ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ቤተ ክርስቲያን የመልካም አስተዳደር ችግሮች እና የቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና አለመከበር እንዲሁም በርካታ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ጉዳዮች ባይታዋር የሆኑበት፣ ቤተ ክርስቲያኗን ለካህናቱና ጳጳሳቱ ብቻ እየተው የመጡበት ሁኔታ ይታያል፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስትያንን ፖለቲከኞች፣ አማሳኞች፣ ምንደኞች አገልጋዮች እንዲሁም የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላቶቿ አጀንዳ ሲያደርጓት፣ ባልዋለችበት ሲያውሏት፣ የማይገልጻትን ጥላሸት ሲቀቧት፣ ታሪኳን ሲሰርዙ፣ ሲደልዙ፣ የፕሮፖጋንዳ ሰለባ ሲያደርጓት፣ በባሰ ሁኔታ ኵላዊትነቷን፣ ዓለማቀፋዊነቷን ወደ ጎን በማለት በርካሽ የጎሳ ከረጢት ሊከቷት ሲሞክሩ እያዩ ዝም ማለታቸው ነው፡፡
ስለዚህ ቤተ ክርስቲያኗ ክብሯ ተጠብቆ ሲኖዶሳዊ ልዕልና እንዲከበርና በአገልግሎቷና በአስተዳደርዋ ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲመጣ የምእመናን ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡
ይህ ጽሑፍ ስለ ቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና ግንዛቤ ለማሳደግ ታስቦ የቀረበ ነው፡፡
1.1. ቅዱስ ሲኖዶስ ማለት ምን ማለት ነው?
ሲኖዶስ ቃሉ የጽርዕ ቋንቋ ሲሆን ትርጉሙም ስብሰባ (ጉባኤ) ማለት ነው፡፡ አንድ/ቃለ ዓዋዲ፣ ሀብታችንና ሥርዓቱ/ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት/
ቤተ ክርስቲያናችን በሕግና በሥርዓት እንድትመራ ልዩ ልዩ መመሪያዎች ተሰጥተዋታል፡፡ የመመሪያው ባለቤትም ራሱ መሥራቿ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ነው፡፡ ‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው እና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ›› በማለት አደራ የሰጣቸው የሐዋርያት ተከታዮች የሆኑ ሊቃነ ጳጳሳትን ነው፡፡ (2ኛ የሐዋ.ሥራ 20፥28) የጳጳሳቱ አንድነት ጉባኤ /ስብስብ /ደግሞ ሲኖዶስ ይባላል፡፡
1.2. የቅዱስ ሲኖዶስ ታሪካዊ አመጣጥ፡–
በብዙ ታሪኮች ላይ እንደ መጀመሪያ ሲኖዶስ ጉባኤ ተመዝግቦ የሚገኘው በ፶ ዓ.ም በኢየሩሳሌም የተደረገውን ጉባኤ ነው፡፡ ጉባኤውም በሐዋርያት የተደረገ ስብሰባ ሲሆን መሪውም የኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ያዕቆብ እንደነበረና የስብሰባው ምክንያትም ከአይሁድ ወደ ክርስትና የመጡት እና ከአሕዛብ በመጡት መካከል በነበረው አለመግባባት ላይ ለመምከር ነበር፡፡ (የሐዋ.ሥራ 1፥15) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በርካታ ስብሰባዎች ተደርገዋል፤ በርካታ ሥርዓቶች እና ሕግጋት ለቤተ ክርስቲያን ተደንግገውበታል፡፡ በዚህም ሲኖዶስ እየተባሉ የሚጠሩ እና እስካሁን ቤተ ክርስቲያን የምትመራባቸው ሕጎች ወጥተውበታል፡፡ በኋላም በብዙ ዓለም አቀፍ ጉባኤያት /ኒቅያ፣ ቍስጥንጥንያ፣ ኤፌሶን ወዘተ/ ዳብረውና ጸንተው የተላለፉ ውሳኔዎች አሉ፡፡ ፍትሐ ነገሥት ዋናውና ትልቁ ሲሆን በርካታ የሐዋርያት ሲኖዶስ ውሳኔዎችና ሌሎች ሕጎችን ይዟል፡፡
