መቀመጫውን ኒዮርክ ያደረገው የጋዜጠኞች ተከላካይ ኮሚቴ በእንግሊዝኛ ምህጻሩ ሲፒጄ ለስድስት ሃገራት ጋዜጠኞች እውቅና ሰጠ። 16ቱ የታሰሩ ኤርትራውያን ጋዜጠኞች ናቸው። ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተው ዓለም አቀፍ ተቋም ኢትዮጵያው ውስጥም በእስር ላይ የሚገኙ አምስት ጋዜጠኞችን እንዲፈቱ ለሀገሪቱ ባለሥልጣናት ጥሪ አቅርቧል።
«ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም» CPj
ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ በ36ኛው ዓመታዊ የፕሬስ ነጻነት ሽልማት መርኀግብሩ ከስድስት ሃገራት ለተመረጡ ጋዜጠኞች ክብርና እውቅና ለመስጠት መዘጋጀቱን ይፋ ያደረገው ትናንት ነው።
በመጪው ዓመት ኅዳር ወር አጋማሽ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የፕረስ ነጻነት ቀን ሽልማት በመስጠት የሚያከብረው የኮሎምቢያ፤ ኤርትራ፤ ኤል ሳልቫዶር፤ ሀንጋሪ፤ ሊባኖስ፤ እና ምያንማር ጋዜጠኞችን እንደሚሆንም አመልክቷል።
ሲፒጄ ስለኤርትራ ፕረስ ይዞታ
ሲፒጄ እንደሚለው ኤርትራ ውስጥ ገለልተኛመገናኛ ብዙኃን ከታፈነ እና አንዳንድ ጋዜጠኞችም ከታሠሩ በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 25ኛ ዓመት ደፈነ። እንደ ተቋሙ በተለይ በጎርጎሪዮሳዊው 2001 ዓ,ም መስከረም 18 ቀን ለኤርትራ ፕረስ «ጥቁር ማክሰኞ» ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ነው።
በዚህ ዕለት የሀገሪቱ መንግሥት የግል የነበሩ ጋዜጠኞችን ዘጋ። በቀጣይም አማኑኤል አስራት፤ ዳዊት ይስሐቅን ጨምሮ 16 ጋዜጠኞችን አሰረ።
የታሰሩት ጋዜጠኞች ክስ አልተመሰረተባቸውም፤ ወይም ለፍርድ አልቀረቡም። ሆኖም ከቤተሰቦቻቸውም ሆነ ከጠበቆች ጋር እንዳይገናኙ ተደርገው መታሰራቸውንም ሲፒጄ ዘርዝሯል።
የእነዚህን እስረኛ ጋዜጠኞች ጤና፤ የእስር ሁኔታም ሆነ በሕይወት መኖራቸውን በተመለከተ ምንም ዓይነት ከገለልተኛ ወገን የተገኘ መረጃም እንደሌለም ድርጅቱ ገልጿል።
1996 በኤርትራ የፕረስ አዋጅ ሲታወጅ የመጀመሪያውን የግል ጋዜጣ ማተም መጀመሩን የገለጸልን ጋዜጠኛ መሀሪ አብርሐም፤ በሙያው ምክንያት ለስደት ከተዳረገ 25 ዓመት አልፎታል።
በሲፒጄ እውቅና የተሰጣቸው ከታሰሩት አብዛኞቹ የሙያ ባልደረቦቹ በሕይወት እንደሌሉ ነው የሚታወቀው ነው የሚለው።
የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ይዞታ ተንታኝ የሆኑት አብዱራህማን ሰይድ ኤርትራ ውስጥ አንድ ሰው ሲታሰር የታሰረበት ምክንያትም ሆነ ያለበት ስፍራ አይታወቅም ይላሉ።
ኤርትራዊው ስደተኛ ጋዜጠኛ መሐሪ በበኩሉ የሙያ አጋሮቹ የታሰሩት በመጀመሪያ እምባትካላ በሚባል ስፍራ እንደነበር ከዚያም በጎርጎሪዮሳዊው 2003 ዓም ፍሰኃዬ ጆሽዋ የሚባል ጋዜጠኛ የራሱን ሕይወት ካጠፋ በኋላ አዲስ ወደ ተሠራ ከአስመራ ምጽዋ መንገድ ኤራዊሮ በሚባል ቦታ መታሰራቸን ለዶዴ ቬለ ገልጿል።
የስደተኛው ኤርትራዊ ጋዜጠኛ ምልከታ
