መንግስት በ2016 ዓ.ም መገባደጃ ከዓለምቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር በደረሠው ስምምነት መሠረት አጠቃላይ የሚለቀቅለት ብድር ከ2.18 ቢሊዮን ዶላር ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና የገንዘብ ሚኒስቴር በትናንትናው ዕለት በጋራ ባወጡት መግለጫ ሀገር በቀል እያሉ የጠሩት የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ አፈጻጸም ላይ ወሳኝ ምዕራፍ የሆነው አራተኛው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ግምገማ በስኬት መጠናቀቁን አመልክተዋል፡፡
በግምገማቸውም አፈጻጸሙ ከተገመተው በላይ ጠንካራ ሆኖ መገኘቱ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
ኢኮኖሚው በዚህ ወቅት የተለያዩ ውጤቶችን እያሳየ እንደሚገኝ የሚገልፀው መግለጫው የተደረገዉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ካመጣቸው ዉጤቶች አንዱ የዋጋ ግሽበት በከፍተኛ ፍጥነት እንዲቀነስ ማድረጉ መሆኑን አመልክቷል፡፡ የዋጋ ግሽበት ወደነጣል አሐዝ መውረዱን የስታትስቲክስ አገልግሎት ከዚህ ቀደም ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
ጠንካራ እና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት መመዝገብ፣ የተሻሻለ የበጀት ዲሲፕሊን እና የውጭ ምንዛሪ ክምችት በቋሚነት እያደገ መምጣቱ የሪፎርሙ ዉጤቶች ናቸው ሲል አሞካሽቷል፡፡
