
ግልፅ ደብዳቤ
ለክቡር ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር)
አዲስ አበባ
ጉዳዩ:- በአለም መድረክ በወርቅ ቀለም የታተመውን የአድዋ ታሪክ ተገቢውን ክብር እንዲሰጠው ስለመጠየቅ ይመለከታል።
ቅድመ እያቶቻችን የዛሬ 127 አመት ብዙ ፈተናዎችን አልፈው በነፃነታቸውና በሉአላዊነታቸው ምንም ድርድር ሳያደርጉ በጠላት ወረራ ወቅት በአንድነት “ሆ” ብለው በመዝመት አድዋ ላይ የጣሊያንን ጦር ድባቅ በመምታት የአይበገሬነታቸውን ከፍታ ለትውልድ በመተው ለመንፈሳችን ኩራት የሚሆን የታሪክ ክብር ትተውልን በማለፋቸው ነጻነቷ በተረጋገጠ ሀገር የምንኖር ነፃ ህዝብ አድርገውናል::
hአድዋ ድል እንበቃ ዘንድ ያስቻሉን ጀግኖች አርበኞች ቅድመ አያቶቻችን ለሀገራቸው የከፈሉት መስዋዕትነት፣ የደረሰባቸው መከራና ስቃይ ወጣቱ ትውልድ እንዳይዘነጋው የአደራና የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲኖር በማበረታታት ረገድ አሌ የማይባል ሚና ተጫውቷል።
በዚህ ረገድም ታሪኩን የሚያከብር ትውልድ ተፈጥሮ ላለፉት 126 አመታት የአድዋ ጀግኖች እና መሪዎች ወርቃማ ታሪክ ሲዘከርና ተገቢውን ክብር ሲያገኝ ኖሯል።
የዚህ ታሪካዊ የድል ቀን አንድ አካል በነበረውና በ127ኛው የአድዋ ድል ማክበሪያ ዕለት የካቲት 23 ቀን 2015 ዓም በዳግማዊ ምንይልክ አደባባይ እንደተለመደው የድል በአልን ለማክበር የወጣው ሕዝብ ላይ በጅምላ የተፈፀመውን ሕግና ስርአትን ያልተከተለ እስራትና ድብደባ የድል በአሉ ጥቁር ጠባሳ እንዲኖረው አድርጎታል::
በተለይም የድል በአሉን ለማክበር በወጣው የአዲስ አበባ እና የዙሪዋ ከተሞች ነዋሪዎች ላይ የመንግሥት የጸጥታ ሀይሎች:-
1ኛ :- የዳግማዊ ምንይልክ ምስል ያለበት ትሸርት የለበሱና አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ አላማ የያዙ ወጣቶች ተደብድበዋል፣ ታስረዋል፣ሕጋዊ የንግድ ሱቃቸውም ታሽጓል::
2ኛ :-የታጠቁ ወታደሮች በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ቅጥር ግቢ ውስጥ በመግባት በምእመናን ላይ የወሰዱት እርምጃ የሐገሪቱን ሕገመንግስት የሚፃረርና የግለሰብን መብት የሚጋፋ በመሆኑ እጅግ አስቆጥቶናል::
3ኛ:- ከድል በአሉ መከበር በኋላም የጅምላ እስር እየተካሄደ ይገኛል። በዚህም በድል በአሉ ማክበሪያ ዕለት መንግስታዊ ሀላፊነቱን መወጣት ያልቻለው የእርስዎ አስተዳደር ጉዳዩን ሌላ መልክ እና ቅርጽ ለመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ ለመታዘብ ችለናል።
4ኛ:- እንደ ማሕበረሰብ ከገባንበት የጎጥ ፖለቲካና የብሔር ፅንፍኝነት የሞራል ውድቀትና ዝቅጠት እንድንወጣና ወጣቱ ብሔራዊ ስሜት እንዲኖረውና የድል አድራጊነት እና የአሸናፊነት ስሜት እንዲሰማው እንዲሁም ለቀጣይ ሀገር ግንባታ የስነ ልቦና ዝግጅት እንዲያደርግ መንግስት ማገዝና ማበረታት ሲገባው አሳዛኝ የታሪክ ጠበሳ ጥሎ በማለፉ ለእርሰዎም ሆነ ለመንግስትዎትም ክብር የማይመጥን ሆኗል::
በዚህም በድል በአሉ ዕለትም በምኒልክ አደባባይ በአሉን ለማክበር በተሰበሰበ ሕዝብ ላይ የተተኮሰው አስለቃሽ ጭስ ምንም በማያውቁ ሕፃናትና አረጋውያን ቀሳውስትና የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ላይ ጭምር በመሆኑ መላውን የዲያስፓራ ሕብረተሰብ እጅግ አስቆጥቷል::
በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ በአሉን ለማክበር ተገኝተው በነበሩ ሰዎች ላይ በተወሰደው እርምጃ በበርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸውና ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የሚያሳዩ ምስሎች በማህበራዊ ሚዲያ ሲንሸራሸሩ አይተናል::
በተጨማሪም በፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት አንድ መምህር መገደሉን አረጋግጠናል።
