Home ነገረ ግዮን ምርጫ እና የፓርቲዎች ሥነ ምግባር

ምርጫ እና የፓርቲዎች ሥነ ምግባር

በዝግጅት ክፍሉ

ነገረ ምርጫ

ሀገራት በተለያየ ዳራዊ ታሪክ ሃገረ መንግሥታቸውን ይፈጥራሉ፡፡ አንዳንዶቹ በፍጥነት የብሔረ መንግሥት ሥራቸውን ያቀላጥፋሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ “ግዝት ወይም ግዞት” ብለው ይተኛሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ መንግሥት ወርዶ መንግሥት በተተካ ቁጥር የዜሮ ድምር ፖለቲካ ባሕል የሚኾንበት ዕድል ይፈጠራል፡፡ ነፍጥ እና ነውጥ፣ ትርክት እና ንትርክ ይገንናሉ፡፡ እንዲህ ያለው አዙሪት የሕዝብን ደህንነትም ይኹን የሀገርን ሠላም ቅርቃር ውስጥ እንዳይጥል ምርጫ የተሻለ መፍትሔ ኾኖ ይመጣል፡፡     ምርጫ አንድ ሀገር ሉዓላዊነቱን ጠብቆ ሕልውናውን ለማጽናት ቅቡልነቱ በሕዝብ የተረጋገጠ  መንግሥት የሚበጅበት ሥርዓት ነው፡፡ ይኽ ሥርዓት በስፋት የአብላጫ ድምጽ ሥርዓትን ገቢራዊ በማድረጉ አሉ ከሚባሉ መንገዶች ተመራጭ ያደርገዋል፡፡ ኾኖም ይኽ ዐይነቱ የ”ብዙኃን ይመውዕ” አካሄድ አንዳንዴ ከተሻለ ተስፋ ይልቅ ለሀገራት ምስቅልቅል መግፍኤ የኾነበት አጋጣሚም አለ፡፡ በዚህም ሳቢያ ምርጫም ኾነ ዴሞክራሲ ሂደቱ እንጂ ውጤቱ የሚደገፍ ላይኾን ይችላል የሚሉ ምሁራን አሁን አሁን ቁጥራቸው እየተበራከተ ነው፡፡     

የዓለም የምርጫ ታሪክ የቱንም ያህል ዱካው ከጥንታዊያኑ ግሪክና ሮም ይመዘዝ እንጂ “ዘመናዊ ነው” የሚባለውን የእንደራሴ ዴሞክራሲ(Representative Democracy) ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ከ17ኛው መቶ ክፍለዘመን የሚልቅ ታሪክ የለውም፡፡  የአኅጉራችን አፍሪካ የምርጫ ዕድሜም ቢኾን ግማሽ ምዕተ ዓመት የተሻገረ ዕድሜ ባይኖረውም ከተግባር ይልቅ መርኅን ፣ በስፋት ደግሞ የአምባገነኖች “ሕጋዊ” ቅቡልነት ማረጋገጫ ኾኖ እስካለንበት ዘመን ደርሷል፡፡ የሀገራችንን አጭር የምርጫ ታሪክ ደግሞ በሚቀጥሉት አንቀጾች በስሱ እንመልከተው፡፡    

ኢትዮጵያና ምርጫ

በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ጀመረ የሚባለው በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ  በ1947 ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣውን ሕገ መንግሥት መሠረት ያደረገ፣ እርሳቸውንና የላይኛውን ም/ቤት(Senate) የማይመለከት ነገር ግን የእንደራሴ ም/ቤት(Chamber of Deputies) አባላት መምረጥን በ1949 ዓ.ም አስጀምረው ነበር። የምርጫና ቆጠራውን ጉዳይ አስመልክቶ ሲሰጡ የነበሩ እማኝነቶችን ወደጎን ብንል እንኳን “ዴሞክራሲ የሂደት ውጤት” መኾኑን በማገናዘብ መሠረት የተጣለበት አንድ የታሪክ አንጓ አድርገን ልንመለከተው እንችላለን። ኾኖም ንጉሠ ነገሥቱም ኾነ በሥራቸው የነበረው የአመራር ኃይል የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደ ሕገ-መንግሥታዊ ንግሥና(Constitutional Monarchy) ቀይሮ የፖለቲካውን ሥልጣንና የሕዝቡን ተሳትፎ ማስፋት ባለመቻሉ ወታደራዊው የደርግ አገዛዝ የከፋ አንባገነንትን ይዞ ወደሥልጣን እንዲመጣ በር ከፍቷል፡፡

