
አንድ መቶ አዲስ ሰዎችን ማግኘትን ዓላማዬ አድርጌያለሁ፡፡ በተለያየ የእድሜ ክልል፣ ከተለያየ የሃገራችን ክፍል በዛው ልክ የተለያየ የሕይወት መንገድ እየተጓዙ ያሉ ሰዎችን ነው እያገኘሁ ያለሁት፡፡ ታሪካችንን አውርተንና ተግባበተን መጀመሪያ የነበረው አለመተዋወቅ ቀርቶ ሁለታችንም በሕይወታችን አንድ የምናውቀው ሰው ጨምረን እንለያያለን፡፡ በ18/7/2014 ዓ.ም አመሻሽ ማክያቶ ጠጥተን ከለገሃር ወደ ፒያሳ በሚያስኬደው መንገድ የእግር ጉዞ እያረግን በቀጣይ የምታነቡትን አካፈለኝ፡፡
“አባቴ የሦስት ወር ልጅ እያለሁ ነበር ሕይወቱ ያለፈው፡፡ እናታችን ናት ያሳደገችን፡፡ ጠንካራ እናት ነው ያለችን፡፡ አስተዳደጌ በሁለት መንገድ አሁን ያለኝ ሕይወት ላይ አስተዋጽዖ አለው፡፡ አንደኛው መጥፎ ነገር የነበረ ቢሆንም አሁን ወደ መልካም የቀየርኩት ሲሆን ሌላው እንደዛው የወሰድኩት ነው፡፡ ልጅ እያለን ዘመድ አዝማድ የሚሰበሰብበት አጋጠሚ ሲኖር ዘመዶቻችን እኛን በነበረን የኑሮ ደረጃ ምክንያት የሚያዩበት መንገድ ጥሩ የኑሮ ደረጃ ላይ ካሉት ይለያል፡፡ ገና ያኔ ነው እኔ ሳድግ ሃብታም መሆን እንዳለብኝ የወሰንኩት፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን ቤተሰቦቼም ጭምር፡፡ ያኔ እንዳለምኩት ነው የሆነው፡፡ እህቴም ወንድሞቼም አሁን ሁሉም ተምረውም በተለያየ ሥራም ተሰማርተው ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ አሉ፡፡ ሃብታም መሆን ብፈልግም ሕይወቴ ስለ ገንዘብ ብቻ በማሰብና ለገንዘብ ብቻ በመሥራት የተሞላ እንዳይሆን ደግሞ የእናቴ አስተዋጽዖ አለበት፡፡ ልጅ እያለን የቤተሰብ ውርስ ቀጥታ የሚገባት ሆኖ አልፈልግም ብላ ትታዋለች፡፡ ከገንዘብ ይልቅ ለሰዎች ቦታ መስጠትን ከሷ ተምሬያለሁ፡፡
የሀገራችንን የትምህርት ሥርዓት አላምንበትም፡፡ ካምፓስ ገብቼ የምማረውን ትምህርት እንደማልሰራበት አውቅ ነበር፡፡ ቢሆንም መግባት እና መማሩ መደበኛ ትምህርቱንና ወረቀቱንም ከማግኘት ውጪም ጥቅሞች አሉት፡፡ ዋነኛው የወደፊት ሕይወቴ ምን እንዲሆን እንደምፈልግ የማሰቢያ ግዜ ነው፡፡ ለሱ ደግሞ ሦስት ዓመት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሕግ ለመማር ወሰንኩ፡፡ አንደኛ እንደምፈልገው አምስት ዓመት ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ሕግ እንደሌሎቹ ትምህርቶች አይደለም፡፡ በመሸምደድ ብቻ አይታለፍም፡፡ የፍልስፍናም ነገር አለው፡፡ ለውጤት ምንም አልጨነቅም ነበር፡፡ የማለፊያውን