1.3. የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ተግባርና ኃላፊነት ፡–
ቅዱስ ሲኖዶስ ከላይ እንደተገለጸው በዓመት ሁለት ጊዜ እየተሰበሰቡ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ አጀንዳ አድርገው እንዲወያዩ ሥርዓት ተሠርቷል፡፡ (ፍ/መ. 5፥165) ይህም ሥርዓት እስካሁን ቀጥሏል፡፡ የስብሰባውም ምክንያት
- ሃይማኖትን ለማጽናት፣ ምግባርን ለማቅናት
- ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለማስፋት፣ ምእመናንን ለማብዛት
- መናፍቃንን /ከሐድያንን ለመለየት፣ ሕግንና ሥርዓትን ለማውጣት ብሎም ለማስፈጸም
- የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ አንድነት ለማጽናትና ሁለንተናዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ መብቷን ለማስከበር አስተምህሮዋን ለማስፋት እና ለማስቀጥል የሚደረጉ ስብሰባዎች ሲኖዶስ እየተባሉ ይጠራሉ፡፡
ምክንያቱም ተሰብሳቢዎቹ ‹‹አደራ ጥብቅ ሰማይ ሩቅ›› እንዲሉ አበው አደራቸውን ለመወጣት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ፣ ለመንጋው መራራትና ለራሳቸው መጠንቀቅ የተሰጣቸው አደራ ነውና፡፡ (የሐዋ. ሥራ 20፥28) ዋጋቸውንም በሰማይ ይቀበሉ ዘንድ፡፡ አንድም መክሊታቸውን ቀብረው ክፉ አገልጋይ (ማቴ. 25፥24) ተብለው እንዳይፈረድባቸው ተግተው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ይሠራሉ፡፡
1.4. የቅዱስ ሲኖዶስ የክብሩ/የልዕልናውና መገለጫ፡–
ቅዱስ ሲኖዶስ ክብሩ ከፍ ያለ ነው፤ ልዕልናውም እጅግ ታላቅ ነው፤ ቅዱስም ነው፤ ቅድስናው፣ ልዕልናው ክብሩ እንዲሁ አይደለም፤ ምክንያቱም
ሀ. መሪው ሰብሳቢው መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ነው፡፡
ሲሰበሰቡና ሲወስኑ መንፈስ ቅዱስን መሪ ሰብሳቢ አጋዥ አድርገው ስለሆነ ነው፡፡ አርዮስን ለማውገዝ ሃይማኖት ለማጽናት በኒቅያ /የቤተ ክርስቲያን ታሪከ፣ ሃይማኖተ አበው/ የተሰበሰቡ 318 ሊቃውንትም ጌታ አብሯቸው እንደሚሰበሰብ እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል፡፡
ለ. የሐዋርያት ወራሴ መንበር ስለሆነ
‹‹እናንተን የተቀበለ እኔን መቀበሉ ነው ያላቸው የሐዋርያት ተከታዮች ናቸው፤ ሊቃነ ጳጳሳት በክርስቲያኖች ላይ ያላቸው ሹመት ሙሴ በእስራኤል ላይ እንደነበረው ምስፍና ያለ ነው›› ተብሎ ተደንግጓል፡፡ (ፍ/መ/4፣54 እና 55/
ሐ. ለቅድስና የሚያበቃ ሕግና ሥርዓት ስለሚወጣበት ነው፡፡
ሥጋዊ ያይደለ መንፈሳዊ፣ ምድራዊ ያይደለ ሰማያዊ ሥርዓት የሚሠራበትና ሕግ የሚደነገግበት ስለሆነ ነው፡፡
መ. በቅድስናቸው፣ በንጽሕናቸው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጠባቂነት የተመረጡ ስለሚሰበሰቡበት
