Home ምልከታ ሥልጣን ልቀቅ ሥልጣን እንንጠቅ!!!

ሥልጣን ልቀቅ ሥልጣን እንንጠቅ!!!

ሥልጣን ልቀቅ ሥልጣን እንንጠቅ!!!

ከወርቁ ተስፋዬ

ከአንድ ወር እረፍት በኋላ የተመለሱት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፓርላማ አባላት ማክሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም በሚያደርጉት መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር በፓርላማው ስብሰባ ከማድረጋቸው በፊት በዚህች የገዥው ፓርቲ ሆነ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጉድፍ ጠራጊ በሆነችው ‹‹ግዮን›› መጽሔት ላይ ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም ‹‹ይድረስ ለክቡር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)›› በሚል ርዕስ ሰፋ ያለ መጣጥፍ ማቅረቤ ይታወቃል፡፡

      በመሆኑም እንዳቀረብኩት መጣጥፍ ሁሉም የገዥው ብልጽግና ፓርቲ የምክር ቤት ተመራጭ የሆኑ የፓርላማ አባላት ተወካዮች ሳይቀር በእለቱ በተለያየ ቅርጽ በተለያየ አገላለጽ ሀገርን ክዳችኋል፣ ሕዝብን ክዳችኋል፣ ዜጎች በነፃነት ሰርተው የመኖር የመንቀሳቀስ ገደብ እየተጣለባቸው ነው፡፡ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ዜጎች ይታሰራሉ፡፡ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እየተደበደቡ፣ እየታሰሩ፣ እየተገደሉ ይገኛሉ፡፡ ቤታቸው እየፈረሰ፣ ሀብትና ንብረታቸው እየወደመ ነው፡፡ ውስን ቁጥር ያላቸው ማንነቶችን ደፍጥጣችሁ ከምድር ገጽ እያጠፋችሁ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ምን እየሰራችሁ ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ ወድቋል የሚል የተለያየ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡

      በዚሁ መሰረት በተለይም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ከፍተኛ አመራር ውስጥ ካሉት አንዱ የሆኑት፣ ነገር ግን ለመረጣቸው ሆነ ለወከላቸው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም የኢትዮጵያዊያን ድምጽ ጭምር በመጠየቅ የሚታወቁት የፓርላማው አባል የተከበሩ ክርስቲያን ታደለ በዚህ የፓርላማ ስብሰባ ላይ ‹‹ጥያቄን ሳቀርብ ብሔሬን ወክዬ አይደለም፤ የሚወክሉትንም ብሔር በመጥላት አይደለም፤ ለጥያቄዬ ምላሽ እና ማብራሪያ ሲሰጡኝም ብሔርዎንና ምንአልባት የመንግሥት ግልበጣ ሴራ ነው የሚል ጥርጣሬ እንዳያድርብዎት ከወዲሁ አደራ እላለሁ›› የሚል የቅድሚያ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

አስከትለውም ‹‹የአስፈፃሚ የመንግሥት ኃላፊነትዎን ስላልተወጡ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣንዎትን በመልቀቅ የመፍትሄ አካል ለመሆን አላሰቡም ወይ?›› የሚል ጥያቄ በማቅረባቸው ለተጠየቁት ጥያቄ የምክር ቤቱን ክብር እና ሞገስ በሚያሳጣ የብስጭት ስሜት አሳዛኝና አሳፋሪ ምላሽ ከመስጠት አልፈውና ተርፈው ‹‹እኔ ከለቀኩ አብረን እንለቃለን…›› የሚል ሕጋዊ መንግስታዊ ስርአትን ባልተከተለ የማደናገሪያ ምላሽ ከመስጠት በተጨማሪ በአንድ ወቅት ስንኖር ኢትዮጵያ ስንሞት ኢትዮጵያዊ ነን፡፡ እኛ እያለን ኢትዮጵያ አትፈርስም እያሉ በዚህ የጉባኤ የስብሰባ መድረክ ላይ ያውም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉባኤ በኢትዮጵያ ሕዝብ እንደራሲዎች ፊት በቤታችን ሁነን ከአዛውንት እስከ ህፃናት ጭምር በርካታ ወገኖች በቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት በምናዳምጥበት ጊዜ እውነተኛ መልካቸውን የገመና እርቃናቸውን በሚያስቀር ‹‹ኢትዮጵያን ማፍረስ ከፈለግን ከልካይ የለብንም፡፡ በአለም ላይ ከማፍረስ የሚያቆመን ሀይል የለም፡፡›› የሚል እብሪት የታከለበት ንግግር ማድረጋቸው እውነትም ዛሬ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ በራሳቸው ውሳኔ የተንጠለጠለ እንደሆነ የፓርላማው ምክር ቤት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አለቃ መሆኑን እየታወቀ ከእሳቸው በታች ጥርስ የሌለው የወረቀት ላይ አንበሳ እንደሆነ ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ የሚል እጅግ አነጋጋሪ የሆነ ደረጃ ደርሰዋል፡፡

