስተርስ ድግሪን ጭነዉ እስከ 30 ዐመት በክሩነት፣ በአስተማሪነት፣ በማኔጅመንት አባልነት… ያገለገሉ የሀገሬው ሠራተኞች ነበሩ። አሁንም አሉ። በሀገሪቱ ሕግ መሠረት አንድ ተቋም የውጭ ዜጎችን ከመቅጠሩ በፊት የሥራ ማስታወቂያ አውጥቶ የሥራ ዘርፉን የሚሸፍኑ ዜጎች ሲጠፉ ብቻ ነው።

በተወልደ ዘመን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሴትየዋን ቅጥር ‹ፍቃድ አልሰጥም› በሚል ውድቅ አድርጎት ነበር። ለዚህም ምክንያቱ አሮጊትዋ በምትመደብበት ቦታ በሙያና በልምድ የተካኑ አያሌ ኢትዮጵያውያን በመኖራቸው ብቻ አልነበረም። ሴትየዋ የትምህርት ብቃቱም ሆነ ሙያው የሌላት በመሆኑም ጭምር እንጂ። የተወልደ መንግሥት ግን ይህን መመርያ ረግጦ: ከሲቪል አቬሽን የድጋፍ ደብዳቤ አጽፎላት የሥራና የመኖሪያ ፈቃድ እንዲሰጣት አደረገ። እርግጥ ነው። አየርላንድ ከጫካ ጀምሮ የሕወሓት የጡት አባትነቷ ይታወቃል፡፡ ሌላው ቢቀር የሰሜኑን ጦርነትን ተከትሎ በተባበሩት መንግሥታት መድረኮች፣ ከ“ፍየሉ በላይ” በመጮኹ ረገድ አየርላንድን የሚስተካከል አልነበረም፡፡ በቅርቡ ኢትዮጵያ ከአየርላንድ ኤምባሲ አራቱን ዲፕሎማት ስታባርር፤ ወደ መቶ ከሚጠጉ አይሪሾች ደግሞ፣ በፍቃዳቸው ወጥተዋል፡፡ ሥራቸውን ስለሚያውቁ።

የፍዬና ኩፐር ቅንጡ ሕይወት ግን በስካይ-ላይት ሆቴል፣ ቀጥሏል፡፡ ያውም በነጻ። የወር ደሞዝዋ ከአንድ ወረዳ በጀት እንደሚስተካከል በአፍ ከምናገር ይልቅ እነሆ ማስረጃውን ማሳየቱን መረጥኩ። መቼም፣ እንዲህ ዐይነቷን ወይዘሮ በስለላ ላይ ወይም ለከፍተኛ ሙስና ሽፋን ሰጪ ልትሆን ትችላለች ብሎ አለመጠርጠር የበዛ የዋህነት ይሆናል። አገር በአንድ ሰው ሊለማ ወይም ሊጠፋ የመቻሉ አይቀሬነት በታሪካዊ ክስተቶች የተረጋገጠ ነውና፡፡ የአንደኛው የዐለም ጦርነት የወዲያውኑ ምክንያት የሃንጋሬው ልዑል ፍራንዝ ፈርዲናድ መገድል መሆኑ አይዘነጋም፡፡ የምድራችን ዘግናኙ የዘር ማጥፋት ወንጀል የተፈጸመውም የሩዋንዳውን ፕሬዚዳንት ግድያ ተከትሎ ነበር፡፡ በአጭሩ፣ እያወራሁ ያለሁት ስለአንዲት ለምንኩስና የተጠጋች ወይዘሮ ከፍተኛ ደሞዝ ሳይሆን፤ ስለ አገር ህልውና ነው፡፡

አቶ ተወልደ የሰጣት የሥራ ኮንትራት ሲያልቅ፣ አቶ መስፍን ኮንትራቷን ማራዘሙ ሲሰማ ብዙዎችን ማስደንገጡ እና ማስቆጨቱ አልቀረም። የበረራ አስተናጋጆች በሙሉ እንደ ክፉ የእንጀራ እናት የሚያዩዋት ሴትዮ እደሜዋን አቶ መስፍን ቀጠለ።

ጉድ በል ጎንደር የሚያስብለው ደግሞ የወር ደሞዝዋ ነዉ። በወር አራት መቶ ሺሕ ሠላሳ አራት ብር ከሰባ ሦስት ሳንቲም (411,034.73) እንዲከፈላት በሚያደርግ ውል በአቶ መስፍን ጣሰው ፊርማ ፀድቆ ስራዋን መቀጠሏን በጆሮ ሳይሆን በአይን ስመለከት የለውጡ ተስፋ ውሀ በላው እንዴ? ብዬ ለመጠየቅም ዳዳሁ።

እነሆ እንኳን ከዘመነ-ተወልደ ወደ ዘመነ መስፍን ተሻገራችሁ ብለን የደስታ መልእክቱን ሳንጨርስ የክፉውን ዘመን ቅርስ መውረስ ጀምረናል እላችኋለሁ።

(የሰነድ ማስረጃውን ከታች ተመልከቱት፡-)

ከሀገሪቱ የሥራ እና አሰሪ ሕግ ውጪ የድጋፍ ደብዳቤውን ከጻፈው የሲቪል አቬሽን ባለስልጣኑ አቶ እንደሻው ይግዙ ታቦርም ሆኑ አቶ መስፍን ጣሰው በየትኛው ደንብ ይህን ቅጥር እንደፈጸሙ ሊጣራ የሚገባ የአገር ጉዳይ እንደሆነ ጉዳዩ የሚመለከተው አይዘንጋው ባይ ነኝ፡፡

ጉዱ ይቀጥላል……

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ሁሉ እሳተፋለሁ

በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ...

በሲዳማ ክልል ከ62% በመቶ በላይ የሚታረሰው መሬት በአሲዳማነት የተጎዳ ነዉ

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚታየው የምርታማነት ማነቆ በዋናነት የመሬት አሲዳማነት...

የኢትዮጵያ እዳ እና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባ ሳይገኙ ቀሩ

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እዳ እና...

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ-ሕንድ...