ለቅድስና በምታበቃ ክህነት የተሾሙ፣ ሹመታቸው/መመረጣቸው ከሰው ሳይሆን ከእግዚአብሔር የሆነ፣ እኛና መንፈስ ቅዱስ ብለው የሚወስኑ፣ ጥብቅናቸው ለቤተ ክርስቲያን የሆኑ ብፁዓን አበው የሚሰበሰቡበት ስለሆነ ቅዱስ ነው፡፡
ሠ. ሃይማኖት እምነት የሚጸናበት ጉባኤ ስለሆነ
የሃይማኖት አንድነት የሚጸናበት፣ ክሕደት፣ ጥርጥር፣ የሚወገዱበት፣ አጋንንትና ውሉደ አጋንንት የሚገሠፁበት እና የቅዱሳን ቅድስና የሚነገርበት/የሚወሰንበት/ ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ ስንል ቅድስናው የሚመነጨው ከሰው ሳይሆን ከራሱ ሁሉን ከሚቀድስ መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ክቡር፣ ቅዱስና ልዑል ነው፡፡
1.5. የልዕልናው መገለጫ የውሳኔዎቹ መፈጸም ነው፡፡
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ሲኖዶስ ክቡር ነው፤ ቅዱስ ነው፤ መሪውም መንፈስ ቅዱስ ነው፤ የክብሩ መገለጫ የልዕልናው መታያ መሆን ያለበት በመንፈስ ቅዱስ በብፁዓን አባቶች የተወሰነ ውሳኔ ሁሉ ሲከበር እና ሲተገበር ነው፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለብዙ ሺህ ዓመታት ጸንታ የቆየችው ወርቃማውን ሥርዓቷን ጠብቃ ለትውልዱ ሁሉ ኩራት የጥበብ፣ የዕውቀት ሥጋዊ ወመንፈሳዊ ቤት፣ የመልካም ሰብእና ማእከል ሆና የዘለቀችው የማይናወጽ ሲኖዶሳዊ ሥርዓት በመጠበቁ በመከበሩ ውሳኔዋ በመፈጸሙ ነው፡፡ በርግጥ አንዳዶች በሊቃውንት ጉባኤ ስትመራ እንደኖረችናየሲኖዶሳዊ ታሪኳ ከ50 ዓመት ያልዘለዘለ መሆኑን ይሞግታሉ፡፡ (አቡነ ሳሙኤል) ቢሆንም በሐዋርያት ሲኖደስ የምንተዳደር፣ ‹‹ማርቆስ አባታችን እስክንድርያ እናታችን›› ብለን የኖርን ሲኖዶስ አልነበረንም ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ ስለሆነም፡-
- የሕግና ሥርዓት ምንጭ፣ የቤተ ክርስቲያን ጠበቃና ዳኛ
- የጾታ ምእመናን ባላደራ፣ የሐዋርያት ወራሴ መንበር የሆነ
- የምሥጢራት ባለቤት፣ የክህነት መገኛ ወዘተ የሆነው
ቅዱስ ሲኖዶስ ክብሩ ልዕልናው ካልተከበረ ውሳኔው ካልተፈጸመ ህልውናው ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቀርቶ ሀገርና ትውልድ አደጋ ላይ ይወድቃሉ፡፡ ምክንያቱም ሕግ ሁሉ ከሰው ከሆነ ሕገ ሰብእ መሆኑ ይቀርና ሕገ አራዊት ይሆናልና፡፡ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ መገለጫዋ መሪዋ የሕግ ሁሉ ምንጭ ሲኖዶሷ ነውና፡፡
2.1. ሲኖዶሳዊ ልዕልና እንዲሸረሸር ያደረጉ ምክንያቶች፡-
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እንደ ሀገር ትልቅ ችግር ገጥሞናል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና የሚዳፈሩ፣ የሚያወጣቸው ሕጎች እና ውሳኔዎች እንዳይፈጸሙ የሚሠሩ፣ ሲኖዶሱን ለመከፋፈል፣ ሚዛኑን እንዲስት፣ ለአገልግሎት እንዳይተጋ፣ አደራውን እንዳይጠብቅ፣ በሕዝቡ ዘንድ ውዥንብሮች የሚፈጥሩና የሚከፋፍሉ፣ ከሲኖዶሱ የበለጠ ሐሳባቸው የሚደመጥ ግለሰቦችና ቡድኖች መፈጠራቸው ብዙ ውጫዊና ውስጣዊ ቅንጅት የፈጠሩ አካላት ቀላል የማይባል ችግር እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡
ይህም ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ደካማና መሪ የሌላት አስመስሏታል፤ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብቷን መጠበቅ እንዳትችልና ለውስጣዊና ለውጫዊ ጠላት እንድትጋለጥ ያደረገ ሲሆን የከፋው ደግሞ ያለስሟ ስም እንዲሰጣት፣ የታሪክ ሽሚያ እንዲደረግባት፣ ትውልዱ በተዛባ መንገድ እንዲረዳት፣ በእርሷ እንዳይጠቀም፣ ይልቁንም በጥላቻ እንዲነሣባት ሀገራዊ ውለታዋንም እንዳያስታወሰው አድርጎታል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የሚድያ ዘመቻ ይከፈትባታል፤ የጥቃት ሰለባ እንድትሆን፣ ሀብቷ ለውድመት አማኞቿም ለሞትና ለስደት እንዲዳረጉ አድርጓል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ የፖለቲካ ተሰሚነት እና ውክልና እንዳይኖራት፣ እጅግ ብዙ ችግር እንዲከባት ተሠርቷል፤ አሁንም እየተሠራ ይገኛል፡፡ ይህንም ለማድረግ የተቻለው በተቀናጀ ስልት ሲሆን ሲኖዶሱ ክብሩ ልዕልናው እንዳይጠበቅ በማድረግ፣ የመሪነት ሚናውን እንዳይወጣ፣ የተጠራበትን ሰማያዊ ተልእኮውን እንዳያሳካ፣ በመከፋፈል እና በራሱ ውስጣዊ አጀንዳ እንዲጠለፍና፣ ውሳኔው መሬት እንዳይነካ በማድረግ ነው፡፡ ከምንም በላይ መሪና ተመሪ እንዳይገናኙ፣ ሲኖዶሱ በምእመናን ዘንድ ተቀባይነት እንዲያጣ አድርጎታል፡፡ ‹‹መሪ የሌላቸው ሕዝቦች እንደረገፉ ቅጠሎች እንደተረበረቡ ግንዶች ናቸው›› እንዲሉ መሪ የማሳጣት መሪና ተመሪን የማለያየት ሥራ ነው፤ የተሠራው አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡
ለዚህም የችግሮቹ ምንጭ ከሁለት ወገን የመጡ ናቸው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡
1. ውስጣዊ ምክንያቶች እና
2. ውጫዊ ምክንያቶች ናቸው፡፡
2.1.1. ውስጣዊ ምክንያቶች /የችግር ምንጮች/
ውስጣዊ የሆነው ችግር ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ የተወሰነውን ለማየት ያክል
ሀ. ከራሱ ከቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት የሚመነጩ ችግሮች እየተበራከቱ መምጣታቸው
- የራሱ የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ዘመኑን የዋጀ አሠራርን አለመከተል፤
- ክብረ ክህነት ተገቢውን ቦታ አለማግኘቱ፤
- የፖለቲካና የብሔርተኝነት ዝንባሌ ያላቸው አንዳንድ የሲኖዶስ አባላት መታየታቸው፤
- የጳጳሳት አመራረጥና ሹመት አሰጣጥ ተአማኒነት የጎደለው ከሲሞናዊነት፣ ከብሔርተኝነት እና ከፖለቲካ አመለካከት ጋር በተያያዘ የሚነቀፉ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጥረዋል ተብለው ነቀፌታ የገጠማቸው እንዲሁም የሥነ ምግባር ጉድለት ያለባቸውን ወዘተ ወደ ሹመት መምጣት፤
- ከመንፈስ ቅዱስ ከሥራ ይልቅ የመንግሥትን አቋምና አጀንዳ የሚያራምዱ መኖራቸው
- የወሰኑት ውሳኔ የት እንደደረሰ ወረድ ብለው መፈጸሙን የመከታተልና ባልፈጸሙት አካላት ላይ ተገቢውን ርምጃ የመውሰድ ቁርጠኝነት አለመኖር፤
- የውጭ/የፖለቲከኞችን/ ጣልቃ ገብነት የመፍቀድ/የመፈለግ ዝንባሌ መታየት፤
- መንፈሳዊ እና ቁሳዊ አስተዳደሩ አለመለየቱና በተገቢው ሰው አለመመራቱ
