መግባቢያ
በአሁናዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተዋስዖ ሁነኛ ጉዳይ ነው፡፡ የውይይቶቹ፣ የመድረኮቹ ጭብጥ ከዚህ ንፍቀ ክበብ ፈቅ ሲሉ አይታይም፡፡ በርካታ ወገኖች መብት ከዜግነት መቀዳት አለመቻሉ የወለደው ችግር አድርገውም ይቆጥሩታል፡፡ የታሪክን ጉዳይ! ታሪክ በጽንሠ ሃሳባዊ ብየናው ‘የሁነቶች ቅደም ተከተል’ የሚል ማፍታቻ ይሰጠዋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ፣ ሀገር የተገመደችበትን ውል ለመበጠስም ይኹን የታነጸችበትን ሲሚንቶ በዶማ ለመቆፋፈር የሚጋጋጡ “የፖለቲካ ሳይንቲስቶች” ባሉበት ይኽ ዐይነቱ ብየና ወንዝ የሚያሻግር አይመስልም፡፡
በታሪክ ተጸንሶ፣ በታሪክ ተወልዶ፣ በታሪክ አድጎ፣ በታሪክ ጎልምሶ ዛሬ በደረሰ ፖለቲካ ‘ታሪክ የሁነቶች ቅደም ተከተል ነው’ የሚለው ትርጉም አያጠረቃውም፡፡ በዚህም ምክንያት ሕገ መንግሥት፣ የግዛት አሃዶች(ክልሎች) እና የሥልጣን መዋቅሩ ታሪክን መሠረት አድርጎ ሊፈጠር(ሊዋቀር) ችሏል፡፡ “…መጪው የጋራ ዕድላችን መመሥረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረም…” የሚለው ሕገ መንግሥታዊ መቅድምም የዛሬው የኢትዮጵያ እውነታ በታሪክ ሰንሰለት ምን ያህል እንደተቀየደ ማሳያ ነው፡፡
“መግባቢያ” የሚል ንዑስ ርዕስ በሰጠነው በዚህ ክፍል ስለታሪክ መፈትፈት የፈለግነው እንበለ ምክንያት አይደለም፡፡ ዓቢይ ርዕሳችን እንደሚናገረው የጠፋብንን ግን ደግሞ የሚያስፈልገንን “ብሔራዊ ትርክት” ለማዋለድ እንዲያመቸን ያስቀመጥነው እርካብ ኾኖ እንጂ፡፡ ብሔራዊ ትርክት (National narrative) የሚወለደው ከታሪክ ነው፡፡ የእኛ ከኾነው፣ የ”እኛ” ብለን ከምንጠራው የትናንት ታሪካችን፡፡ በመኾኑም ታሪክን ለዛሬ እኛነታችን ጥቅም ላይ የምናውልበት ስልትን ጠንቅቆ ማወቅ እንጂ ከታሪክ የተነጠለ ሃገረ መንግሥት ይዞ መቀጠል ለየትኛውም ብሔረ መንግሥት አስቸጋሪ እንደኾነ መገንዘብ ጠቃሚ ይመስላል፡፡ እዚህ ጋር አንድ መከራከሪያ ሲጠቀስ ይደመጣል፡፡
በአንድ ወቅትም የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ፤ መከራከሪያውን አምነውበት ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡ ጭብጡ “አብሮ ለመኖር ታሪክ ምንም ነው” የሚል ነው፡፡ ም/ርዕሰ መስተዳድሩ በአንድ ዲስኩር ባሰሙበት መድረክ የተናገሩትን ቀጥታ መጥቀስ ተገቢነት ሳይኖረው አይቀርም፡፡ “…በዚህች ሀገር ብሔራዊ መግባባትና አንድነት እንዳይመጣ እያደረጉ ካሉ ነገሮች አንዱ በታሪክ ዙርያ ያለው ውዝግብ ነው፡፡ በኃይማኖቶቻችን፣ በባህሎቻችን፣ ወዘተ… ዙርያ በመካከላችን መቻቻል፣ መግባባት አለ:: በታሪካችን ዙርያ ግን ይኽ የለም:: በታሪክ ላይ መነታረክ አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም፡፡ አብሮ ለመኖር በታሪክ መስማማት የግድ አይደለም፡፡”
