ከሁለት ሳምንት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በካዛን ሩሲያ በተካሔደው የብሪክስ 16ኛው መደበኛ ጉባኤ ላይ ታድመው ተመልሰዋል፡፡ እንደ እውነቱ ከኾነ የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ብዙ ተጻራሪ ሐሳቦች እንዲሰነዘሩ መግፍኤ የሚኾን ነው። በአንድ በኩል እርምጃው ሊገኙ ይችላሉ ከሚባሉት ጥቅሞች አንጻር ይበል የሚያሰኝ መኾኑ ግልጽ ነው፡፡በሌላ በኩል ግን ከሚመጡት ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖዎች በመነሳት ነገሩ ይበልጥ የከፋ ሊኾን ይችላል የሚል ሥጋትም ይፈጥራል። ለዚህ በምክንያትነት ሊጠቀሱ ከሚገባቸው ነጥቦች መካከል አንዱ፣ ብሪክስ ብዙ ሕጸጾች ያሉበት እና መጻኢ እድሉ ገና ‹‹እንዲህ ነው›› ያልተባለ ከመሆኑ አንጻር፣ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያለውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲ እና ሌሎችም ግንኙነቶች የሚያበላሽ ከመሆኑ በላይ ሀገሪቱን በጠላትነት የሚያስፈርጅ ሊኾን የመቻሉ እውነታ ነው። አንዳንዶች የደሀዋ ኢትዮጵያ በዚህ የዝሆኖች ፍልሚያ ላይ መገኘት ‹‹እዩኝ እዩኝ›› ከማለት ያልዘለለ እና ወደ ኋላ ብዙ ጣጣና መከራ ይዞ መምጣቱ የማይቀር ነው የሚል አስተያየት በድፍረት ለማንሳታቸው መግፍኤ የኾነውም ይኼ ነው።
አሁን እያየነው እንዳለው እውነታ ከኾነ፣ ኢትዮጵያ በዚህ የዝሆኖች ፍልሚያ ላይ በሁለት ካርድ መጫወቱን የመረጠች ይመስላል። እጅግ ታሪካዊና ሥርነቀል በሚባል ሁኔታ ከምዕራቡ ዓለም ተቋማት ጋር ያደረገችው ስምምነት መንፈቅ እንኳ ሳይሞላው፣ ከነዚህ ተቋማት ጋር ዐይን እና ናጫ ከሆነው ቡድን (ብሪክስ) ጋር እኩል ቆማ መሰለፏ የሚያሳየውም ይኼን ነው። በዐለም ባንክ እና በአይ ኤፍ ኤም ገፋፊነት የተተገበረ የሚመስለው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ለሀገሪቱ ይዞላት የሚመጣው በረከት ይሁን መርገምት ገና ምኑም ባልታወቀበት ሁኔታ፣ በምዕራባውያን ወጥመድ ውስጥ መውደቋ፣ ኢኮኖሚዋን ያሻሽለዋል ወይም ያዘምነዋል የሚለው ጥያቄ ግን በቀጣይነት የሚታይ ነው። ኾኖም በብዙ ቅድመ ሁኔታ እና ሤራ የተተበተበውን የምዕራቡ ዓለም ተቋማት ስምምነት ፈርሞ፣ ከተቃራኒው ኃይል ጎን መሰለፍ ምናልባት አንገቷ ላይ የተተበተበውን ሸምቀቆ ከማጥበቅ እና የበለጠ ከመታነቅ የዘለለ ውጤት ላይኖረው ይችላል የሚለው ሥጋት መናቅ አይኖርበትም።
ይኽም ኾኖ ኢትዮጵያ የጨዋታውን ሕግ በአግባቡ ተረድታ በደንብ መጫወት ከቻለች፣ በሁለት ካርድ መጫወቷ ጥቅሟን የሚያስከብር እንጂ ምንም ጉዳት ላይኖረው የመቻል ዕድል እንዳለውም ማመን አስፈላጊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በእስከ አሁኑ ጉዞዋ ሌላው ቀርቶ ከዩናይትድ ዐረብ ኢምሬትስ እና ከቻይና ጋር ያደረገችው በራስ ገንዘብ የመገበያየት ስምምነት፣ የብሪክስ በረከት መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያዎች መኖራቸው፤ በቀጣይም ከሌሎች ሀገራት ጋር ይህን ስምምነት አጠናክራ ከቀጠለች ከጉዳቷ ጥቅሟ እንደሚበዛ ማመንን ቀሊል ያደርገዋል፡፡
ይኽም በውጭ ምንዛሪ እጥረት ረገድ በተለይም ደግሞ የዶላርን ሚና መቀነስ የሚያስችላት ሲሆን ይህም ኢኮኖሚዋን የሚታደግ፣ ከዚህም አልፎ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትን የሚከላከል በመኾኑ አዋጭነቱ ቀላል አለመኾኑን እርግጥ ያደርገዋል። የኢትዮጵያ የገቢ እና የወጪ ንግድ በአብዛኛው ከነዚህ የብሪክስ አባል ሀገራት ጋር ከመሆኑ አንጻርም፣ ኢትዮጵያ የዚህ ስብስብ አባል መሆኗ አብዝቶ የሚጠቅማት እና ብዙ በረከቶችን የሚያዘንብላት ሊኾንም ይችላል፡፡ ግዮን መጽሔትም መንግሥት፣ የመንግሥትነት ሚናውን የሚወጣው የታላቋን ኢትዮጵያ እና የሕዝቦቿን ጥቅም የሚያስጠብቅ፣ አስተውሎት የተሞላበት እና እርጋታን የተላበሰ መርህን በመከተል ከመኾኑ አንጻር ጉዳዩን በአሸናፊነት ለመወጣት የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራውን በአንድ በኩል፣ የብሪክስ አባልነቱ የሚሰጠውን ጥቅም ደግሞ በሌላ በኩል አሰናስሎ ሀገሪቱን የገዛ እጆቿ ሳይኾኑ ሌሎች ወገኖች በጻፉላት ዕጣ ፈንታ ላይ እንዳትራመድ የበኩሉን ያድርግ ስትል ምክረ ሐሳቧን ለማስተላለፍ ትወዳለች፡፡
———-
ቅጽ 6 ግዮን ቁጥር 218 ሕዳር 14 ቀን 2017 ዓ.ም