በእርግጥ እዚህ ደረጃ ለደረሱበት ዋናው ምክንያቶች የሚኒስትር ካብኔዎቻቸውን እንደፈለጉ እንደሸሚዝ ሲቀያይሩ ከማጽደቅ በፊት የተሻሩትንም ቢሆን ፓርላማ ፊት ቀርበው እንዲያስረዱ በማድረግ ውሳኔአቸውን ቢገድቡ ኖሮ የፓርላማውን ስልጣን እና አለቅነት በመገንዘብ ሁሉም በእጄ ሁሉም በደጄ አይሉም ነበር፡፡

      ይህ ባለመሆኑ ነው በቅርቡ የሕግ ተቋማት በፖለቲካ ወይም በዘር አመለካከት ሲፋለስ አይተው እንዳላዩ መሆን የማይሹት የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዜዳንት ከምክትላቸው ጋር በፍቃዳቸው የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸው ተገልፆ በምትካቸው ሌላ የተሾሙት፡፡ እነሱን ተከትለውም የዳኝነት ነፃነት ብቻ ሳይሆን ተጠያቂነትም ባለመኖሩ ምክንያቶች የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዜዳንት ከምክትላቸው ጋር የስራ መልቀቂያ ያስገቡት፡፡

ከዚህ በፊትም ሰኔ 16 ቀን በመስቀል አደባባይ በመገኘት ድጋፋቸውን ለመግለጽ በታደሙበት ጊዜ በተሞከረባቸው የግድያ ድግስ ተረባርቦ በመቁሰል፣ በመድማት የሕይወት መሰዋዕትነት በመክፈል የታደጋቸውን ሕዝብ በተመሳሳይ ሁኔታ በፓርላማ እንደራሲዎች ፊት ‹‹የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ኦሮሞ ጠል ናቸው›› የሚል የዘር ፍጅት የሚያነሳሳ ቅስቀሳ ቢያደርጉም አስተዋዩ የአዲስ አበባ ሕዝብ ሆነ አቃፊ የሆነው የኦሮሞ ሕዝብ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ሁሉንም ቻይ ለሆነው ፈጣሪው አምላክ በመስጠት ባያሳልፈው ኖሮ በከተማዋ ውስጥ እንደ አፍሪካዊቷ የሩዋንዳ ሀገር የዘር ፍጅት እንዲቀጣጠል አድርገው ነበር፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርብ ሰው እና የውጭ ጉዳይ አማካሪያቸው አቶ አዲሱ አረጋ፣ በፓርላማው በቀረበው ጥያቄ መሠረት እንዴት ቢንቁን እንዴት ቢደፍሩን በሚል ትምክተኝነት በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት የኦሮሞ ተወላጅ ብቻ የሆነ ይመስል ‹‹ስልጣን ልቀቅ ስልጣን እንንጠቅ›› የሚል የአማራ ፖለቲከኞች የጠቅላዩን ስልጣን የመንጠቅ ፍላጎት እንዳላቸው በማስመሰል በሀገሪቱ ውስጥ እርባና ቢስ በሆነ ንግግር በኦሮሞ ክልል ነዋሪ የሆኑትን በማነሳሳት ሰላማዊ ሰልፍ እንዲወጡ በማስደረግ የዘር ፍጅት እንዲቀጣጠል አዋጅ አውጀዋል፡፡