ይኽ ሃሳብ የመጠፋፋት ቋፍ ላይ ለቆመው ታሪካችን የዋህ (Simple) ማመቻመች ሊባል ይችላል፡፡ “አንተም ተው፣ አንቺም ተዪ” ዓይነት እሳቱን የማጥፋት ሳይሆን እቶኑን የመሸሽ ምክረ-ሃሳብ ሊኾን ይችላል፡፡ “ሳይራመድ በታሪክ ምንጣፍ ሰው አይደርስም ከዛሬ ደጃፍ” እንዳለው ከያኒ ሆኖ ግን ታሪክ የትናንት ፖለቲካ ቅሪት በመሆኑ፤ የዛሬያችንንም የነጋችንንም ፍኖት የሚቀይስበት ወሳኝ ሚና እንዳለው በአቶ ሙስጠፌ ንግግር ብዙም ከግምት የገባ አይመስልም፡፡
በታሪካችን ላይ ያለው ምንታዌ(Dualism) ዲስኩር በ”አጥፊ” እና “ጠፊ” ላይ የተቸነከረ መሆኑ የቀደሙ መንግሥታትን በጥንካሬና ድክመታቸው ልክ አስልቶ ሚዛናዊ ለመሆን የቸገረበት ዘመን ላይ አድርሶናል። ይኽ አዎንታዊ አካሄድ ቦታ ያጣው ደግሞ ታሪክ ለዛሬና ነጋችን ትርጉሙ ትልቅ መሆኑ በሁለቱም ወገን በመታመኑ ይመስላል፡፡ በርግጥ ይኽ ታሪክ ላይ ክችች ያለ አተያይ አሁን አሁን ለዘብ ያለ ቢመስልም፣ አንድን ሥርዓተ መንግሥትና መሪውን በፍትሐዊ የታሪክ ሚዛን ለመዳኘት ችግር ሆኖ ጽልመቱ ብቻ ለአንድ ወገን ፤ አብርሆቱ ብቻ ደግሞ ለሌላው ወገን መታየቱ መግፍዔው ምንም ይሁን ምን ታሪክ ለዛሬ እውነታችን ትርጉሙ ትልቅ መኾኑን ያሳያል፡፡
ታዲያ ብሔራዊ ትርክት ምንድነው?
ከፍ ሲል በመጠኑ ለመጠቆም እንደሞከርነው የዛሬው ዓቢይ ጉዳይ ብሔራዊ ትርክት “National narrative” በመፍጠር ዙሪያ የሚያተኩር ነው፡፡ ከአንድ ሳምንት በፊት በሰላም ሚኒስቴር “ብሔራዊ መግባባት፣ ለዘላቂ ሰላምና ሀገር ግንባታ” በሚል በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ይኽ አጀንዳ ወደፊት መጥቷል፡፡ በጽንሠ ሃሳቡ ዙሪያም በምሑራን ንድፈ ሃሳባዊና ተጨባጭ ማሳያዎች ቀርበው ለመወያየት ተሞክሯል፡፡ በመድረኩ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ አበባው አያሌው ብሔራዊ መግባባትን እና ሀገር ግንባታን በማሰናሰል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ውስጥ እያንዳንዱ ሃገር የራሱ ብሔራዊ ትርክት እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ብሔራዊ ትርክት የሁሉም ታሪኮች አካታች ጥቅል አላባ መኾኑን በማንሳትም ጠቃሚና የጋራ ከነበሩ የአብርኾት ታሪኮች በመነሳት ብሔራዊ ትርክትን መፍጠር ይቻላል ብለዋል፡፡
