የኢትዮጵያ መንግሥት የሀገር ውስጥና የውጪ አጠቃላይ ብድር ከሦስት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ጭማሪ ማሳየቱን የገንዘብ ሚኒስቴር በየሶስት ወሩ የሚያወጣው የሀገሪቱን የብድር ሁኔታ የሚያትተው ሰነድ አመለከተ። አጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግስት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ብድር በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሰኔ 2022 ላይ 57.3 ቢሊየን ዶላር የነበረ ሲሆን፣ ይኸው ቁጥር መጋቢት 2023 ላይ 60.6 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ደርሷል። ይሄም በመቶኛ ሲገለጽ የሀገሪቱ አጠቃላይ ብድር የስድስት በመቶ ጭማሬን አሳይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ለተነሱላቸው ጥያቄዎችን ምላሽ ሲሰጡ የኢትዮጵያ ብድር ከሀገሪቱ አጠቃላይ አመታዊ ምርት አንጻር ከነበረው የ59 በመቶ ድርሻ ወደ 38 በመቶ ዝቅ ማለቱን ተናርግረው ነበር። ሆኖም የብድር ምጣኔው ከሀገራዊ ምርት አንጻር ያለው ድርሻ ይውረድ እንጂ የብድሩ መጠን ግን በራሱ ጭማሪ እያሳየ መጥቷል። ለብድር መጠኑ መጨመር የውጭውም የሀገሪቱም የብድር መጠን ማደግ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ሰነድ ማብራሪያ አመልክቷል።
የውጭ ብድር እ.አ.አ ሰኔ 30 2022 ከነበረበት 27.9 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እ.አ.አ መጋቢት 2023 ወደ 28.1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር አድጓል። ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች ተጠቅሰዋል። አንዱ የአሜሪካ ዶላር የምንዛሬ አቅም ተለዋዋጭ ሆኖ በአንጻሩ ደግሞ ላለፉት ወራት ከሌሎች ሀገራት ምንዛሬዎች አንጻር በትንሹም ቢሆን ደከም ብሎ መታየቱ በምክንያትነት ተጠቅሷል።
ሌላው የኢትዮጵያን የውጭ ብድር ከፍ እንዲል ያደረገው በተጠቀሱት ዘጠኝ ወራት ወደ ሀገር ውስጥ የገባው ብድር ፣ ወለድን ሳይጨምር ከተከፈለው ዋና ብድር ከፍ ብሎ በመታየቱ እንደሆነ የገንዘብ ሚኒስቴር ጠቅሷል። ካለፈው አመት ሀምሌ ወር መጀመርያ አንስቶ እስከዚህ አመት መጋቢት ወር መጨረሻ ድረስ የአለም አቀፍ የልማት ድጋፍ ብዙ ድርሻ ያለበት ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ ብድር የገባ ሲሆን፣ ወለድን ሳይጨምር የተከፈለው ዋና ብድር ግን 948 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ነው።
የኢትዮጵያ የውጭ ብድር ከሀገሪቱ አጠቃላይ አመታዊ ምርት አንጻር ያለው ድርሻ 13 በመቶ እንደሆነ ተጠቅሷል። ከሀገራዊ ምርት አንጻር የውጭ ብድር ምጣኔው ኢትዮጵያን አስጊ ጫና ካለባቸው ሀገራት ተርታ ያስወጣት ቢሆንም የዕዳ ከፋይነት ዋና መለኪያ በሆነው መመዘኛ ግን ሀገሪቱ አሁንም ችግር ውስጥ ነች።
የዕዳ ከፋይነት አቅም መለኪያ የሆነው የሸቀጦች እና አገልግሎቶች የወጪ ንግድ ገቢ ከሀገሪቱ እዳ አንጻር ያለው ምጣኔ ሲሆን ፣ በዚህ እይታ ሲቃኝ አሁንም የኢትዮጵያ የዕዳ ከፋይነትም ሆነ ተሸካሚነት አቅም አሁንም ችግር ውስጥ ያለ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች “ኢትዮጵያ አለባት የሚባለው የውጭ ብድር ብዙ የሚባል አይደለም ፣ ችግሩ ያለው ሀገሪቱ ምርትና አገልግሎቶችን ለውጭ ገበያ አቅርባ በውጭ ምንዛሬ ያለባትን ዕዳ የመክፈል አቅሟ ደካማ መሆኑ ነው” ሲሉ አብራርተዋል።
ባለፈው አመት ሀገሪቱ ክብረ ወሰን በተባለ ደረጃ ከ4 ቢሊየን ዶላር በላይ ከሸቀጦች የወጪ ንግድ አግኝታለች። በዚህ አመት የሚኖረው የሸቀጦች የወጪ ንግድ ያሉ አመላካቾች ግን ገቢው ከአምና ዝቅ እንደሚል ያሳያሉ። እነዚህ ምክንያቶች የሀገሪቱን የብድር መክፈል አቅም ያዳክሙታል።