ውጤት ካገኘሁ ለኔ በቂ ነበር፡፡ ሌሎች ተማሪዎች ለፈተና ተጨናንቀው ሲያነቡ እኔ የፈለኩትን ሌላ ነገር አነባለሁ፡፡ ካምፓስ እያለን የክርክር ፕሮግራም የኛ እና የኢኮኖሚክስ የትምህርት ክፍል ጋር አንድ ላይ በመሆን እናዘጋጅ ነበር፡፡ አዳራሹ ሞልቶ አስተማሪዎቻችንም ተገኘተው የተለያዩ ሐሳቦችን አንስተን እንከራከር እና እንወያይ ነበር፡፡”
መጻሕፍት
“ተግባራዊ የሚሆን መጽሐፍ ማንበብ እወዳለሁ፡፡ መጻሕፍት ሳነብ ለሆነ ዓላማ ነው፡፡ ብዙ ሰዎችን ጠይቄ ለምን እንደሚያነቡ ለመረዳት ጥሬያለሁ፡፡ አውቃለሁ ምንም ዐይነት ነገር ማንበብ መጥፎ ሆኖ አይደለም፤ ግን በቃ ግዜያችንን የምናጠፋበት ነገር ሊጠቅመን ይገባል፡፡ ለምሳሌ ፍርሐትን ስለማስወገድ የሚያወራ መጽሐፍ ከሆነ መጽሐፉን አስቀምጬ የሚያስፈሩኝን ነገሮች ዝርዝር እጽፍና አንድ በአንድ ማድረግ እጀምራለሁ፡፡ እውቀት ወደ ድርጊት ካልተቀየረ ምንም ዋጋ አይኖረውም፡፡”
ቢዝነስ
“ተመርቄ ከወጣሁ በኋላ እንዲሁ ከወንድሞቼ ጋር አንዳንድ ቢዝነስ እሰራ ነበር፡፡ የሆነ ግዜ ሰዎች ንግግር ሳደርግ አይተውኝ ሥራ አስኪያጅ እንድኾን ጥያቄ አቀረቡልኝ፡፡ ከምንም ነገር በላይ ነጻነቴን ነው ማስቀድመው፡፡ ሥራ አስኪያጅ መሆን ደግሞ ከተቀጣሪነት በተሻለ ነጻነት አለው፡፡ ስለዚህ ብዙም ሳላቅማማ ሥራውን ተቀበልኩ፡፡
በዚህ መሃል ከጓደኞቼ ጋር “bucket list” ማድረግ የምንፈልጋቸውን ወጣ ያሉ መቶ ነገሮች ዘረዘርን፡፡ ለምሳሌ ከዝርዝሮቹ ውስጥ የሰው ግቢ አንኳኩተን ግቢያችሁ ውስጥ ኳስ እንጫወት ማለት፤ ትልልቅ ሆቴሎች ሄደን ክፍል በነጻ እንድንጠቀም መጠየቅ፡፡ እንቢ ሲሉን መሄድ አይደለም ደግሞ “አሁን ያልተያዙ ክፍሎች አሉ አይደል? ምን ችግር አለው ብናርፍበት” እያልን ለማሳመን እጥራለን፡፡ መንገድ ላይ የማናቃቸውንም ሰዎች አቅፈናል፡፡ አንድ ላይ እናቅደው አንጂ ድርጊቶቹን ለየብቻ ነበር የምናደርገው፡፡ ከሁሉም የማይረሳኝ እና ከልቤ ለምንም ነገር ግድ የለኘም የሚል ስሜት እንዲሰማኝ ያደረገው መስቀል አደባባይ ላይ ሱፍ ለብሼ በጀርባዬ የተኛሁበት ነው፡፡ ብዙ ነገሮችን ስናደርግ ሰዎች ምን ይሉን ይሆን ብለን እንፈራለን፡፡ የሚያቀኝ ሰው ቢያየኝ ምን ያስባል ብለን እንጨነቃለን፡፡ ምን እሱ ብቻ ድጋሚ የማናገኛቸው ሰዎች ስለኛ ለሚኖራቸው ግምት እንቅልፍ አጥተን እናድራለን፡፡ በዛ ብዙ ሰው እንደ እብድ እያየኝ በተኛሁበት ቅጽበት ግን ስለማንምና ስለምንም ግድ ያለመኖር እና ፍጹም የሆነ ነጻነት ተሰማኝ፡፡ ወዲያው ሥራ ለመልቀቅ ወሰንኩ እና ለቀቅኩ፡፡ የራሴ ቢዝነስ እንዲኖረኝ እፈልግና እንደሚኖረኝም አውቅ ነበር፡፡ የራሴን ቢዝነስ ከቢዝነስ አጋሮቼ ጋር አቋቁመን መሥራት ጀመርን፡፡