ስለብሔራዊ ትርክት “National narrative” የጻፉ ምሁራን እንደሚያነሱት ብሔራዊ ትርክት የ“ማህበራዊ ትርክት” ዐይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ ማኅበራዊነቱ የሚገለጸው ደግሞ በትናንት ውስጥ የነበረን የማኅበረሰብ አስደናቂ ታሪክ የማንነት መለዮ አድርጎ የሚያቀርብ በመኾኑ ነው፡፡ ብሔራዊ ትርክት በሌላ መልኩ ማፍታቻ የሚሰጡትንም አላጣም፡፡ በዚህም መሠረት ‘በአንድ ቡድን(ወገን) የተያዘና ስለዚያ ቡድን በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የሚነገር ተረክ ማለት’ ሊኾን ይችላል፡፡ የአንድ ሀገር ቀደምት እውነታዎች ተምኔታዊም(Ideal) ተውኔታዊም(Dramatic) በኾኑ ታሪኮች እየተጀቦኑ ሲቀርቡ ወደብሔራዊ ትርክትነት የማደግ ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ እንደነዚህ ያሉት ተረኮች ለብሔራዊ ማንነቶች መሠረት መኾናቸው ስለሚታመንበት በበርካታ ሀገራት መንግሥታት ዘንድ “ሕጋዊ” ተደርገው ይደገፋሉ፡፡ በሥነ-ጽሑፋዊ ሥራዎች እንዲህ ያሉትን “ብሔራዊ ትርክቶች”፣ “ብሔራዊ ማንነት” አድርጎ ለመፍጠር ስለሚያግዙም በእጅጉ ይበረታታሉ፡፡ በዚህ ረገድ ሀገራት ተጨባጭ የታሪክ ማስረጃ ከሚገኝላቸው ታሪኮች በላቀ አፈ-ተረኮች(Mythologies)ን ጥቅም ላይ ሲያውሉ ይታያሉ፡፡ ግሪክ፣ ኢጣሊያ፣ ሕንድና የሩቅ ምሥራቅ ሀገራት በዚህ ረገድ በስፋት ይጠቀሳሉ፡፡
የ“ትርክቶች”ን ባሕሪ አስመልክተው የሚጽፉ ሌሎች ምሁራን እንደሚሉት አንድ ትርክት መሠረቱ የቱንም ያህል ከእውነት ይቀዳ/አይቀዳ የሀገሪቱ ዜጎች ያንን እውነታ ማንጸባረቅ ሥነአእምሯዊ ግዴታ ውስጥ ይገባሉ፡፡ በሌላ አገላለጽ ብሔራዊ ትርክቶች ሁልጊዜም በግልጽም ኾነ በተዘዋዋሪ የማኅበረሰቡን የወደፊት ሁኔታ የሚያመለክቱ በመኾናቸው፣ ስለትናንት ከሚፈጥሩት የመመካት(Boasting) ስሜት በላቀ በወደፊቱ ፖለቲካ ላይ ያላቸው ሚና ጥልቅ ነው፡፡ በመኾኑም ዜጎች በሀገራቸው አዳዲስ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች ብሎም ሕገ መንግሥት ሲረቅና ሲወጣ በምን ምክንያት መደገፍ/መቃወም እንደሚገባቸው ብሔራዊ ስንቅ በመኾን ያገለግላቸዋል፡፡
የብሔራዊ ትርክት ባሕሪ
ብሔራዊ ትረካዎች ከጊዜ በኋላ ሊለወጡ ይችላሉ፡፡ በሌላ አማርኛ ዶግማዊ ስሪት የላቸውም፡፡ የመዳበር፣ የመሻሻል፣ የመጨመር ባሕሪያት አሏቸው፡፡ ለዚህ ባሕሪ ክሱት መኾን ምክንያት የሚኾነው ደግሞ የሃገራቱ ሥሪት ነው፡፡ የግዛት መጥበብና መስፋትን ተከትሎ የአንድ ወገን የበላይነት የሚስተዋልባቸው ሥርዓተ ማኅበሮች ከነበሩ ብሔራዊ ትርክቱን አካታች ማድረግ አስፈላጊ ይኾናል፡፡ በተለይም ባሕውርታዊ ሕዝብና መንግሥት ባላቸው ሀገራት የየማኅበረሰቦቹ የታሪክና የማንነት መረዳቶች መኖር ነባር የነበረውን ብሔራዊ ትርክት ማስተካከል ወሳኝ ሊኾን ይችላል ፤ እንደ ምሑራኑ አስተያየት። በዚህ ረገድ ተጠቃሽ የኾኑ ሁለት የብሔራዊ ትርክት ምሰሶዎች አሉ፡፡ እነርሱም “ነፃነት” እና “አንድነት” ናቸው፡፡ እነኚህ ንባበ-ቃላት ለአብዛኛው ሕዝብ ትርጉማቸው ጥልቅ ነው፡፡ ከሰው ልጅ ባሕሪ አኳያም ነጻነትን መሻትም ይኹን በጋርዮሽ የመኖር ባሕል ወሳኝ ናቸው፡፡ ነገር ግን ንባበ-ቃላቱ ወጥ የኾነ ብየና ስለሌላቸው ግንዛቤ ላይ የሚፈጥሩት አሻሚነት ግልጽ ነው፡፡
ለአንድ ሀገር ኅላዌ በሚገነባ ብሔራዊ ትርክት ውስጥ “ነጻነት” እና “አንድነት” ያላቸው ግዘፍ የሚነሳ ትርጉም ብቅ የሚለውም እዚህ ጋር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ለእነኚህ ወሳኝ ጽንሠ ሃሳቦች “ስልታዊ ትርክት” (strategic narratives) ማጎናጸፍ የግድ ይኾናል፡፡ በሌላ በኩል ሀገራት የሥነ ሕዝብ አወቃቀራቸውን፣ የሕብረተሰብ ዐይነታቸውን እና ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላቸውን ግንኙነት (ፌዴሬሽን፣ ኮንፌዴሬሽን) ሲለውጡ ብሔራዊ ትርክቶቻቸው ሊለወጡ፣ ሊረሱ ወይም ሊጨመሩ ይችላሉ፡፡ ይኽም የብሔራዊ ትርክት አንድ ባሕሪ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ቤኔዲክት አንደርሰን የተባለ ጸሐፊ አንድን ሀገር “ተምኔታዊ የፖለቲካ ማኅበረሰብ” (an imagined political community) ሲል ይጠራዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አንዳንድ ሀገራት በሥራቸው ያሉትን ወይም አጠገባቸው ስለሚኖሩት ሕዝብ ያላቸው የየራሳቸው መረዳት(ስዕለ ኅሊና) ካልኾነ በስተቀር ተጨባጭ እውነታን መሠረት ያደረገ ባለመኾኑ ነው፡፡ በእኛም ሀገር አንዳችን ለአንዳችን ያለንን ስዕል አስመልክቶ የሚነሱና የሚጣሉ ሃሳቦች እንዳሉ አቶ የሱፍ ያሲን “ኢትዮጵያዊነት፤ አሰባሳቢ ማንነት በአንድ ሀገር ልጅነት” በሚል ርዕስ በሰየሙት መጽሐፋቸው ጠቅሰውታል፡፡ አንድ ማኅበረሰብ ጎረቤቱ ላለው ሌላ ማኅበረሰብ የሚኖረው ስዕል የተለያዩ አጋጣሚዎችን የተንተራሰ ነው፡፡ በስፋት ደግሞ በጦርነት ላይ ባላቸው ሚና፣ በአመጋገብ፣ አኗኗር፣ ምሑራዊ እውቀት ወዘተ… ላይ ያጠነጥናል፡፡ እነኚህ የሩቅ ተመልካችነትን በአብዛኛው ደግሞ ግምትን መሠረት በሚያደርጉ መረዳቶች የተለያዩ ትርክቶች የመፍጠር ዕድል ይኖራቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ብሔራዊ ትርክት በመፍጠር ሂደት ውስጥ መታረም ፣ መስተካከልና መቀነስ የሚገባቸው ልዩ ልዩ ተረኮች የሚኖሩት፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ትርክት ምንድነው?