የደርግ ወታደራዊ ኃይል ሥልጣን ከያዘ በኋላ ኢትዮጵያ በምርጫ በኩል ያለው ታሪኳ ፍጹም ተቀይሯል፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ ሊጠቀስ የሚችለው ደርግ ራሱን የሶሻሊዝም ርዕዮት ተከታይ በማድረጉ ለፍትሓዊ ምርጫ ያለው ፈቃደኝነት ጥያቄ ላይ በመውደቁ ነው፡፡ በወቅቱ “ሕዝባዊ መንግሥት” የሚለውን መፈክር የሥማቸው ያህል የሚደጋግሙ ልዩ ልዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን በሴራና በሥራ ከመድረኩ ያስወጣበት መንገድም ሥርዓቱ በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ውስጥ ደማቅ አሻራ እንዳያሳርፍ ምክንያት ኾኖታል፡፡ ይኹን እንጂ ደርግ ሕጋዊ የፓርቲ ሥርዓትን በማስተዋወቅ ረገድ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ(ኢሰፓ)ን በመመሥረት በኩል ፈርቀዳጅ መኾኑን በመጥቀስ እንደበጎ ጅምር የሚቆጥሩለት ወገኖችም አሉ፡፡    

የቀዝቃዛው ጦርነት ማክተምን ተከትሎ ወደሥልጣን የመጣው የኢሕአዴግ አገዛዝ ግን ምርጫን በተመለከተ አዲስ መንገድ ተከትሏል፡፡ ህወሓት መሩ አገዛዝ ዓለም ወደ ዴሞክራሲ በጣም በቀረበችበት፣ በርካታ ሀገራት ወደ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ባደጉበት ዘመን ወደ ሥልጣን መምጣቱ የምርጫን ጉዳይ የማይገፋው ተራራ ኾኖበታል። በዚህም ሳቢያ በሥልጣኑ እስካረጠበት ጊዜ ድረስ አምስት ያህል ምርጫዎችን አሰናድቷል፡፡ አምስቱ ምርጫዎች በሂደት ዴሞክራሲያዊም ኾነ ነጻና ፍትሓዊ የመኾን ዕድላቸው እየኮሰመነ በመምጣቱ በሕዝብም ይኹን በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ቅቡልነት አላገኙም፡፡ በእነዚህ ሁሉ መሃል ደግሞ የበርካታ ንጹሐንን ሕይወት የቀጠፉ፣ የአያሌ ዜጎችን ቅስም የሰበሩ አጋጣሚዎች መፈጠራቸው መንግሥትም የይስሙላ ምርጫ የማድረግ ድፍረቱ እንዲበረታ፣ ዜጎችም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፈጠር ያላቸው የሰላማዊ ትግል ትዕግሥት እንዲሟጠጥና አመጽና ነውጥን ምርጫ ወደማድረግ እንዲሄዱ ገፍቷቸዋል፡፡

ስድስተኛው ምርጫ

ጭቆና የወለደው ሕዝባዊ አመጻ የቱንም ያህል መንግሥታዊ አቅሙ የደረጀ መንግሥት መፍጠር ችሏል ማለት ባያስችልም፣ ለሀገሪቱ ዘላቂ የዴሞክራሲያዊ ባሕል ልምምድና የሥልጣን ሽግግር የሚበጁ ወሳኝ ተቋማትን ለመፍጠር እርሾ ማስቀመጡን መካድ ግን የሚቻል አይመስልም፡፡ በዚህም ሳቢያ ለነጻ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ ምርጫ መካሄድ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝ የሚታመንለት ፍትሓዊ የምርጫ ተቋም እንዲኖር አንዳንድ በጎ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ በጎ እርምጃው ለቦታው አቅም ያላቸውን ግለሰቦች ከመመደብ በላይ የምርጫውን ሂደትና ውጤት በመወሰን ረገድ ልዩ ትርጉም ያላቸውን ሕጎች ከማሻሻል አንጻር የተሄደበት ርቀት ለብዙዎች ተስፋን የሰጠ ነው፡፡

