በኢትዮጵያ የሪል እስቴት ዘርፍ ግንባር ቀደም ከሆኑት ድርጅቶች አንዱ የሆነው ዴማ ሆፕ ሪል እስቴት፣ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ አገልግሎት ከሚሰጠው ፋስትፔይ (FastPay) ጋር ስልታዊ የሥራ አጋርነት ስምምነት መፈራረሙን አስታውቋል።
ይህ አዲስ ጥምረት በዋናነት በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን (ዲያስፖራዎች) ያሉባቸውን የክፍያ ፈተናዎች ለመቅረፍ ያለመ ሲሆን፣ ደንበኞች ህጋዊ፣ ፈጣን እና አስተማማኝ በሆነ መንገድ የመኖሪያ ቤቶችና የንግድ ሱቆች ክፍያ መፈጸም የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።
በስምምነቱ መሠረት፣ ደንበኞች የፋስትፔይን የክፍያ ሥርዓት በመጠቀም ከዴማ ሆፕ ሪል እስቴት የሚገዟቸውን ቤቶች ክፍያ በቀጥታና በቀላሉ ማከናወን ይችላሉ። ይህም ዲያስፖራው በሀገሩ ያለ ስጋት ኢንቨስት እንዲያደርግ ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው ተገልጿል።
ዴማ ሆፕ ሪል እስቴት በአሁኑ ወቅት ከዘጠኝ በላይ ፕሮጀክቶች ያሉት ሲሆን፣ ከንግድ ስራው ባለፈ በትምህርት ቤቶች ግንባታና በማህበራዊ ኃላፊነት ስራዎች ላይ በንቃት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ተጠቁሟል። ፋስትፔይ በበኩሉ፣ ወደ ሀገር ውስጥ የሚላክን የውጭ ምንዛሬ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘና የተሻለ የምንዛሬ ዋጋ የሚያቀርብ በመሆኑ፣ ይህ አጋርነት በዘርፉ ላይ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል ተብሎ ይጠበቃል።