ከፍ ብለን ለማስቀመጥ ከሞከርነው ንድፈ ሃሳባዊ አባሪዎች ተነስተን መጠየቅ ያለብን ጥያቄ ይኽ ነው፡፡ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ትርክት ምንድነው?” ጥያቄው በተለያዩ ምሑራን ዘንድ ምላሽ ለመሥጠት መፍጨርጨር የሚደረግበት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከፍ ብለን የጠቀስናቸው ምሁር (አቶ አበባው አያሌው) ዓድዋን እንደ አንድ ብሔራዊ ትርክት ይቆጥሩታል፡፡ በርግጥም ዓድዋ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ትርክቶች የተሻለ ቅቡልነት ያለው ተረክ ነው፡፡ በዓድዋ ውስጥ የሚተነተኑ ዝርዝር አላባዎች(Elements) ደግሞ ይበልጥ አካታች መኾን አለመኾናቸውን ለመመርመር ዕድል ሰጪ ነው፡፡ በዓድዋ ውስጥ ተደጋግሞ እንደሚነገረው አይበገሬነት፣ ጀግንነት፣ እልኸኝነት፣ ድል አድራጊነትና ተያያዥ ጉዳዮች የኢትዮጵያዊያን መለዮዎች ተደርገው ይገለጻሉ፡፡ አሕመድ ዘካሪያ የተባሉ የሀገራችን ምሁር እነኚህን ባሕሪያት(አላባዎች) ለይቶ በማጥናት “የተራራ ላይ ሕዝብ” ብለው ለመጥራት ተገድደዋል፡፡ በዓለማችን የኢትዮጵያ ዐይነት መልክዐምድራዊ አቀማመጥ ባላቸው ሀገራት ሕዝቦች ዘንድም ይኽ ዐይነቱ ባሕሪ ጎልቶ ይታያል ከሚል መነሻ የሰጡት ስያሜ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የባዕድ ወራሪያንን እንቅስቃሴ ለመግታት በተደረገው ፍልሚያ(በተለይም በዓድዋ) ኢትዮጵያዊያን ከጫፍ ጫፍ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በውጤቱም ድል አድራጊ ኾነዋል፡፡ በርግጥም ይኽን ሀቅ ሀገራዊ አንድነት የራቃት በምትመስለው የዛሬዋ ኢትዮጵያ በርካታ የዘውግ ፖለቲካ አቀንቃኞች ሳይቀሩ የሚጋሩት ነው፡፡ እያንዳንዷ እንቅስቃሴ የፖለቲካ ምንዛሬ በማታጣበት የዛሬው ዘመን ዓድዋ በየዓመቱ የካቲት 23 ሲዘከር የሚሰማ አንድም ተቃውሞ አለመኖሩም ሌላ ማጠናከሪያ ይኾናል፡፡ ዓድዋ ብሔራዊ ትርክታችን በመኾኑ ረገድ ኢትዮጵያን በሚያህል ግዙፍ ሀገር ሌሎች አግባቢ ትርክቶችስ በምን ያህል አሉ የሚለው ጥያቄ ወደፊት ይመጣል፡፡ ዛሬ ዛሬ አፍአዊነታቸው ሚዛን የደፋ ቢመስልም “እንግዳ ተቀባይነታችን፣ በጋራ ማዕድ መቁረሳችን፣ ሃይማኖተኛ ሕዝብነታችን፣ የራሳችን ፊደል ባለቤት መኾናችን…” መልስ ኾኖ ሊመጣ ይችላል፡፡ የብሔረ መንግሥት ግንባታን በማሳለጡ ሂደት ብሔራዊ ትርክትን በመፍጠር በኩል ደካማ የመኾናችን እውነታ ቁልጭ ብሎ የሚታየውም እዚህ ጋር ነው፡፡