- ‘አጥማቂ ነን፤ ነቢይ ነን፤ ባሕታዊ ነን’ የሚሉ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የሚጥሱ ሕዝቡን በሐሳብ የሚከፋፍሉ ሥርዓት አልበኞችን አለመገሥፅ ዝምታን መምረጣቸው ወዘተ፡፡
በመጽሐፈ ዲድስቅልያ ላይ ‹‹ሴቶችና ሕዝባዊ የክህነትን ሥራ አይሥሩ፤ እንዳያጠምቁ፤ በአንብሮተ እድም እንዳይባርኩ፤ በረከተ ኅብስቱንም እንደይሰጡ›› ሲሉ ቅዱሳን ሐዋርያት አዘዋል፡፡ (ዲድስቅልያ 14፥6 እና አንቀጽ 15፥1)
- አሁን ግን ሲኖዶሱንና አባላቱን ብሎም የክህነትን ክብር ያቃለሉና የተዳፈሩ፣ በማን ክህነት እንደተሰጣቸው፣ የትና በማን እንደመነኮሱ የማይታወቁ ምእመኑን የሚበዘብዙ ሥርዓት የጣሱ ‘አጥማቂ ነን፤ ባለ ሕልም ነን፤ እንባርካለን” እያሉ የሚያውኩትን ዝም በማለታቸው፣ ደረጃው አድጎ በብሔር ተደራጅቶ ማኅበር ማቋቋም፣ ቤተ ክህነት ማቋቋም እያለ ሲኖዶስ እስከማቋቋም የደረሰ ድፍረትን በእንቁላሉ መቅጨት አለመቻላቸው፤
- የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት ባለመቃወማቸው፣ ሥርዓት አልበኞችን መገሠፅ፣ ድኃ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ ብሎ መናገር ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ አለመሆናቸው ነው፡፡ አንዳድ አባቶች አልፎ አልፎ ደፍረው መንግሥትን ሲገሥፁ እንደብርቅና ድንቅ እየታየ እንደ ጀግና እንዲቆጠሩና እነርሱን ለማጀግን ብዙኃኑን ለመተቸት ዕድል ሲፈጥር ይታያል፡፡
ለ. በቅድስት ቤተ ክርስቲያን መዋቅሮች ግልጸኝነትና ተጠያቂነት መጥፋቱ፡-
በመምሪያዎች፣ በሀገረ ስብከቶች፣ በወረዳ ቤተ ክህነትና በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያለው አሠራር ግልጸኝነትና ተጠያቂነት የለውም፡፡ ከዚህም የተነሣ የሰው ሀብት፣ የፋይናንስና የንብረት አስተዳደሩ ሁሉም በራሱ አሳታፊ፣ ግልጽ እና ከአድልዎ የጸዳ በሆነ መንገድ አለመመራቱ፤ ሙሰኞች፣ ፖለቲከኞች፣ አማሳኞች፣ ያልተማሩ እና ቤተ ክርስቲያኒቱን በውል የማያውቋት፣ ጥቅመኞች፣ መናፍቃን ሳይቀሩ በመዋቅሩ ተሰግስገው እንዲዘርፏት፣ ስሟ እንዲጠፋ፣ ትክክለኞቹ ልጆቿ አንገት እንዲደፉና ከመዋቅሯ እንዲገፉ፣ ምእመናንም እንዲያፍሩና እንዲሸማቀቁ በር የከፈተ መሆኑ ነው፡፡ ይህም ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመፍጠሩም በላይ ሲኖዶሳዊቱን ልዕልናው እንዲጠፋ፣ ውሳኔውም እንዳይከበር አንድ ምክንያት ሆኗል፡፡
ሐ. ምእመኑ ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ የመጣውን መንፈሳዊ ዕውቀቱን ለትችትና ለነቀፋ መጠቀሙ ወቅቱ ምእመኑ በተለይም ወጣቱ ትውልድ አንጻራዊ መንፈሳዊ ዕውቀት በንባብም በትምህርትም በልዩ ልዩ መንገድ ያገኘበት ነው፡፡ የሚያውቀውን የሚኖርበት የሕይወት ለውጥ አምጥቷል ማለት ባይቻልም፡፡ ነገር ግን ያወቀውን ዕውቀት አባቶቹን ለመተቸትና ለማቃለል ምክንያት ሆኖታል፡፡ ይህም በራሱ በአሁኑ ወቅት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ፈተና እየሆነባት ይገኛል፡፡ ምክንያቱም አባቶችን ነቅፎ ለነቀፋ እየሰጠና ክብረ ክህነትን እያዋረደ በመሆኑ ነው፡፡ ምንጭ፡- ማኅበረ ቅዱሳን
