ከሁለት ሳምንት በፊት ሚያዝያ 15 ቀን 2015 ዓ.ም በወዳጅነት አደባባይ አንድ መርኀ ግብር ተከናውኗል፡፡ መርኀ ግብሩ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ (ፕሪቶሪያ) በመንግሥትና በህወሓት መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት መሬት የማውረድ እንቅስቃሴዎችን መሠረት በማድረግ ‹‹ጦርነት ይብቃ ፤ ሰላምን እናጽና›› በሚል መሪ ቃል የተከናወነ ነው፡፡ በዚህ መርኀ ግብር የኢፌዲሪ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ፣ የሁሉም ክልሎች ርዕሣነ መስተዳድሮች፣ የአፍሪካ ሕብረት የድርድር ከፍተኛ የፓናል አባላት ታዳሚዎች ነበሩ፡፡ መርኀ ግብሩ በመርኅ ደረጃ የሚተች ባይኾንም በጠ/ሚኒስትሩ እና በአንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጦርነቱን አስመልክቶ የተላለፉ መልዕክትች ግን አደገኛ ናቸው የሚል ዕምነት ግዮን አድሮባታል፡፡
ለዚህ እንደ ቀዳሚ አብነት የሚነሳው ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጦርነቱን የአማራና የትግራይ ለማስመሰል የተጠቀሙት ቋንቋ ነው፡፡ ከሁለት ለላቁ ዓመታት በዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያው ደም አሳፋሽ ጦርነት፣ በዋናነት የፌዴራል መንግሥቱ በሚመራው ጦር እና በህወሓት መካከል የተደረገ ጦርነት መኾኑ ግልጽ በኾነበት ሁኔታ፣ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ውጊያውን የአማራ እና የትግራይ ክልል አመራሮች ጸብ የሚያስመስሉ ዐረፍተ ነገሮችን ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ እና ለአቶ ይልቃል ከፋለ ያቀረቡት ጥሪዎችም ጸቡ በሁለቱ ክልሎች መካከል የተደረገ እና ጠ/ሚኒስትሩ ግን እንደ ጲላጦስ ከደሙ ንጹሕ መኾናቸውን ለመግለጽ የፈለጉ መኾናቸውን የሚያሳብቅ ነው፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚህ የመድረክ ንግግራቸው የአማራ ክልል ርዕሠ መስተዳድርን በአደባባይ ግትር እንደሆኑ፣ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ደግሞ ለዘብተኛና የሰላም ሰው እንደሆኑ ለማሳየትም ሞክረዋል፡፡ ተመሳሳይ ይዘት ያለውን መልዕክት አቶ ጌታቸው ረዳም በንግግራቸው ለመድገም ሲሞክሩ መታዘብ ይቻላል፡፡
መንግሥት በተደጋጋሚ ጦርነትንም ኾነ ሰላምን ለሕዝቦች ‹‹ምን ዘላቂ ጥቅም ያመጣል?›› የሚለውን አይቶ ከመወሰንና ደፍሮ ከመግባት ይልቅ ጊዜያዊ የሚመስሉ ጥቅሞችን እና ስልቶችን አስልቶ ሲያከውናቸው መመልከት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ጦርነቱ ግልጽ በኾነ ሁኔታ የተመራው ጠ/ሚኒስትሩ በሚመሩት መንግሥት ኾኖ ሳለ፣ አንድ ማኅበረሰብ እና የፖለቲካ ቡድን ብቻ በጦርነቱ መግፍኤነት ተደጋግሞ ሲወቀስ እና ሥሙ ሲጠፋ ዝምታ በመምረጥ ያጡትን የፖለቲካ የበላይነት ለማግኘት መጣር የሥርዓቱ ሁነኛ ሥልት ከኾነ ከራርሟል፡፡ አሁን ደግሞ ከዛም አልፎ የሰላም አየር መንፈስ ሲጀምር ራስን የሰላም ሐዋርያ፣ ‹‹ሌሎችን›› ደግሞ ሰላሙ ወደ መሬት እንዳይወርድ እንቅፋት አስመስሎ ኃላፊነትን ከትከሻ ለመወርወር የሚደረገው ሩጫ ፈጽሞ ዘላቂነትን የማያመጣ አካሔድ ነው፡፡
መንግሥት ከምንም በላይ የሕዝብ ደህንነትን እና የሀገርን ሕልውና የማስከበር እና የማጽናት መንግሥታዊ ኃላፊነት በእጁ እስካለ ድረስ ከየትኛውም የፖለቲካ ኃይል ጋር ሰላማዊ እና ንግግርን ማዕከል ያደረገ የችግር መፍቻ ሥልትን ተግባራዊ ማድረጉ የሚደገፍ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከህወሓትም ኾነ ከኦነግ ሸኔ ጋር በውይይት ችግሮችን ለመፍታት ያሳየው ፍላጎት የሚበረታታ ነው፡፡ የዛኑ ያህል ግን በየጊዜው በማንነቱ ተመርጦ ለሚገደለው፣ መኖሪያ ቤቱ ለሚፈርስበት እና መድረሻ ያጣ እንዲኾን ፈርጀ ብዙ መዋቅራዊ እና ሕጋዊ ማሳደዶች ላልቆሙለት ሕዝብም በተመሳሳይ መንገድ ችግሮቹንና ጥያቄዎቹን መልስ ለመሥጠት ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ኾኖም በተደጋጋሚ ይኽን ከማድረግ ይልቅ በወልጋዳ ሚዛን (Double Standard) ትችት ላይ ሊጥሉት የሚችሉትን ውሣኔዎች ገቢራዊ ሲያደርግ ይታያል፡፡ እንዲህ ያለው አካሔድ መንግሥት ውሣኔዎቹና አካሔዶቹ ሁሉ የእርሱን የፖለቲካ ግብ ከግምት ያስገቡ ብቻ ተደርገው እንዲወሰዱ ለትርጉም ክፍት ከማድረግ ዘልለው፣ ሰላምን ጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ማካበቻ ለማድረግ መወሰኑን ያሳብቃሉና እንዲህ ካለው አካሔድ መቆጠብ ይገባዋል ለማለት እንወዳለን!