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያዊያን በማንኛውም ሁኔታ ልዩነት ሳይደረግባቸው በቀጥታ እና በነፃነት በመረጧቸው ተወካዮች አማካኝነት ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ሥልጣናቸውን በተግባር ላይ ማዋል አስፈላጊ መኾንን መሠረት ስለማድረጉ የሚገልጸው “የኢትዮጵያ  የምርጫ፣ የፖለቲካ  ፓርቲዎች  ምዝገባና የምርጫ  ሥነምግባር አዋጅ ቁጥር ፩ሺ፩፻፷፪/፪ሺ፲፩” በፖለቲካ ድርጅቶችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሃሳብና አስተያየት ተሰጥቶበት ይኹንታ አግኝቶ መጽደቁ ስድስተኛውን ምርጫ ቀላል በማይባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ዘንድ ተጠባቂ እንዲኾን አድርጎታል፡፡  

የምርጫ ቦርድ ዝግጅት

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በርካታ ዓለም አቀፍና ሃገራዊ ታዛቢዎች ሊሳተፉ እንደሚችሉ አስታውቋል። ምርጫው የሚታሰብለትን ነጻና ገለልተኝነት ጠብቆ የተሳካ ይኾን ዘንድም ከ170 በላይ ለሚኾኑ የሲቪክ ማኅበራት ማመልከቻ ማስገባቱን አስታውቋል፡፡ ቦርዱ ከትግራይ ክልል ውጪ አጠቃላይ ምርጫ ለማከናወን ያግዘው ዘንድ የምርጫ ክልሎችንም ይፋ አድርጓል፡፡ እያንዳንዱ ክልል ውስጥ ለፌዴራል (የተወካዮች ምክር ቤት) መቀመጫ እና ለክልል ምክር ቤት መቀመጫ የሚመረጥባቸው የምርጫ ክልሎች እና የመቀመጫዎች ብዛት ዝርዝርንም ገልጹዋል። በዚህም መሠረት በአጠቃላይ የጊዜ ሰሌዳ በወጣለት 6ተኛው አገር አቀፍ ምርጫ 673 የምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ ይደረጋል።

ቦርዱ በምርጫ ሥርዓት፣ የድምፅ አሰጣጥ ከመጀመሩ በፊት ከሚደረገው የቅድመ ምርጫ ዝግጅት ጀምሮ ውጤቱ እስኪታወቅና ይፋ ሆኖ ለአሸናፊዎቹ የአሸናፊነት ማረጋገጫ እስከሚሰጥበት እንዲሁ ቅሬታ ካለ ቅሬታ በመስማት ሂደቱ የሚከናወንበት የድህረ ምርጫ ክንውን ድረስ ያለውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በተመለከተ “የምርጫ ዑደት” የሚል ሥም የሰጠው ዝርዝር የማብራሪያ ሰነድ አዘጋጅቷል፡፡ በሰነዱ መሠረት የምርጫ ዑደት ሦስት ዋና ዋና ክፍሎችን ያቀፈ ሲኾን፣ እነርሱም፡- 1. ቅድመ ምርጫ 2. የምርጫ ዕለት እና 3. ድህረ ምርጫ ናቸው፡፡