ለአብነት የገዳ ሥርዓት የዓለም ቅርስ ተብሎ ቢመዘገበም የኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ ትርክት አካል ሊኾን አልቻለም፡፡ “ነጭን ያንበረከክን” የሚለው መፈክር ያህል “ዴሞክራሲን ለዓለም ያስተዋወቅን” የሚል ኩራት አይሰማም፡፡ ይኽ ለመኾኑ አያሌ ምክንያቶችን መደርደር ይቻል ይኾናል፡፡ መሠረታዊው ጥያቄ ግን ከፍ ሲል የብሔራዊ ትርክት “National narrative” ባሕሪ ብለን ከጠቃቀስናቸው ጉዳዮች አኳያ “ነባር” አድርገን ከያዝነው ተረክ በተጨማሪ አዳዲስ ትርክቶችን በመፍጠር ብሔራዊ ማንነት የማጎልበት ውጥናችን ደካማ መኾኑን ያሳየናል፡፡ በርግጥ ይኽ ላለመኾኑም የሚደረደሩ አመክንዮዎች ላይጠፉ ይችላሉ፡፡ ደረጃችንና የብሔረ መንግሥት ግንባታችን (Nation Building) ያሉበትን ሽንቁሮች ለመታዘብ ግን ዕድል ሰጪ ነው፡፡ ብሔራዊ ትርክቶች መከራ ለኾነብን ብሔራዊ መግባባት ያላቸውን ፋይዳ ለመገንዘብ ደግሞ ወረድ ብለን እንመልከት፡፡
ብሔራዊ ትርክት ለብሔራዊ መግባባት?
ዶ/ር አየለ በክሬ የታሪክ ተመራማሪና መምሕር ናቸው፡፡ ከፍ ሲል በጠቀስነው የሰላም ሚኒስቴር መድረክ ብሔራዊ መግባባትን በሀገራችን ለማምጣት በሚያስችሉ መሠረቶች ዙሪያ በርካታ ሃሳቦችን አንስተዋል፡፡ በእርሳቸው እምነት ለአንድ ሀገር ብሔራዊ መግባባት ፍትሓዊነት፣ እኩልነትና ግልጽነት እጅጉን ያስፈልጋሉ፡፡ ሀገራዊ ትርክትን በማዋለድ ሂደት ውስጥ የእነኚህ ሦስት ጉዳዮች ወሳኝነት ብቅ የሚለውም እዚህ ጋር ነው፡፡ ትርክትን ከፍትሓዊነት አንጻር ከቃኘነው ኹሉንም ወገን ሊያስማማ የሚችለውን ወደፊት የማምጣት ጉዳይ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ በዚያ ብሔራዊ ትርክት(ቶች) ውስጥ የትኛውም በሃገረ መንግሥቱ ሥር ያለ ማኅበረሰብ ራሱን መመልከት የሚችልበት ዕድል ከተፈጠረ ደግሞ የእኩልነቱን ጥያቄ በምልዓት ይመልሰዋል፡፡ ግልጸኝነት አስፈላጊ የሚኾነው ደግሞ ከእያንዳንዱ ብሔራዊ ትርክት ዓላማ አንጻር የተቃኘ ስለሚኾን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ትርክቶቹ የብሔረ መንግሥት ግንባታውን ከማሳለጥ ትልም አንጻር የሚቀመሙ በመኾናቸው መግባባት ያስፈልጋቸዋል፡፡ መግባባቱ የሚጀምረው ደግሞ ስለእያንዳንዱ ትርክት በሕዝብ ዘንድ ግልጸኝነቱ በሰፊው ሲኖር ነው፡፡