ይህ አሳዛኝ ሁኔታ የተፈፀመው በፌደራል መንግስት መቀመጫ ከተማ በመሆኑ እጅግ አሳፋሪ ነው።
በመሆኑም እኛ የዳያስፖራ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች እና ማህበራት በጋራ የሚከተሉትን የማስተካከያ እርምጃዎች መንግስት እንዲወስድ እንጠይቃለን።
1ኛ. ለውጡን መነሻ በማድረግ ከጎንዎ የነበረው የዳያስፖራ ሕብረተሰብ ከልብ ያሳዘነ ድርጊት በመሆኑ በአስቸኳይ ለተፈጠረው ስህተት መንግስት ሕዝቡን ይቅርታ እንዲጠይቅ እና ለሟች ቤተሰብም ካሳ እንዲከፍል በጥብቅ እናሳስባለን። በተጨማሪም የአላግባብ ማሸበርና ማፈን እንዲሁም ተኩሶ በመግደል ወንጀል የፈፀሙትን የፀጥታ ሐይሎች በሕግ አካላት እንዲጠየቁና ቅጣታቸውን እንዲቀበሉ መንግስትን እንጠይቃለን::
2ኛ. ከዚህ ጋር በተያያዘም የኢፌዴሪ የባህል እና ቱሪዝም ሚ/ሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳ የተሰጣቸውን የስልጣን ገደብ በመተላለፍ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከመገንባት ይልቅ ማፈራረስን፣ከመፈቃቀር ይልቅ ማጥላላትን፣ ከአንድነት ይልቅ መለያየትን፣ ከማረጋጋት ይልቅ ማበጣበጥን መርጠው የነገዋን ኢትዮጵያ ወሳኝ ትውልድ 127ኛውን የአድዋ ክብረ በአል በደመቀ ሁኔታ በጎዳና ላይ ትርኢት እንዲያከበር ሐላፊነታቸውን በእኩልነት እና በተገቢው መንገድ ያልተወጡ በመሆናቸው መንግስት አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን::
3ኛ. የአዲስ አበባ አስተዳደርና ፌዴራል ፖሊስ ህዝቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባ ሕጋዊ ጥበቃ ማድረግ ሲገባቸው በታጠቁ ወታደሮቻቸው አማካኝነት ያልተመጣጠነ እርምጃ በመውሰድ ለተፈፀመው ወንጀል ተቋማቱ የአዲስ አበባ ከተማን ሕዝብ ይቅርታ እንዲጠይቁ በጥብቅ እናሳስባለን:: የተወሰዱትንም ዝርዝር እና ግልጽ እርምጃዎች ለህዝብ በአስቸኳይ ይፋ እንዲያደርግ እንጠይቃለን።
በመጨረሻም አበክረን የምናሳስበው ጉዳይ ቢኖር አሁን የምንገኘው በሐገራችን በተለየ ታሪካዊ ወቅት በመሆኑ ከዘመኑና ከሕዝብ ፍላጎት ጋር ልንጣጣም የማንችል ከሆነ በራስ ላይ ሰይፍ እንደመምዘዝ የሚቆጠር መሆኑን በማስታወስ በዚህ እና ሌሎች ተደራራቢ ምክንያቶች መነሻነት በሐገራችንና በታሪካችን ላይ የማንደራደር በመሆኑ ታውቆ፣
ለሀገራችን ክብር ላለማስደፈር ሲሉ በክብር የወደቁ አባቶቻችንን በውሸት ትርክት እያበሻቀጡ ትውልዱ ተደግፎ የሚቆምበት የታሪክ ምርኩዝ ለማሳጣትና የአዲሱን የለውጥ ስርዓት አቅጣጫውን ለማደናቀፍ ብሎም እርካሽ የፖለቲካ ጠቀሜታን ለማግኘት የሚሯሯጡትን ስነምግባር የሌላቸው የመንግስትዎ አመራሮች ከሚራምዱት አደገኛ የዘረኝነት አካሄዳቸው እንዲቆጠቡ በጥብቅ እናሳስባለን::
የአድዋ ድልንም ሆነ ሌሎች ህዝባዊ በአላትን ሕዝቡ በነፃነት እና በፈለገው ቦታ የመረጠውን ልብስ ለብሶ ክብረ በአላቱን ማክበር እንዲችል መንግሥት አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃዎችን እንዲወስድና ቁርጠኛ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ በአስቸኳይ እንጠይቃለን።
አድዋ አባቶቻችን ያወረሱን የመንፈስ ኩራት ከመሆን ባሻገር ቋሚ የኢትዮጵያዊነትና የነጻነት ርስታች ነው:: የኢትዮጵያውያኖች ህብር፣ ብሎም የብዙኃነታችን መገለጫ የሆነው አድዋ በፅንፈኞች የከሰረ አሰተሳሰብና የታሪክን ትርክት የሳተ አሰተሳሰብ መኮላሸት የለበትም::
ኢትዮጵያዊነት የዘላለም ችቦ ነው:: ኢትዮጵያን ሊያጠፏት የሚነሱትን እያጠፋች ትበራለች እንጅ በፅንፈኛዎች ተንኰል አትጠፋም::
ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ፈጣሪ አብዝቶ ይባርክ!
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት (CEDA)