ቅድመ ምርጫ አብዛኛው የምርጫ እንቅስቃሴ የሚከናወንበት ወቅት ሲሆን ይህም ከምርጫ ቀን በፊት ያለውን ጊዜያት ያጠቃልላል። በቅድመ ምርጫ ወቅት የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት፣ ማቀድ እና መተግበር፣ በጀት መመደብ፣ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝግጅትና ምዝገባ፣ የምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላ፣ ሥልጠናና ምደባ፣ የምርጫ ክልል የማካለል ሥራዎች፣ የመራጮች ምዝገባ፣ ሥርዓተ ፆታ አሳታፊነት፣ የብዙሃን ማህበራት አሳታፊነት፣ የስነዜጋና መራጮች ትምህርት እና የመገናኛ ብዙሃን የሥራ እንቅስቃሴዎች በስፋትና በጥልቀት የሚሠሩበት ወቅት ነው።

በምርጫ ዑደት (Electoral cycle) መሠረት በምርጫ ጊዜ ደግሞ በርካታ ወሳኝ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡ የድምፅ አሰጣጥ፣ ቆጠራና ውጤት አገላለጽ፣ እንዲሁም የቅሬታ አቀራረብና አፈታት የተካተቱበት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከድምፅ መስጫ ቀን በፊት ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ፣ በመራጮች ምዝገባ ስለሚነሱ ክርክሮች፣ በዕጩ ምዝገባ ስለሚነሱ ክርክሮች፣ በድምፅ አሰጣጥ ስለሚነሱ ክርክሮችና ሌሎችም ጉዳዮች በዝርዝር አብራርቷል፡፡

ድህረ ምርጫ የምርጫ ወቅት የምርጫ ውጤት ይፋ ከሆነ በኋላ ቀጥሎ ያለው ጊዜ ሲሆን በዚህ ወቅት የድህረ ምርጫ ግምገማ፣ የምርጫ ክልል ማካለልና የተቋሙን ስተራቴጂካዊ ዕቅድ ዝግጅትና የመሳሰሉ ሰፋፊ ሥራዎችን የሚያካትት ነው፡፡ የድህረ ምርጫ ግምገማ በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ በየወቅቱ የሚካሄዱ ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎች በትክክለኛው መንገድ በሕገ መንግሥቱና በምርጫ ሕጉ መሠረት መከናወናቸውን ወይም አለመከናወናቸውን ለማረጋገጥ ምርጫን በገለልተኛነት ለማስፈጸም ሥልጣን በተሰጠው አካል የምርጫ ውጤት ከተገለጸና አሸናፊው የፖለቲካ ፓርቲ ከታወቀ በኋላ በመላ ሀገሪቱ የሚካሄድ የዳሰሳ ግምገማ ጥናት ነው፡፡

ይኽ የምርጫ ቦርድ “የምርጫ ዑደት” የመመሪያ ሰነድ ከቅድመ እስከ ድኅረ ምርጫው ባለው ሂደት ውስጥ ቦርዱ በቅደም ተከተል ስለሚያደርጋቸው ተግባራት የጠራ ስዕል ከመሥጠቱ በላይ ተወዳዳሪ/ተፎካካሪ ድርጅቶች ሂደቱን በጥንቃቄ እንዲከታተሉ ያመቻል፡፡ ኾኖም ከመርኅ ይልቅ ተግባር ጥያቄ ኾኖ በኖረበት ሀገር በተለይም በምርጫው ጊዜ ለሚፈጠሩ ችግሮች በድኅረ ምርጫው የሚቀርቡ ቅሬታዎችን የመፍታት አቅሙ ምን ያህል ያስተማምናል የሚለው ክፍት ኾኖ የሚተው ነው፡፡   