ይሁንና እሳቸው በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ዘርፍ ኃላፊ በነበሩበት ጊዜ ወለጋ ላይ እናት በጥይት በተገደለ ልጃቸው አስክሬን ላይ እንዲቀመጡ የተደረገበት፣ ወጣቶች እስናይፐር ከታጠቁ ወታደሮች ጋር እየተናነቁ በሚወድቁበት ጊዜ ‹‹ወጣቶቻችን በልማት ላይ ናቸው›› የሚል የትውልድ አሳፋሪ መግለጫ የሰጡ ናቸው፡፡

የኦሮሚያ ክልል ም/ፕሬዘዳንት በነበሩበት ጊዜም የኦሮሞን ማኅበረሰብ ከጥቃት ያዳኑበት ጊዜ አልነበረም፡፡ እንዲያውም በሳቸው የስልጣን ዘመን ወጣቶችን በጅምላ በማስጨፍጨፍ በየእስር ቤቶች የሚማቅቁበት የደም መሬት አድርገዋል፡፡

ዛሬም በአሉበት የስልጣን ቦታ ላይ ሆነው የቁጭት የበታችነትና የበቀል ስሜት ከተጠናወታቸው የታሪክ ምርኮኞች ጋር ሆነው ለፍትህ፣ ለዲሞክራሲ፣ ለእኩልነት ፣ለነጻነት የሚታገለውን ከማንኛውም ኢትዮጵያዊያን ጋር በአምቻ ጋብቻ ተሳስረን ተዋልደን በአንድ ኢትዮጵያ ጥላ ስር ያለነውን ማህበረሰብ ከእለት ወደ እለት ማንንም በህግ ተጠያቂ በማያደርግ መልኩ ከኢትዮጵያዊነት ወደ አማራነት ከአማራነትም ፈጥፍጠው ወደ ተራ ሰውነት አውርደው በሴራ መዶሻ ሊያጠፉን የማያደርጉት ጥረት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡

አሁን ደግሞ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከሚመሩት ህዝባቸው ያጡትን ተቀባይት ለማሰባሰብ ወደ ወለጋ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ነቀምት በመሄድ በኦሮምኛ ቋንቋ ያስተላለፉትን መልዕክት በኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሙሉ መረጃ መዝግቦ ባያስተላልፍም በስብሰባው በተገኙ አንዳንድ ሀገር እና ሕዝብ ወዳድ በሆኑ ኢትዮጵያውያን በአወጡት መረጃ ‹‹እናንተ ወደ እኛ ኑ እንጂ በሌላ አታስቡ፤ ሌላው ያወራሉ እኛ ግን ለኦሮሞ ነው የምንሰራው እየሰራንም ነው፡፡ ብልጽግና የኦሮሞ መንግሥት ነው በዚህ ወቅት ስልጣኑ ከእጃች ከወጣ በመቶ ዓመት ውስጥ አናገኘውም፡፡ በሰሜን በኩል ያሉት እያንገራገሩን ነው፡፡ እኛ ተደራጅተን እነሱን ማንበርከክ ካልቻልን እኛ ስልጣን ላይ ያለነውን ብቻ ሳይሆን የምንጎዳው ኦሮሞ የሆነ ሁሉ ነው የሚጎዳው፡፡ በወለጋ በርካታ የተፈናቀሉ አሉ፤ እነዚያ የተፈናቀሉ ለእኛ የሚተኙልን ይመስላችኋል ወይ? ከዛሬ ጀምሮ ሸኔ ከእኛ ጋር መቆም ሆነ መግባት ይችላል›› የሚል እጅግ አደገኛ በሆነ ሁኔታ የድጋፍ ጥሪ ማስተላለፋቸው የኦሮሞን ማህበረሰብ ቀርቶ መላውን ኢትዮጵያዊያንን ከድህነት ወደ ብልጽግና የማያሻግር ለዘር ፍጅት ግን የሚጋብዝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

