የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ወደ ሰሜን ኮሪያ በማቅናት ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን ጋር ተወያዩ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሰሜን ኮሪያው ፕሬዚዳንት ጋር መገናኘታቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ያጋሩ ሲሆን፤ እስከ እሑድ ድረስ እዚያው ቆይተው በተለያዩ ጉዳዮች ከሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር እንደሚመርክሩ ተዘግቧል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የሁለቱ ሀገራትን ወታደራዊ ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል ማሳያ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ኪም ከኒውክሌር የጦር መሣሪያ ጋር ተያይዞ ከውጭ ለሚደረግባቸው ጫና የሩሲያን ቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚፈልጉ ተጠቅሷል።
ላቭሮቭ ፕሬዚዳንቱን ከማግኘታቸው በፊት፤ በምሥራቅ የሀገሪቱ ባሕር ዳርቻ በምትገኘው ቮንሳን ከተማ በቅርቡ በተከፈተው ትልቅ ሪዞርት ውስጥ ከአቻቸው ከቾ ሶን ሁ ጋር ተወያይተዋል።
ሰሜን ኮሪያ በዩክሬን ጦርነት ላይ ወታደሮቿን በመላክ ላደረገችላቸው ድጋፍ ያመሰገኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ስለጦርነቱ ሁኔታ እና ቀጣይ ድጋፍ መወያታቸውን ታስ የዜና ወኪልን ጠቅሶ የዘገበው እልጄዚራ ነው።
