በሱዳን ከ60ሺ በላይ ሰዎች ኤል-ፋሸር ከተማን ለቀው መሠደዳቸውን ተመድ አስታወቀ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ እንዳስታወቀው፥ በዳርፉር ግዛት የምትገኘው ኤል-ፋሸር ከተማ በፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች (አርኤስኤፍ) ስር በመግባቷ ከ60ሺ በላይ ዜጎች ከከተማዋ ለመሰደድ ተገደዋል።
ሪፓርቶች እንዳሳዩት፥ የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ለ18 ወራት ከበባ ውስጥ ያቆያትን ከተማ ከተቆጣጠረ በኋላ፥ በከተማዋ ከባድ ጥቃት በመክፈት በሰዎች ላይ ግድያና አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸሙ ተነግሯል።
በስፍራው ረሀብ መከሰቱን ተከትሎም፥ ከኤል ፋሸር በስተምዕራብ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ወደ ታዊላ ከተማ የሚሰደዱ ሰዎች ፍሰት ባለፉት ጥቂት ቀናት እጅጉን ጨምሯል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ አሳውቆኛል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
በምእራብ ዳርፉር ግዛት በኤል ፋሸር ከ150ሺ በላይ ሰዎች ለእስር ተዳርገዋልም ነው የተባለው።
አርኤስኤፍ በኤል ፋሸር የተፈጸመው ግድያ ብሄርን መሰረት ያደረገ እና የአረብ ወታደራዊ ሃይሎች አረብ ባልሆኑ ህዝቦች ላይ ያነጣጠሩበት ነው በሚል የቀረበበትን ውንጀላ አስተባብሏል።
በሱዳን ጦር እና በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል መካከል በሚያዝያ 2023 የስልጣን ትግል ከተቀሰቀሰ በኋላ፥ ሀይላቱ ሀገሪቱን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ከትተዋታል።
በምእራብ ዳርፉር ክልል ረሃብ እና የከፋ እልቂት መከሰቱ ሲነገር፥ በመላ ሀገሪቱ በተከሰተው ጦርነት ከ150ሺ በላይ ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።
12 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ መሰደዳቸውን የመንግስታቱ ድርጅት የዓለማችን ትልቁ የሰብአዊ ቀውስ ሲል ባቀረበው ሪፓርት ገልጿል።
