ከእሸቱ ደስታ
መደበኛ ያልሆነው የኢኮኖሚ ዘርፍ ጠቃሚ እንዲሁም አነጋጋሪ ሚና በብሔራዊ ኢኮኖሚ ውስጥ እንዳለው ይታወቃል፡፡ መደበኛ ያልሆነው ክፍለ ኢኮኖሚ አነጋጋሪ የሆነበት ምክንያት በመንግሥት የማበረታቻ ሁኔታ ስላልተዘረጋለትና በማበረታቻ ማዕቀፍ ውስጥ ስላልተካተተ ነው፡፡ በሌላ በኩል ይህ ዘርፍ ድህነትን ከመቅረፍ፣ የሥራ ዕድልን ከመፍጠር፣ ሥራ አጥነትንና ሥራ ፈትነትን ከመቀነስ አንፃር እጅግ ጠቃሚ በመሆኑ ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ቢኖሩም መደበኛ ባልሆነው የኢኮኖሚ ዘርፍ የራሱ የሆነ መለያ ባሕሪያት አሉት፡፡ ከነዚህም መካከል፡-
- ለመቀላቀል ቀላል የሆነ፣
- በሀገር ሃብት ላይ የተመሠረተ፣
- በቤተሰብ ባለቤትነት የሚቋቋም፣
- በአነስተኛ ደረጃ የሚሰራ፣
- በሰው ጉልበት የሚሰራና በቀላሉ የሚለመድ ቴክኖሎጂ፣
- ሙያው ከመደበኛ ክፍለ ኢኮኖሚ ውጪ የሆነ፣
- ቁጥጥር አልባና ውድድር የበዛበት ንግድ፣
- የከተሞች እድገት፣
- የኢኮኖሚ ድቀት፣
- ሥራ አጥነትና
- ፍትሐዊ ያልሆነ ማኅበራዊ ክፍፍል
ሲሆኑ እነዚህም መደበኛ ላልሆነው ኢኮኖሚ ያለማቋረጥ መቀጠል እንደ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል ፡፡
በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው 50.6 ከመቶ የሚሆነው የከተማ ሰራተኛ ኃይል የተሰማራው መደበኛ ባልሆነ ክፍለ ኢኮኖሚ ውስጥ ነው ይላል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች መደበኛ ክፍለ ኢኮኖሚውን የለቀቁ ሰራተኞች ለኑሮአቸው መደጎሚያ ለማግኘት ሲሉ መደበኛ ወደአልሆነው የኢኮኖሚ ዘርፍ ይቀላቀላሉ፡፡ በመሆኑም መደበኛ ያልሆነው የኢኮኖሚ ዘርፍ በማያቋርጥ ሁኔታ በማደግ ላይ ነው ፡፡
መደበኛ ባልሆነ ክፍለ ኢኮኖሚ የሚሳተፉ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ሴቶች አና ድህነት ያላቸው ትስስር ምንድን ነው ብለን ስንጠይቅ መደበኛ ያልሆነ ክፍለ ኢኮኖሚ መሥራትና ድህነት ግልጽ የሆነ ቁርኝት አላቸው ፡፡ መደበኛ በሆነው ክፍለ ኢኮኖሚ ውስጥ ከሚሰሩት ሰዎች መደበኛ ባልሆነው ዘርፍ የሚሰሩት በድህነት ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ የሚያሳየው ከፍተኛ ቁጥርን የያዙት ሴቶች መሆናቸውን ነው፡፡
ይህ አካል የብድር አገልግሎት ለማግኘት ያለው እድል አናሳ መሆኑ ለአሰሪና ሰራተኛ አዋጅም ቢሆን ከለላ ያልተደረገለትና ፖሊስ በሚነደፍበትም ጊዜ ድምፁ የሚሰማበት ሁኔታ ያልተመቻቸለት ነው፡፡ በአብዛኛውም በዘርፉ የሚሳተፉት አነስተኛ ክፍያ የሚያገኙ የገቢ ዋስትና የሌላቸውና በሕብረተሰቡም ሆነ በሥራ ስምሪት የሚሰጣቸው ግምት ዝቅተኛ የሆኑ ናቸው፡፡ ለኢኮኖሚ እድገት ከፍ ያለ ሚና የሚያበረክቱ ቢሆኑም እውቅና ያልተሰጣቸው፣ ያልተመዘገቡ፣ የሕግ ከለላ ያላገኙ በጥቅሉ ከማኅበረሰቡ የተገለሉ አካላት ናቸው ለማለት ያስደፍራል፡፡ በመሆኑም እንደዚህ ባለ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ከድህነት አዙሪት ውስጥ ለመውጣት ይቻላል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡
በተለይ መደበኛ ባልሆነ ክፍለ ኢኮኖሚ ውስጥ የተሰማሩ ሴቶች ከመሰል ወንድሞቻቸው አንፃር ሲታይ የበለጠ ሰብአዊ መብታቸው የተጣሰና ተጎጂ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ሊሆን የቻለው በኢትዮጵ በሚታየው የተለያየ ባህላዊና ማህበራዊ ምክንያቶች ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሕጉ ከለላ ስለማያደርግለቸው ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ ካለማግኘታቸውም በተጨማሪ የተለያዩ የመብት ጥሰቶች ይደርስባቸዋል፡፡