ሥራ ከሰዎች ጋር መስራት ከባድ የሚያረገው ብዙ ነገሮች አሉ፤ ግን ደግሞ ለኔ እንደግዴታ ነው፡፡ በተለይ በኛ ሀገር “startup” አዲስ ቢዝነስ ሲጀመሩ ብዙ ውጣ ውረድ አለው፡፡ ችግሮችን አብረውን የሚካፈሉና ስኬቱንም አብረውን የሚያከብሩ ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ ችግሮቹን ለመቀነስ በደንብ በንግግር ማመን ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ደግሞ በመካከል ታይታ የሚወድ ሰው አለመኖሩን ማረጋገጥ ነው፡፡”
ስለ ቢዝነስ ባለቤቶች ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች
”ብዙ ሰዎች የቢዝነስ ባለቤቶችን ’ታድለው’ ይላሉ፡፡ የሚሉት ከተሳሳተ አመለካከት ተነስተው ነው፡፡ አንደኛው አንድ ሰው አዲስ ቢዝነስ መጀመር ሲያስብ እና ሲጀምር ሃሳቡ በቤተሰቡና አካባቢው ባሉ ሰዎች ተቀባይነት አያገኘም፡፡ እንደ ጥሩ ነገር አይታይም፡፡ በተለይ የተማረ ከሆነ በቃ የተረጋጋ እና ዘላቂ የሆነ ሥራ ተይዞ መኖር ነው እንደ ተሻለ አማራጭ የሚታየው፡፡
ሁለተኛው ከተቀጣሪዎች ባነሰ የምንሰራና ቁጭ ብለን የምናዝ ይመስላቸዋል፡፡ በፍጹም እንደዛ አይደለም፡፡ ለምሳሌ እኔ ቅዳሜን ጨምሮ በቀን ለ12 ሰዓታት እሰራለሁ፡፡ በዛ ላይ እረፍት የሚነሳና የሚያጨናንቅ ሥራ፡፡ ሌላኛው ደግሞ በጣም ሀብታም እንመስላቸዋልን፡፡ አሁንም እንደዚህ አደለም፡፡ ገንዘብ ሲገኝ እንኳን ድርጅቱ ላይ ነው በድጋሚ ሥራ ላይ እንዲውል የሚደረገው፡፡
ሌላው የተሳሳተ ነገር ብዬ የማስበው ለሁሉም ቢዝነስ የሚበቃ ገበያ የለም፡፡ አብዛኛውን ግዜ ሁለት ቢዝነሶች ናቸው ገበያውን የሚቆጣጠሩት፡፡ ሁሉም ቢዝነስ ተፎካካሪ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ተፎካክሮ ከመጀመሪያዎቹ ሁለት ውስጥ ካልገባ ያስቸግረዋል፡፡ ለምሳሌ ራይድና ፈረስን ማየት እንችላለን፡፡ ቀሪዎቹ አሉ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ሁለም ሰው ቢዝነስ ለመስራትም አልተፈጠረም ብዬ ነው ማስበው፡፡ የቢዝነስ ሰው መሆንም ተሰጥኦ ይጠይቃል፡፡ ለመዝፈን፣ ወይ ጋዜጠኛ ለመሆን የሆነ ተሰጥኦ እንደሚያስፈልገው ማለት ነው፡፡ ሁሉም ሰው በሚወደው ነገር ላይ በሙሉ ልቡ እራሱን ሆኖ ሲሰራ ነው ወጤታማ መሆን የሚችለው፡፡ ሌሎች ሰዎች በተፈጥሮ የምናደርገውን እና ስናስመስል ወይንም ያልሆነውን ለመሆን ስንጥር ይታወቃቸዋል፡፡”