የሥነ ምግባር ሕጎች

ከፍ ብለን በመጠኑ ለመጥቀስ እንደሞከርነው አዲሱ የምርጫ ቦርድ እንደአዲስ ከተቋቋመ በኋላ “የኢትዮጵያ  የምርጫ፣ የፖለቲካ  ፓርቲዎች  ምዝገባና የምርጫ  ሥነምግባር አዋጅ ቁጥር ፩ሺ፩፻፷፪/፪ሺ፲፩” ጸድቋል፡፡ በዚህም መሠረት የፖለቲካ ድርጅቶቹ በቅን ልቦና እየተመሩ:- የምርጫ ሥነምግባር መርሆዎች እንዲያከብሩ፤ ምርጫ የመላው ህዝብ ነፃ እና ተቀባይነት ያለው ውሳኔ መግለጫ ሆኖ እንዲታወቅ፤ የመራጩ ሕዝብ ውሳኔ በሁሉም ዘንድ የተከበረ እንዲሆን መሥራት እንዳለባቸው በግልጽ ተደንግጓል፡፡ እንደሚታወቀው የሥነ ምግባር ሕጎች ለጤናማና ፍትሓዊ የምርጫ ውድድር ያላቸው ሚና አይተኬ ነው፡፡ በተለይ እንደኢትጵያ ያለ የተንፈራቀቀ የፖለቲካ ትንተና ያላቸው ድርጅቶች ባሉበት ሀገር መጠላላት እና ጠልፎ መጣል አካሄዶች ገዝፈው እንዳይወጡ በሕግ ልጓም የተበጀለት የሥነ ምግባር ደንብ ማውጣት አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ምርጫ ቦርድ ኹለት ጊዜ ያጸደቀው(አሻሽሎ) አዋጅ በዚህ ረገድ የሚደነግጋቸውን ነጥቦች መመልከት ጠቃሚ ነው፡፡

በአዋጁ እንደሰፈረው ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የግል ዕጩ ተወዳዳሪ:- በአዋጁ ድንጋጌዎች መሠረት መንቀሳቀስ እንዳለበት፤ መሪዎቹ፣ ኃላፊዎቹ፣ እጩዎቹ እና አባላቱ የአዋጁን ድንጋጌዎች እንዳይጥሱ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንደሚገባው፤ የፓርቲው ኃላፊዎች እጩዎችና አባላት የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች የሚጥስ ተግባር እንዳይፈጽሙ፤ ደጋፊዎቹም የተከለከሉ ድርጊቶች ከመፈጸም እንዲቆጠቡ ለማድረግ የሚያስችሉ ተገቢ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚጠበቅበት በግልጽ ተመላክቷል፡፡

የምርጫ ዘመቻ አካሄድን አስመልክቶም ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ፣ የሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ዘመቻ የማካሄድ የፖለቲካ ሀሳቦችንና መርሆዎቻቸውን ያለስጋት የማሰራጨት መብቶቻቸውን ማክበር እንደሚገባው፤ እንቅስቃሴው የሌላውን የፖለቲካ ፓርቲ፣ የመራጩን ሕዝብ እና የሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች መብቶችን ያከበረ መሆን እንዳለበት፤ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትን፤ ተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ለመራጩ ሕዝብ ያላቸውን የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ፤ እንዲሁም በፖለቲካ እንቅስቃሴ ለመሳተፍ የሚሹ የመምረጥና የመመረጥ መብት ያላቸው ዜጎች ሁሉ በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ የበኩሉን አስተዋጽዖ ማድረግ እንደሚኖርበት ተደንግጓል፡፡

አዋጁ በተጨማሪነትም ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ፣ የግል ወይም የመንግሥት ጋዜጠኞች በሙያዊ ሥራቸው ላይ እንዳይሰማሩ ማዋከብ፣ እንቅፋት መፍጠር፤ በማንኛውም ዓይነት ድርጊት የሌሎች ፓርቲዎች የምርጫ ዘመቻ እንዲስተጓጐል፣ እንዲቋረጥ፣ እንዲበላሽ፣ እንዲዳከም ማድረግና መተባበር፤ የሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም እጩ ተወዳዳሪዎች የምርጫ ማስታወቂያ፣ በራሪ ጽሑፍ ወይም ፖስተር እንዳይሰራጭ ማወክ፤ የሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም እጩ ተወዳዳሪዎች ፖስተሮችን ማበላሸት፣ ማጥፋት ወይም በሌላ በማንኛውም መንገድ እንዳይታዩ ወይም እንዳይነበቡ ማድረግ፤ ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ፣ ስብሰባ ፣የእግር ጉዞ ፣ሰላማዊ ሰልፍ እንዳያደርግ በአመራሩ፣ በአባላቱ፣ ወይም በደጋፊዎቹ አማካኝነት ማገድ፣ ማወክ፣ ቅስቀሳ ማድረግ ወይም በሌላ በማንኛውም መንገድ ማደናቀፍ፤ ማንኛውም ሰው በሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ድጋፍ ሰልፍ እንዳይሳተፍ መከልከል፤ ደጋፊዎቹ በዚህ ክፍል የተከለከሉ ማናቸውንም ተግባራት እንዲፈፅሙ መቀስቀስና ማነሳሳት እንደሌለበትም ያስቀምጣል፡፡