መደበኛ ያልሆነው ክፍለ ኢኮኖሚ ያለው ምርታማነት በአንፃራዊ መልኩ ሲታይ ዝቅተኛ ነው፡፡ ስለሆነም ለስልጠና፣ ለእውቀት ሽግግር፣ ለአደረጃጀት እድገትና ለህግ ትኩረት መስጠት ተስማሚ የሥራ እድል የሚገኝበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ክፍለ ኢኮኖሚው በስፋት ያቀፋቸው በርካታ ቁጥር ያላቸው በአነስተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በተለይም ሴት ነጋዴዎችና አሰሪዎችን በመሆኑም ተጠቃሚ ማድረግ ለኢኮኖሚ እድገት የጎላ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡
በአብዛኛው የአንድ መንግሥት ታላቅነት የሚለካው ለድሆች በሚሰጠው ድጋፍ ነው፡፡ መንግሥት ከፊል መንግሥታዊና እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች “መብትን መሠረት ባደረገ ሁኔታ” ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ባሻገር ተጎጂ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ማስተማር ውጤታማነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ዘዴ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በዚህም መደበኛ ባልሆነው ኢኮኖሚ ውስጥ ያሉ ሰራተኞች ኃይላቸውን እንዲያጠናክሩ በጋራ በመረዳዳት መንፈስና ሰብዓዊ መብታቸውን በማስከበር ለውጥ ለመምጣት ያስችላቸዋል፡፡
መደበኛ ያልሆነውን ክፍለ ኢኮኖሚ መደበኛ ባልሆኑ ማኅበራት ወይም በማንኛውም ተመሳሳይነት ባላቸው ድርጅቶች ውስጥ እንዲደራጁ ማድረግ ነው፡፡ መደበኛ ባልሆነ ኢኮኖሚ ውስጥ በተሰማሩ ሰራተኞች ላይ የተሳሳተ አመለካከት ምክንያት ሕጋዊ ለመሆን አይፈልጉም የሚሉ አካላት አሉ፡፡ በተቃራኒው ሰራተኞች በራሳቸው መንገድ መልካም የሥራ ሁኔታን ለማምጣት በመደራጀት ዙሪያ የተወሰነ እንቅስቃሴዎችን አድርገዋል፡፡ ሆኖም ሕጋዊ የመሆን ጥረታቸው ባላቸው ዝቅተኛ እውቀት ያልተቀናጀ አሠራርና ዝቅተኛ የሰብአዊ መብት እውቀት ምክንያት ተዳከመ ነው፡፡
መደበኛ ባልሆነው ኢኮኖሚ ውስጥ የተሰማሩትም የሙያ ዘርፋቸው የተለያየ ከመሆኑም በላይ በዘርፉም የሚሳተፉት አንድ ዐይነት ስብስቦች አይደሉም፡፡ በዘርፉ የሴቶች ተሳትፎ ከፍተኛ በመሆኑ በፆታቸውና በዝቅተኛ ማህበራዊ ምጣኔ ሐብት ሁኔታዎቻቸው ምክንያት ለበርካታ ችግሮች ተጋላጭ ሆነዋል፡፡
በዚህ ሰፊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሳተፈው የሕብረተሰብ ክፍል አሁን በዘርፉ ላይ የተሰማራው ብቻ ሳይሆን ከፈጠራ ሥራና አነስተኛና ጥቃቅን ሥራዎችን በማስፋት በተለይ ወጣቱን የሥራ ባለቤት ለማድረግ ከተያዘው ስትራቴጂ አንጻር ቁጥሩ በርካታ ሊሆን እንደሚችል በመገመትና በተለይም ሴቶች በዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑና በሥራው ላይ ከተሰማሩም በኋላ ከወንድ ወንድሞቻቸው እኩል ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበትን ሥርዓት በመዘርጋትና በጾታቸውም የተነሳ ከሚደርስባቸው የወሲብ ትንኮሳ አስገድዶ መደፈርና ሌሎች አካላዊ ጥቃቶች እንዲጠበቁ ሁሉም ወገን ተባብሮ መሥራት የግድ ይላል፡፡
ሌላው ዛሬ መደበኛ ባልሆነው የኢኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ ተሰማርተው የሚገኙ በተለይም ሴት ሰራተኞች እየደረሰባቸው ካለው መጠነ ሰፊ ችግር በማላቀቅ ለተያዘው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአጠቃላይ ከሁሉም ወገን ተገቢው ድጋፍ ከተደረገ የእነዚህን ችግር በማላቀቅ ለሀገር የኢኮኖሚ እድገት ያለው አወንታዊ አስተዋፅኦ የማይናቅ ነው፡፡
