የጋሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋዴፓ)
የጋሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋዴፓ) አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክላስተር ክልል አደረጃጀት የጋሞ ሕዝብ ፍላጎት ያልወከለና በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን “ማንኛውም ብሔር ብሄረሰብ የራሱን ክልል የመመስረት መብት” ያላከበረ ነው ሲል አደረጃጀቱን እንደማይቀበለው አስታውቋል። ፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክላስተር ክልል አደረጃጀትን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ “የጋሞ ሕዝብ በክልል የመደራጀትና ራስን በራስ የማስተዳደር ሕገ-መንግሥታዊ መብቱ ሊከበር ይገባል” ያለ ሲሆን፤ “መንግሥት የጋሞ ሕዝብ ያቀረበው ሕጋዊ የክልልነት ጥያቄ እያፈነ ይገኛል” ሲልም ከሷል፡፡ ፓርቲው “የጋሞ ሕዝብ ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ ገና ምላሽ ባላገኘበት ወቅት፤ የዞኑ አስተዳደርና ገዢው ፓርቲ ራሳቸው የሚቆጣጠሩት ከዓመታት በፊት የተመረጠና፤ በአዲስ ምርጫ ያልታደሰ የዞን ምክር ቤት ሰብስበው፤ “መንግሥት ያስቀመጠው የአደረጃጀት አቅጣጫ” ባሉት የክላስተር ክልል አደረጃጀት የጋሞ ሕዝብ እንዲካተት በማስወሰን ለሕዝብ፣ ለዴሞክራሲና ለሕገ-መንግሥታዊ አሠራሩ ያላቸውን እንቢተኝነት አሳይተዋል” ሲል ነው የገለጸው፡፡
በአሁኑ ሰዓት “በአዲስ መልክ ይደራጃል” ተብሎ የታሰበለት የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች የክላስተር ክልል፤ በየዞኑ በሚቀርቡ የማዕከልነት እንዲሁም የተሻሉ የክልል ቢሮዎችን ወደየራስ የማምጣት ፍላጎቶች መሐል እንደሚገኝም ፓርቲው ገልጿል፡፡ በተጨማሪም “የማዕከልነትና የቢሮ ድልድሉ እጅግ ኢ-ፍትሐዊነት የታየበትን አፈፃፀም እንዳስቀመጠም ከሚወጡ መረጃዎች መረዳት ችያለሁ” ነው ያለው፡፡ “የጋሞ ሕዝብ የራሱ የሆነውን ያለፈቃዱ አሳልፎ የሚሰጥ ሕዝብ አይደለም፡፡” ያለው ፓርቲው፤ “ይህ ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦችም ጋር አብሮነቱን አጠናክሮ በሰላምና በፍቅር የሚኖር የሰላምና የፍቅር ተምሳሌት ሕዝብ ነው፡፡” ሲልም ገልጿል፡፡ የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋዴፓ) “የሕዝብን ፍላጎት ያላማከለው መንግሥታዊ የክልል አደረጃጀት ነው፡፡” ያለውን አደረጃጀት ከእሳቤው ጀምሮ ሲቃወም መቆቱን በማስታወስ፤ ወደ ተግባር ለማስገባት እየተደረገ ያለውንም ጥድፊያ የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ለነሐሴ 04/2015 በአርባ ምንጭ ከተማ ጠርቶ እንደነበር አስታውሷል፡፡ ይህንንም በአዋጁ መሠረት ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቁን የገለጸው ፓርቲው፤ ነገር ግን የጋሞ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ የሕዝብ ሃሳብን የመግለጽ ኹለንተናዊ ሰብዓዊ መብቱን የሚጠቀምበትን አካሔድ በመደፍጠጥ ሰላማዊ ሰልፉ እንዳይከናወን መከልከሉን ገልጿል፡፡
“ሰላማዊ ሰልፉ በተጠራበት ሐሙስ ነሐሴ 04/2015 እጅግ ብዙ ቁጥር ያለው የግልና የቡድን መሣሪያዎችን የታጠቀ የወታደር ሠራዊት በአርባ ምንጭ ከተማ በየሰፈሩ ተበትኖ ሕዝቡን ሲያስፈራራና ነዋሪዎች ሰላማዊ ሰልፉን እንዳይወጡ ሲያፍን ውሏል” ያለው ፓርቲው፤ በዚህም ከ400 በላይ ዜጎች ለእስርና ለድብደባ ተዳርገው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከ60 ሰዓታት በላይ መቆየታቸውን አስታውቋል፡፡ በዚህም መሰረት የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋዴፓ) “መንግሥት የጋሞን ሕዝብ ክልላዊና አገራዊ መብት፣ ጥቅምና ክብር በሕገ-መንግሥታዊ መንገድ ያላከበረውን የአዲሱን የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምሥረታ ሒደትን ከማጣደፍ ተቆጥቦ፤ የመንግሥት ምሥረታ ሒደቱን እንዲያቆም እና የጋሞን ሕዝብ በዚሁ ጉዳይ ከላይ እስከታች የሚያወያበትን አካታችና አሳታፊ መድረኮች በአስቸኳይ እንዲፈጥር” ጠይቋል፡፡ በተጨማሪም “የዞኑ ምክር ቤት ለኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕጋዊ አሠራሩን ተከትሎ ቅሬታ ያቀረበበት የጋሞ ብሔራዊ ክልል ጥያቄ የአገሪቱ ሕገ-መንግሥት በሚያዘው መንገድ ብቻ ታይቶ አስቸኳይ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል” ብሏል፡፡ እንዲሁም “ፓርቲው ነሐሴ 04/2015 ለጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ሕገ-ወጥነትን በመከተል የጋሞ ሕዝብ ሀሳቡን በነፃነት የመግለጽ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቱን የረገጡት የጋሞ ዞን አስተዳደር እና የጋሞ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ በሕግ እንዲጠየቁና ይንንም መንግሥት ተግባራዊ አድርጎ ለሕዝብ ሊገልጽ ይገባል፡፡” ሲል በመግለጫው አሳስቧል፡፡
“በትምህርት ቤቶች” እና “በተለያዩ ቦታዎች” የታሰሩ ሰዎች መኖራቸውን መንግሥት አመነ
