ግዮን መጽሔት :-ለኢትዮጵያ ሰላም ምርጫ አማራጭ የሌለው መንገድ ነው። በጠመንጃ ኃይል ወይም በግርግር የሚመጣ ለውጥ ዘላቂ ሰላምን አያመጣም። ይልቁንም አዲስ ቂምና ቁርሾን ይወልዳል። ምርጫ ግን የሐሳብ ግጭቶችን በወረቀትና በድምፅ የመፍቻ መድረክ ነው።
ዜጎች በምርጫ ሲሳተፉ፣ የፖለቲካ ልዩነቶቻቸውን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መስማማታቸውን እያሳዩ ነው። ይህ ደግሞ ለባህላዊ ዕድገታችንም ወሳኝ ነው። “የውይይትና የድርድር ባህል” በዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ውስጥ ይጎለምሳል። YCDF እንደሚያምነው፣ ባህላዊ እሴቶቻችንን ከዘመናዊ ዲሞክራሲያዊ መርሆዎች ጋር በማቀናጀት፣ ምርጫን እንደ ትልቅ አገራዊ የሰላም ፌስቲቫል ማየት ይገባናል።
ካለመሳተፍ የሚመጣ አደጋ
“ፖለቲካ አይመለከተኝም” የሚል አቋም መያዝ ራሱ የፖለቲካ ምርጫ ነው። ይህ ምርጫ ግን አደገኛ ነው። ዜጎች በምርጫ ካልተሳተፉ፣ ሥልጣን ያላቸው አካላት ተጠያቂነት እንዲሰማቸው የሚያደርግ ኃይል ይጠፋል።
በተጨማሪም፣ ዝቅተኛ የመራጮች ተሳትፎ ባለበት ምርጫ የሚመረጥ መንግሥት ጠንካራ የሕዝብ ቅቡልነት (Legitimacy) ላይኖረው ይችላል። ይህ ደግሞ ለመረጋጋትና ለልማት እንቅፋት ይሆናል። ስለዚህ፣ የምርጫ ተሳትፎ የግል መብት ብቻ ሳይሆን፣ ለአገር ህልውና ሲባል የሚከፈል የዜግነት ግብር ነው።
ጥሪ ለወጣቱና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ
የመጪው 7ኛው አገራዊ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን የወጣቶችና ባህል ልማት ፋውንዴሽን (YCDF) የሚከተሉትን ጥሪዎች ያቀርባል፡-
- ለወጣቶች፡ እናንተ የአገሪቱ ጉልበትና አእምሮ ናችሁ። በምርጫ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ ስትሆኑ ስለ ወደፊት ዕጣ ፈንታችሁ እየወሰናችሁ መሆኑን እወቁ። የምዝገባ ካርድ ውሰዱ፤ ሌሎችንም አነሳሱ። በምርጫ ወቅትም ከጥልና ከሁከት በመራቅ፣ በሐሳብ የበላይነት ብቻ ተከራከሩ።
- ለወላጆችና ለማኅበረሰብ መሪዎች፡ ልጆቻችሁና የአካባቢያችሁ ነዋሪዎች የምርጫ ካርድ እንዲወስዱና በንቃት እንዲሳተፉ መምከርና ማበረታታት ታሪካዊ ኃላፊነታችሁ ነው።
- ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፡ የዜጎችን ንቃተ-ሕሊና ለማሳደግና ገለልተኛ የሆነ የምርጫ ትምህርት ለመስጠት የምታደርጉትን ጥረት አጠናክሩ።
ማጠቃለያ
ዲሞክራሲ ረጅም ጉዞ ነው። በሂደቱ ውስጥ ስህተቶች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ተግዳሮቶችም ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ነገር ግን እነዚህን ችግሮች ለመፍታት መፍትሔው ከሂደቱ መሸሽ ሳይሆን፣ በሂደቱ ውስጥ በንቃት በመሳተፍ ማስተካከል ነው።
የ7ኛው አገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ የዴሞክራሲ ምዕራፍ የምትሸጋገርበት ድልድይ እንዲሆን ሁላችንም የድርሻችንን እንወጣ። እምነታችንን ወደ ተግባር እንለውጥ። የምርጫ ካርድ መውሰድ ዛሬ የምናደርገው ተግባር ቢሆንም፣ ውጤቱ ግን ለትውልድ የሚተርፍ ሰላምና ብልጽግና ነው።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረትና ተሳትፎ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀው በወጣቶች እና ባህል ልማት ፋውንዴሽን (Youth and Cultural Development Foun dation – YCDF) ከአውሮፓ የምርጫ ድጋፍ ማዕከል (ECES) ጋር በመተባበር ነው። የወጣቶች እና ባህል ልማት ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ውስጥ የወጣቶችን ሁለንተናዊ አቅም በመገንባት፣ ባህላዊ እሴቶችን በማሳደግ፣ የሰላም ግንባታ ሥራዎችን በማስፋፋት እና የወጣቶችን ንቁ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ በማጎልበት ላይ በትኩረት የሚሠራ ገለልተኛ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ነው። ድርጅቱ ወጣቶች በሀገር ግንባታ ሒደት ውስጥ ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ግንዛቤ በመፍጠርና አቅማቸውን በማጎልበት የላቀ አስተዋጽዖ በማድረግ ላይ ይገኛል