የዛሬ 26 ዓመት ገደማ ከኤርትራ ለመሰደድ ግድ እንደሆነበት ለዶቼ ቬለ የገለጸው ጋዜጠኛ መሐሪ የሀገሪቱን የፕሬስ ነጻነት ይዞታ በሚመለከት ሲናገር፤ «ከዚያ ወዲህ ኤርትራ ጨለማ ውስጥ የምትገኝ ሀገር ናት። የመናገር፤ የማሰብ፤ የመጻፍና ሌላ ኢንፎርሜሽን የሌለባት ሀገር እና እስካሁንም ኢንተርኔት የሌለባት ሀገር ናት።» ነው ያለው።
የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ይዞታ ተንታኝ የሆኑት አብዱራህማን ሰይድ በበኩላቸው ኤርትራ ውስጥም ምንም ዓይነት የመረጃ ነጻነት አለመኖሩን ነው የሚገልጹት። ይህንንም ዓለም አቀፍ የፕሬስና የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪዎች በየጊዜው እንደሚገልጹትም ነው ያመለከቱት።
ጋዜጠኛ መሐሪ እና እንደ እሱ እስርም ሆነ ሞትን ሸሽተው ለስደት የተዳረጉ የሙያ አጋሮቹ ስዊድን ላይ ተሰባስበውባቋቋሙት ዓለም አቀፍ እውቅና ባለው በስደት የሚገኙ የኤርትራ ጋዜጠኖች ማኅበር አማካኝነት መረጃን ለማድረስ እንደሚሞክሩም ይናገራል።
ሲፒጄ በእስር ላይ ለሚገኙ 16 የኤርትራ ጋዜጠኞች እውቅና መስጠቱ እንደእሱ አገላለጽ ቢዘገይም ለእነሱም ለቤተሰቦቻቸውም ትርጉም ያለው ነው።
እንዲያም ሆኖ ጋዜጠኞች በሚል ስማቸው በሲፒጄ ከተጠቀሱት መካከል ምንም እንኳን እነሱን እስር ቤት የሚገኙ ቢሆኑም በዚህ ሙያ ውስጥ እንደሌሉና ማስተካከያውን ለድርጅቱ እንደሚያሳውቅም ገልጾልናል።
እውቅና የተሰጣቸው ጋዜጠኞች ተምሳሌትነት
ከተጠቀሰው ዓመት ወዲህም የኤርትራ የመገናኛ ብዙኃን ይዞታ እንዳላገገመ የሚገልጸው ሲፒጄ በዚህ ጊዜ ውስጥ ያደገው ትውልድ መንግሥት ከሚቆጣጠረው መገናኛ ብዙኃን ሌላ እንደማያውቅም አመልክቷል።
ሲፒጄ የዘንድሮው ተሸላሚዎች በመላው ዓለም ጋዜጠኞች ለሙያቸው ያላቸው ቁርጠኝነትና ድፍረት ተምሳሌት እንደሆኑ የሲፒጄ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጆዲ ጊንስበርግ መናገራቸው ተጠቅሷል።
ጋዜጠኞቹኢላማ መሆናቸው፤ መታሰራቸው፤ ለስደት እና ስለላ መዳረጋቸውን ያመለከቱት ጊንስበርግ፤ ለእነሱ እውቅና መስጠትና እውነታውን ለታሪክ ሰንዶ ማስቀመጡ በራሱ ክብር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሲፒጄ ከትናንት በስተያ ባወጣው መግለጫ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የዛሬ ሦስት ዓመት በነሐሴ ወር ለእስር የተዳረጉ አምስት ጋዜጠኞችን በስም ዘርዝሮ ባለሥልጣናት ከእስር እንዲለቋቸው ጥሪ አቅርቧል።
ሲፒጄ ጋዜጠኛ ገነት አስማማው፤ ጎበዜ ሲሳይ፤ መስከረም አበራ ፤ አባይ ዘውዱ እና ዳዊት በጋሻው አማራ ክልል ስለተከሰተው አለመረጋጋት በመዘገባቸው መታሰራቸውን አመልክቷል። እስረኞቹ በሽብር የተከሰሱ መሆናቸውን የጠቀሰው ድርጅቱ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የሞት ቅጣት ይጠብቃቸዋል ብሏል።
«ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም» ያለው ሲፒጄ ታሳሪዎቹ ከፍርድ በፊት መታሰራቸው እና በተራዘመው የፍትህ ሂደት ምክንያት ሳይፈረድባቸው እየተቀጡ እንደሆነም አመልክቷል።
ሲፒጄ ባለሥልጣናት ጋዜጠኞችን እንደአሸባሪ መያዝ እንደሌለባቸው በማመልከትም አፋጣኝ ሚዛናዊ እና ግልጽ የፍትህ ሂደት እንዲኖርና በፍትህ ሂደቱም መብታቸው እንዲከበር እንዲያደርጉ ጠይቋል።
DW