ከዚህ ቀደምም በጥልቀት አልተገነዘብነውም እንጂ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ የመከላከያ ሰራዊታችን የሆኑት ከነሙሉ ትጥቃቸው ጋር ወደ ሥራ ቦታዎ የመጡትን በብልጠት በታከለበት ከሸኙአቸው በኋላ የዘር ፍጅት ቅስቀሳ አድርገው ነበር፡፡ እስኪ እንዳለፈው መጣጥፌ ዛሬ ደግሞ ሌላ አንድ ሁለት ጥያቄ ልጠይቅዎት፡፡ እርስዎ የኦሮሞ ተወላጅ ነዎት፡፡ ባለቤትዎ ቀዳማዊት እመቤት ደግሞ የአማራ ተወላጅ ናቸው፡፡ ከሁለታችሁ አብራክ የተገኙት ልጆች የማን ብሔር ተወላጅ ናቸው፡፡ ሌላውም በወለጋ ነቀምት ባደረጉት ንግግር ተንተርሼ አሁንስ ብልጽግና ፓርቲ የኦሮሞ ተወላጆች ብቻ ነው? የኢትዮጵያ መንግሥትም ቢሆን የኦሮሞ ተወላጆች ብቻ ነው ይላሉ? ስለዚህ እባካችሁን ሳይማሩ እንደተማሩ ምቾት ሳይደላቸው ባዶ እግራቸውን ለጠጠር ደረታቸውን ለጥይት ሰጥተው ያቆዩንን ሀገር ዛሬ ያውም የውጪውን ትምህርት ሳይቀር ቀስመናል ተምረናል ሁሉን አውቀናል የምትሉት እንኳን አይደለም ለወዳጅ ወገኑ ላውሬ በሩ ላይ ወተት እና ውሃ የሚያስቀምጠውን አቃፊ የኦሮሞን ሕዝብ አሁንም ለግል ስልጣናችሁ እና ምቾታችሁ ስትሉ በሀሰተኛ ትርክት በመጋት በኢትዮጵያ ጥላ ሥር ያለውን ወገንን ፣ ዜጋውን ጠልቶ እንዲጠላ ባታደርጉት፡፡ ስልጣንም ቢሆን በብሔር ስም ተደብቆ እና ተሸሽጎ የሚያዝ ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር ቅቡልነት ባለው የምርጫ ቦርድ ውሳኔ መሰረት መሆን አለበት፡፡ ያለበለዚያ ግን ሥልጣኑም ባንኩም ታንኩም በእጃቸው እንደነበረው ህወሓት በተረኝነት የግዛት ማስፋፋት በማነሳሳት ከአማራው፣ በሱማሌው፣  ከአፋሩ፣ ከቤንሻንጉሉ፣ ከጋንቤላው፣ ከሲዳማው፣ ከጋሞው መሬት ይገባዋል በሚል ግልጽ ወረራ ባታጋጩት ጥሩ ነው፡፡ መጋጨቱም እና ግጭት መፍጠሩ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡

ወደ ተነሳሁበት ርዕስ ልመለስና ሰፊው የአማራ ተወላጆች ከእንግዲህ ወዳጅና ጠላትክን ማወቅ አለብህ፡፡ ወዳጅህ ለሰላም የሚሰብክና ለአንድነትህ የሚታገልልህ ነው፡፡ ጠላትህ ደግሞ በምላጭ ምላሱ እና አንደበቱ እየሸነገለህ በተግባር ሲታይ ግን መልካሙን እንዳናጭድ እንክርዳድ ሆኖብን ተረጋግተን እንዳንኖር የጦርነት ድግስ የሚጋብዘን ነው፡፡ በመሆኑም ዛሬም እንደ ትናንቱ በየአቅጣጫው እረፍት እንዳናገኝ የመንግስታዊ አመራሮች እውቅናና ድጋፍ ባለበት መልኩ በእርስ በእርስ ሴራና ሽኩቻ በሞት ከተነጠቅናቸው እንደ አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)፣ እንደ ምግባሩ ከበደ እንዲሁም ወደ ፊት የአማራ ሕዝብ በነፃነት በሀገሩ ተንቀሳቅሶ በሰላም እንዳይኖር ከወዲሁ የመከራ ሴራ ሸፍጥ እየተሰራበት እንደሆነ ሁሉም ከታች እስከ ላይ ያሉ የክልሉ አመራሮች በጥብቅ በማስገንዘብ ከፖለቲከኞች በላይ ተሰሚነት ያላቸው የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶችም ከህዝባቸው ጋር እንዲያውቁት በማሳሰብ በተለይ የሀይማኖት አባቶች እውነትን ተናግረው እንደ አቡነ ጴጥሮስ መስዋዕዋት ክፈሉ የሚል የትንቢት ጥሪ ያደረጉት በዚህና በሌሎችም ጉዳዮች በአስመሳይ አስብቶ አራጆች በሕይወት እንዳይያዝ የሚል ፍትሕ አልባ የግድያ ትዕዛዝ የተላለፈባቸው ጀኔራል አሳምነው ጽጌ ባለፈው ሳምንትም በትውልድ ቀያቸው ከባልደረቦቻቸው ጋር የግፍና የጭካኔ ጭፍጨፋ የተፈጸመባቸው አቶ ግርማ የሺጥላ ከመሳሰሉ በሳል አመራሮች ከነበሩት ትምህርት በመውሰድ ከመቸውም በላቀ ሁኔታ ከምትመሩት ሕዝብ ጋር በመቀራረብ ተማምናችሁ እና መከታ አድርጋችሁ መነሳሳት አለባችሁ፡፡

 በዚህም መቀራረብ በማንነት ተኮር ጥቃት ተመርጠው የተገደሉትን ወገኖቻችን እና ዜጎቻችንን በህይወት ባናገኛቸውም ወደፊት በዘር ማጥፋት፣ ማሳሳት የገደሉትንና ያስገደሉትን ለፍርድ ማቅረብ አያቅትም፡፡

ሌላውም በሰሜኑ ኢትዮጵያ በተከሰተው የሀገር ህልውናን ለማስከበር በተደረገው ዘመቻ የሀገሪቱ የመጨረሻ ምሽግ ከሆነው ከኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ጋር በድንጋይ ትራስ ተንተርሰው፣ በጋራ ኮዳ ውሃ ተጋርተው በመጠጣት፣ በመቁሰል የህይወት መስዋእትነት ከፍለው በአንድ ጉድጓድ የተቀበረው የአማራ ልዩ ኃይላችን ሆነ የፋኖ አርበኞች ከክልሉ ከፍተኛ እስከ መካከለኛ አመራሮች ጋር ችግሮችን በመሳሪያ ኃይል ግጭት በመፍጠር ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ ተቀራርበው በመወያየት ችግሮችን መፍታት ከጉዳቱ ጥቅሙ ያመዝናል፡፡ በዚህም በውጤቱ ሲመዘን በጦርነት በመፈናቀል ለተጎዳው የአማራ ክልል ማህበረሰብ የሰላም እረፍትን በማረጋገጥ ልማትን ወደ ነበረበት በማምጣት በክልላችን የተጀመሩትን የልማት አውታሮችንም በማፋጠን እንዲቀጥሉ በማድረግ ፍላጎታችን ደረጃ በደረጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላችሁን ጥረት ማድረግ አለባችሁ ያለበለዚያ ግን ወዳጅ መስለው ቁሞ ቀሮች እያሉ ለሚያበጣብጡን የታሪክ ምርኮኞች መሳቂያና መቀለጃ እንዳታደርጉን፡፡ በመሆኑም ሁላችሁም አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን መቶ ጊዜም ቢሆን አስቡበት፡፡