ሌላው ለኢትዮጵያ መንግስት ብድር መጨመር አስተዋጽኦ ያደረገው የሀገር ውስጥ ብድር ሲሆን ፣ ይህም ባለፈው ሀምሌ ወር ላይ 1.5 ትሪሊየን ብር የነበረው የመንግስት የሀገር ውስጥ ብድር በዚህ አመት መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ የ14 በመቶ እድገት አሳይቶ 1.7 ትሪሊየን ብር ደርሷል።
ከሁለት ወራት በፊት ኢትዮጵያ ከዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ድጋፍ ለማግኘት በምታካሂደው የፖሊሲ ማሻሻያ ውይይት ስምምነት ላይ ለመድረስ መቃረቧ መገለጹ አይዘነጋም። ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በተካሄደው፣ የአይ ኤፍ ኤም እና የዓለም ባንክ “የስፕሪንግ” ጉባኤ ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ልዑክ፣ የኢትዮጵያን የውጭ ዕዳ መልሶ በማዋቀር ዕፎይታና ብድር ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክሮ ነበር። በወቅቱ በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የተመራ የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን፣ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በተካኼደው፣ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትና ዓለም ባንክ ጉባዔ ላይ ተሳትፎም ነበር።
የጊዜው የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት ዴቪድ ማልፕስ፣ ኢትዮጵያ ጨምሮ ሌሎች ታዳጊ አገሮች ያለባችሁን ከፍተኛ የውጭ ዕዳ ማቅለያ ለማራዘም ያቀረቡትን ጥያቄ መዘግየቱን ‹‹አሳሳቢ›› ብለውት ነበር። በአፍሪቃ ልማት ባንክና ዓለም ባንክ የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሰሩ የተለያዩ ባለሙያዎችም ጥያቄው በርግጥም ጊዜ መፍጀቱ፣ የሀገራቱን ምጣኔ ሀብት የሚጎዳ መሆኑን ገልፀው፣ በአጭር ግዜ ውስጥ መፍትሄ ያገኛል የሚል እምነት እንዳላቸው ሲጠቁሙ ነበር።
ኢትዮጵያ የብርን የመግዛት አቅም ማዳከሟ አይቀሬ መሆኑን ኢኮኖሚስቶች በተደጋጋሚ ሲናገሩ የቆዩ ሲኾን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንደ ሀገር የገጠመውን የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታት በሚል በየጊዜው የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱ አይዘነጋም። በዚህ ረገድ የወጪ ንግድን ለማበረታታት እና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታት እንደ መፍትሔ ሲወሰድ የቆየው የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም አንዱ ነው። ለአብነትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት አንድ የአሜሪካ ዶላር 27 ብር ገደማ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ በባንኮች 54 ነጥብ 2 ብር በመመንዘር ላይ ሲሆን በጥቁር ገበያ ደግሞ እስከ115 ብር ድረስ እየተመነዘረ ይገኛል።
በብዙ ጉዳዮች እየተፈተነ ያለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የገጠመውን የውጭ ምንዛሬ ተመን ለመፍታት ሲል መንግስት ብድር እና ሌሎች የገንዘብ ድጋፎችን ለማግኘት የብርን የመግዛት አቅም ያዳክማል፣ ለዚህ ደግሞ የውጪ ንግስትን ለማበረታታት የሚል ስም ይሰጣል የሚሉት የምጣኔ ሃብት ባለሙዎች ደግሞ፣ ከዚህ በፊት የተደረጉ የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም ውሳኔዎች የኑሮ ውድነትን ከማባባስ፣ የሐብት ሽሽትን ከመፍጠር እና የንግድ ሚዛንን ከማዛባት ውጪ ጥቅም አለማስገኘታቸውንም ያስታውሳሉ።