እነኚህንና ሌሎችንም ወሳኝ የሚባሉ የሥነምግባር ደንቦችን በአዋጁ ያሰፈረው ቦርዱ ፓርቲዎች ጤናማ ፉክክር አድርገው የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት እንዲኾኑ ይመክራል፡፡ እዚህ ጋር አዋጁ በፓርቲዎቹ ዘንድ ይኹንታ አግኝቶ መጽደቁን በማስታወስ የአፈጻጸም ጉዳዩ ምን ድረስ በትክክል ይተገበራል የሚለው ትልቅ ጥያቄ ኾኖ አሁንም ይነሳል፡፡ ቦርዱ ከኹለት ሳምንት በፊት በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች “ለጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ድጋፍ” በተባሉ ሰልፎች ላይ አንዳንድ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ሕጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ድርጅቶችን ከፍ ሲል የተቀመጡትን የሥነ ምግባር ድንጋጌዎች በጣሰ ሁኔታ የጥላቻና የፍረጃ ቅስቀሳዎችን ሲያደርጉ መደመጣቸውን ተከትሎ ያሳለፈው ውሳኔ እንደ አብነት ሊጠቀስ የሚችልና የሚበረታታ፣ ኃላፊነትን የመወጣት አንድ መንደርደሪያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡

ማጠቃለያ

ይኽም ኾኖ ኢትዮጵያ ለማድረግ ሽር ጉድ የምትልለት ምርጫ ኹሉንም የፖለቲካ ወገን ያስማማ ነው ማለት አይቻልም፡፡ አሁንም የተለያዩ ድርጅቶች ከአባላት እሥር ጋር በተያያዘ የሚያነሷቸው ቅሬታዎች ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የቀደሙት ዓይነት ወቀሳዎችና ከሠሣዎች እንዳያስተናግድ የሚሰጉ አሉ፡፡ ገና ከአሁኑም ከዕጩ ዝግጅት ጀምሮ በምርጫው እስካለመሳተፍ ድረስ ራሳቸውን እያገለሉ የሚገኙ ድርጅቶች ድምጽ እየተሰማ መኾኑ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የቱንም ያህል ካለፉት አምስት የጨረባ ምርጫዎች የተለየ ቀለም ቢኖረውም ከቅሬታ የጸዳ እንዳይኾን ግን አድርጎታል፡፡ በርግጥ እንኳንስ እንደሦስተኛው ዓለም ሀገራት የዴሞክራሲ ዳዴ፣ ኃያላኑ ሀገራት ዘንድም ፍትሓዊ ምርጫ ተሰርቶ ያላለቀ ተግባር መኾኑ ነገሩን ሊያመቻምቸው ይችል ይኾናል፡፡ ይኹንና በኢትዮጵያ የዘውግ ፖለቲካ ተዋስዖ በስፋት መግነኑን ተከትሎ ድኅረ ምርጫው እንዲኖር ከሚፈለገው ውጤት አንጻር በሂደቱ ሊኖር የሚችለው አሰላለፍ በራሱ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳይዝ መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡  አንዳንድ ችግሮች ተንከባላይ ዕዳ ኾነው አሁንም የመጪው ትውልድ ፈተና እንዳይኾኑ ቦርዱ ታሪካዊ ኃላፊነቱን አብሮ ማሰብም ይጠበቅበታል፡፡ ሠላም!