በአማራ ክልል ከተከሰተው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ “በትምህርት ቤቶች” እና “በተለያዩ ቦታዎች” የታሰሩ ሰዎች መኖራቸውን የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም አመኑ። በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው በይፋ ከተገለጹ ግለሰቦች ውጭ ያሉ እስሮች የተፈጸሙት፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንጂ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ (ኮማንድ ፖስት) አለመሆኑንም ገልጸዋል። የሰላም ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ የታሰሩ ሰዎችን በተመለከተ ማረጋገጫ የሰጡት፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር ሰኞ ነሐሴ 8 ቀን 2015 ባደረጉት ውይይት ላይ ይህንኑ አስመልክቶ ለተነሱላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ ነው። አቶ ብናልፍ እና የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል የመሩት ይህ ስብሰባ የተካሄደው፤ በአማራ ክልል የተከሰተውን የጸጥታ ችግር አስመልክቶ ለፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮቹ ገለጻ ለማድረግ ነበር።
ሦስት ሰዓት ከ40 ደቂቃ ገደማ በፈጀው በዚህ ስብሰባ ላይ፤ ሁለቱ ሚኒስትሮች ያቀረቡትን ገለጻ ተከትሎ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ሀሳብ እና ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል። በስብሰባው ላይ ከታደሙ 16 የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ውስጥ ጥያቄም ሆነ አስተያየት ያላቀረቡት ሁለት ተሳታፊዎች ብቻ ናቸው። አብዛኛዎቹ ተሳታፊዎች በአማራ ክልል ለተከሰተው ግጭት መንግስት ጥፋተኛ ሲያደርጉ ተደምጠዋል። መንግስት በክልሉ ላለው ችግር አስቀድሞ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ “ጉዳዩን በኃይል ለመፍታት ሞክሯል” ሲሉም ወቅሰዋል። ይህንን ወቀሳ ካሰሙት አንዱ የሆኑት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ዋና ጸሀፊ አቶ አበበ አካሉ፤ ፓርቲያቸው በሚያወጣቸው መግለጫዎች ሲነሱ የነበሩ ችግሮች እና ስጋቶችን መንግስት “ችላ” እንዳለ በማንሳት ተችተዋል። ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የወጡ የአቸኳይ ጊዜ አዋጆች “ለውጥ እንዳላመጡ” የገለጹት አቶ አበበ፤ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ለተከሰተው ችግር መፍትሔው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ ሳይሆን “ሰላማዊ ድርድር” ማካሄድ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት “የጅምላ እስር ከፍቷል” ያሉት የኢዜማ ዋና ጸሀፊ፤ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ላይ የሚገኙ የፓርቲው አመራሮች “በጅምላ” መታሰራቸውን ለዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል። የአዋጁ መውጣት በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ አመራሮች “ትላንት የጠሉትን ሰው ለማሰር” ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረም አክለዋል። ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ እስሮች ጉዳይ፤ በኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት (ኢዲህ) ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄም ተነስቷል። “በአዲስ አበባ ከፍተኛ አፈሳ ነው ያለው። ብዙ ህዝብ እየታሰረ ነው። ተጭነው የሄዱ የእኛ አባሎች አሉ” ሲሉ አቶ ገብሩ በመዲናዋ “እየተፈጸመ ነው” ስላሉት “የጅምላ እስር” በምሳሌ በማስደገፍ አስረድተዋል። “ትምህርት ቤቶች የታፈሱ [ሰዎች] ማጎሪያ ሆነው ነው የሰነበቱት” ያሉት የኢዲህ ሊቀመንበር፤ የፓርቲያቸው አባላት በደጃዝማች ወንድይራድ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ታስረው መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ ሰዎች በዚህ መልክ እየታሰሩ ቢሆንም፤ በመንግስት በኩል ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተሰጠ መግለጫ የታሰሩት 23 ግለሰቦች መሆናቸው መገለጹ ጥያቄ እንደፈጠረባቸውም አቶ ገብሩ ተናግረዋል። በመግለጫው ከተጠቀሱት ሰዎች ውጭ “የያዝነው የለም ከተባለ፤ ማነው ታዲያ እነዚህን ሰዎች እየያዛቸው ያለው?” ሲሉ ውይይቱን የመሩትን ሚኒስትሮች ጠይቀዋል። ይህን ጉዳይ አስመልክቶ በመንግስት ደረጃ ንግግሮች መደረጋቸውን ያነሱት ሁለቱ ሚኒስትሮች፤ እስሮቹ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ሳይሆን “በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር” የተፈጸሙ መሆኑን ለፓለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች አስረድተዋል። “ሚዲያ ላይ መግለጫ የተሰጠው ኮማንድ ፖስቱ የያዛቸውን ነው። ግን ከዚያ በላይ ብዙ የታሰሩ አሉ፤ በተለይ አዲስ አበባ ያሉ። ቅድም ባላችኋቸው በኮከበ ጽብሃ [ትምህርት ቤት]፣ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የታሰሩ አሉ” ሲሉ የሰላም ሚኒስትሩ በርካታ ሰዎች ለመታሰራቸው ማረጋገጫ ሰጥተዋል ሲል ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል።