ከኢትዮጵያችን እውነታ አኳያ ነገሩን እንመልከተው፡፡ ብሔራዊ ትርክቶችን የማዋለድ ሂደቱ ብዙ እንደሚቀረው ከፍ ብለን ጠቁመናል፡፡ ፖለቲካዊ ጽንፈኝነቱ ደግሞ ተጋግሞ ወደመጠላላት ደርሷል፡፡ የኢትዮጵያን ኅላዌ ለማስጠበቅ በሚደረገው ትግል ውስጥ እነኚህን የተንፈራቀቀ የሚመስል የፖለቲካ ልዩነት ያላቸውን ኃይሎች ወደ ብሔራዊ መግባባት ማምጣት ደግሞ ወሳኝ ተግባር ነው፡፡ በዚህ ረገድ አዲሱ የገንዘብ(ብር) ኖት ላይ የተደረገው አካታች ተግባር ለብሔራዊ መግባባት ያለው ፋይዳ በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ “የጋራ ታሪክ የለንም” የሚል ነጣጣይ ፕሮፓጋንዳ የተዋስዖ አየሩን ሰቅዞ በያዘበት ሀገር ብሔራዊ ትርክት በበቂ ሁኔታ አለማዋለድም ኾነ የተዋለዱትን ተገቢውን ቅቡልነት እንዲያገኙ አለመታተር አዳዲስ ችግሮች የመፈብረክ ዕድሉ ትልቅ ነው፡፡ የመነጠል ስሜቶችን፣ የባዕድነት ሀቲቶችን የመጎተት ኃይሉም ቀላል አይደለም፡፡ ብሔራዊ ትርክት ለብሔራዊ መግባባት ያለው ሚና ግዙፍ ነው የሚባለውም ከዚህ አኳያ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከመንገዱ፣ ከት/ቤቱና ከጤናው ሴክተር እኩል መሥራት የሚገባን የቤት ሥራም ይኽ ነው፡፡
ማጠንጠኛ የሃሳባችንን ማጠንጠኛ ወደአንድ ታሪክ ክፍል እንገፋዋለን፡፡ በኢትዮጵያ የታሪክ ትምህርት ውስጥ የፖለቲካ ታሪክ መግነን ብሔራዊ ትርክት የማዋለዱን ሂደት ዳገት እንዳደረገው መከራከሪያ የሚያቀርቡ ምሁራን አልጠፉም፡፡ እንደምሁራኑ እምነት የባሕል ታሪካችን በልኩ አለመጻፉና በትምህርትነት አለመሰጠቱ ያጎደለው ብዙ ነው፡፡ በርግጥም በበርካታ ሀገራት ብሔራዊ ትርክቶች የሚቀዱት ከሕዝቦች ባሕላዊ ታሪክ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የበርካታ ባሕል ባለቤት ሕዝቦች ሙዚየም መኾኗ ተደጋግሞ ይገለጻል፡፡ እውነት ነው፡፡ የተለያዩ ማኅበረሰቦችም አንዳችም የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ጣጣ ሳይጫናቸው ባሕሎቻቸውን፣ አልባሶቻቸውን፣ ምግብና አመጋገባቸውን ተወራርሰዋል፡፡ ለአብነት ጋቢ በሰፊው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ዘንድ የጋራ ልብስ ኾኗል፡፡ እንጀራ የሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ብሔራዊ ምግብ ኾኗል፡፡ ሌላም ሌላም… ብሔራዊ ትርክትን እንዴት እንፍጠር የሚለው ጥያቄ ምላሽ በባሕል ታሪክ ዙሪያ የሚሽከረከረውም ለዚህ ነው፡፡ የባሕል ታሪክ አንድ የታሪክ አላባ ነው፡፡ ስለባሕል ታሪክ ወደፊት በሰፊው የምንለው ይኖራል፡፡ ሰላም!
