ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት መንግሥት በጠባብ ቀዳዳ የምታየውን የፖለቲካ ምኅዳር ጭራሹን እንዳያጠፋና ሰሞኑን ያሰራቸውን ሰላማዊ የፖለቲካ ታጋዮች ያለቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ ጥሪ አቀረበ።
ትብብሩ ባወጣው መግለጫ፤ እንደ አበበ አካሉ፣ ይስኃቅ ወልዳይ እና ጠበቃ አበራ ንጉሥ ያሉ ሰላማዊ ታጋዮች ለእሥር መዳረጋቸው በፖለቲካ ምኅዳሩ ላይ ትልቅ አሉታዊ ጫና ማሳደሩንና ህዝቡንም ማስደንግጡን ገልጿል።
ድርጊቱ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 በነፃ የመናገርና ሀሳብ የመግለጽ መብት ጋር እንደሚጋጭ የጠቆመው መግለጫው፤ “ከውዳሴ ውጪ ተቃውሞ እንዳይሰማ ማሳደድ እንደ መርኅ እየተያዘ ይሆን?” ሲል ጠይቋል።
በተጨማሪም የሰላማዊ ትግል በሮችን በመዝጋት ሌሎች አማራጮች እንዲስፋፉ የሚሠራ አካል መኖሩን እንደሚያስጠረጥር በመግለፅ፣ መንግሥት ሁኔታውን ተገንዝቦ የታሰሩትን የፖለቲካ ታጋዮች በአስቸኳይ እንዲፈታ አሳስቧል።
