ስለዝዋይ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተነገረው እና እውነታው!

Date:

በመጋቤ ብሉይ ቆሞስ አባ አትናቴዎስ

‹‹ተግትን እንጸልይ ወደፈተና እንዳንገባ ››

‹‹በህይወታችን በመንገዳችን እግዚአብሄር ይግባ››

ዘንድሮ ዐይኑን አፍጥጦ፥ጥርሱን አግጥጦ የመጣ ውን ችግር ለመመለስ ያለ ዕረፍት መልስ መስጠት ተገቢ ነው።

በቅዱስ ሲኖዶሱ ተወግዘው ከዲቁና እስከ ሊቀ ጵጵስና የነበራቸውን ሥልጣን የተገፈፉት አባቶች ስለ ዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና መንፈሳዊ ኮሌጅ በአደባባይ የተናገሩትን ሐሰት የሚ ገላልጥ እውነት። ሐሰት ጨለማ፥ እውነት ብርሃን ነውና (የጸሐፊው ዓላማ ዘር መቁጠር ሳይሆን እሾ ህን በእሾህ እንዲል ኮሌጁ ከትናንት እስከ ዛሬ ከአራቱም ማዕዝን የሚመጡ የቤተ ክርስቲያንን ልጆች በእኩል እንደሚቀበል ፍንትው አድርጎ ማሳየት ነው። ከዚህ በተረፈ ከኦሮምያ ክልል መግባት ያለባቸው ቋንቋ በመቻል ብቻ ሳይሆን የግድ ደማቸውም የኦሮሞ መሆን አለበት የሚሉትን ዘመድ ካለ ወደ ጠበል መውሰድ ነው። ምክንያቱም ክርስቲያን ሆኖ እንዲህ ማሰብ እብደት ነውና)። እስከዚህ ያለው የኔ አስተያ የት ነው። መልካም ንባብ ይሁንላችሁ።

የዝዋይ ገዳም ኮሌጅ የተመሠረተው ለማን ነው?         

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ካሉ አምስት ኮሌጆች አንዱ የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና ሥራ አመራር መንፈሳዊ ኮሌጅ ነው፡፡ ኮሌጆች ሲመሠረቱ ሀገር አቀፍና ዓለም ዓቀፍ ርዕይ ይዞ ነው የትኛውም ተቅዋም በቤ ክርስቲያን ሲመሠረት ምዕመናንን ማዕከል ያደረገና የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ አምልኮት ሳይዘነጋ ነው፡፡

የዝዋይ ቅዱስ ገብርኤል ገዳምን አጭር የታሪክ ዳሰሳ በሌላ ክታብ እንመለሳለን። አሁን ግን ኮሌጁ እየሰጠ ያለውን ሰፊ አገልግሎት ለመጠቆም ነው። የዝዋይ ገዳም በ1959 ዓ/ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍ ሎስ የተመሠረተ ሲሆን በ1960 ዓ/ም ማስተማር ጀምሯል። በ1966 የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ ተዘግቶ ቆይቷል። በ1971 በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ አማካኝነት ዳግም ተከፍቷል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሺ የሚቆጠሩ መምህራንን ለቤተ ክርስቲያን አበርክቷል። ገዳሙ ትንሿ ኢትዮጵያ ነው። የገዳሙን ውሃ ጠጥቶ፥ ሥልጠናውን ወስዶ በሳል ሰባኪ ያልሆነ የለም። በመላው ዓለም ያለችውን ቤተ ክርስቲያን በማገልገል ያሉ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ቆሞሳት፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ ካህናት እና ዲያቆናት ምስክር ናቸው። በዝዋይ ገዳም ዘር ቀለም የለም። በዝዋይ ገዳም የሚያድጉ ወላጅ አጥ ሕፃናት ከሁሉም ቤተ እምነት መጥተው ነው የሚያድጉት። ቀደምት የነበሩ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በአካለ ሥጋ የሌሉ በነፍሳቸው ምስክር ናቸው። በአካል ያሉ በበረከት ሕዝቡን እየጠበቁ ያሉ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ከዐሥር በላይ ናቸው፡-

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ

ብፁዕ አቡነ ማርቆስ

ብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስ

ብፁዕ አቡነ ኤልያስ

ብፁዕ አቡነ ድዮስቆሮስ

ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ

ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ

ብፁዕ አቡነ ናትናኤል

ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዘአሜሪካ

ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ

ብፁዕ አቡነ በርናባስ

እኔ የማስታውሳቸው ብፁዓን አባቶቼ በአካለ ሥጋ ያሉት እነዚህ አበው ጥቂቶቹ ናቸው። ሌሎቹንም ጨምሮ ከብዙዎቹ መካከል ጥቂቶቹ መምህራን:-

መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ፤

ቀሲስ እሸቱ ታደሰ ወንድም አገኝ፤

ቀሲስ አሸናፊ ዱጋ ዋቄ፤

ቀሲስ ታደሰ ዱጋ ዋቄ፤

መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው በላቸው፤

መልአከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ዳርጌ፤

ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን፤

መምህር ጳውሎስ መልክዓ ሥላሴ፤

ዶ/ር ዲያቆን ታሪኩ ኤገኖ፤

ዶ/ር አባ ጴጥሮስ ዘምስካዬ ኅዙናን፤

የትኛውን ጠርቼ የትኛውን ልተው፣…ብቻ ቤተ ክርስቲያንን በልዩ ልዩ መንገድ እየጠበቁ ያሉ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአረብ፣ በአፍሪካ፣ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የዝዋይ ፍሬዎች የሌሉበት የለም፡፡ ይህ ማለት ገዳሙ ሀገር አቀፍም ዓለም አቀፍም ነው ማለት ነው። ለዚህም በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚያስተምሩ የገዳሙ ልጆች ምስክር ናቸው፡፡ በኮሌጁ ላይ ሰሞኑን ስለ ቀረበበት የሌለ ክስ ኮሌጁ ለማን ነው የተመሠረተው? በቋሚነት የቤተ ክርስቲ ያንን ችግር ፈቺ ትውልድ ማፍራት ነው። ዓላማው በተለይ የቤተ ክርስቲያን ሰው  ቤተ መቅደስ ገብቶ የሚቀድስ፥ቅኔ ማኅሌት ገብቶ ከመምህራኑ ጋር የሚያገለግል ዐውደ ምሕረት ወጥቶ የሚሰብክ የሚያጽ ናና፥ቢሮ ገብቶ የሚያስተዳድር የሚመራ እንዲሆን ማድረግ ነው። የዝዋይ መንፈሳዊ ተቋም ዓለማ ለዚህ ምቹ ዕድልን የፈጠረ ነው። በገዳሙ የሚያድጉ ሕፃናት፡-

1ኛ/ ቁጥር ንባብ ዳዊት እንዲማሩ ይደረጋል፤

2ኛ/ በመቀጠል ዜማ እንዲማሩ ይደረጋል፤

3ኛ/ ቅዳሴ እንዲማሩ ይደረጋል፤

4ኛ/ ቅኔ እንዲማሩ ይደረጋል፤

5ኛ/ አቋቋም እንዲማሩ ይደረጋል፤

6ኛ/ ኮርስ እንዲሰለጥኑ ይደረጋል፤

7ኛ/ ዘመናዊ ትምህርትን ዝዋይ ከተማ ተመላልሰው እንዲማሩ ሳይክል ተገዝቶላቸው ይማራሉ፤

8ኛ/ ወደ ልዩ ልዩ ተቋማት ገብተው ይማራሉ፤

9ኛ/ ወደ አገልግሎት ይሰማራሉ፤

ይህ ገዳም እነዚህን ትምህርቶች ለሁሉም ኢትዮጵያ ውያን ሲሰጥ ቆይቷል።አሁንም እየሰጠ ይገኛል፥ይሄ መሬት ላይ ያለ ሐቅ ነው። ማሰልጠኛው ወደ ኮሌጅ ካደገ በኋላ ስንት ተማሪዎችን ተቀበለ? ከማሰልጠኛ ወደ ኮሌጅ ያደገው በብፁዕ አቡነ ጎርጎ ርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከፍ ተኛ ደካምና ጥረት ሲሆን፡- የተወሰነው በ2010 ዓ/ም በጥቅምት ሲኖዶስ ነው፤ በ2011 ዓ/ም ያልተሟሉ ነገሮችን እያሟላ ቆይቶ በ2012 የኮሌጁ አመራሮችን ከመደበ በኋላ ቅበላ ጀምሯል።

እውነታውን እንመልከት  

  • በ2012 የተቀበላቸው 26 ናቸው። 15ቱ ከኦሮሚያ ክልል ሌሎቹ ከልዩ ልዩ አኅጉረ ስብከት፤
  • በ2013 የተቀበላቸው 21 ናቸው። 10 ተማሪዎች ከኦሮሚያ ቀሪዎቹ ከሌሎች አኅጉረ ስብከት፤
  • በ2014 የተቀበላቸው 22 ናቸው። 10 ተማሪዎች ከኦሮሚያ ክልል ቀሪዎቹ ከሌላ፤
  • በ2015 የተቀበላቸው 22 ናቸው። 12 ተማሪዎች ከኦሮሚያ ክልል ቀሪዎቹ ከሌላ፤

የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች በቋንቋው ማስተማር የሚችሉ ማለት ነው። የሐዲስ ኪዳን ተማሪዎችንና ከፍሬምናጦስ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወስኖ የገቡትን ሳይጨምር ያለውን የመደበኛ ተማሪዎች ዳታ ነው ያቀረብኩት። ይህ ማለት በኮሌጁ የሚማሩ አብዛኛውን ተማሪዎች ከኦሮሚያ ክልል አኅጉረ ስብከቶች ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝ ማረጋገጫ ነው፡፡ ይህንን እውነታ የትም ልንፍቀው አንችልም። የኮሌጁ ሬጅስትራር ክፍል መጥቶ መረጃውን መመልከት ይቻላል።

በመስፈርቱ የተቀመጠው፡- ቢቻል ቢገኝ ይመረጣል ተብሎ እንጂ ከየትኛውም የኦሮሚያ ሀገረ ስብከት ዲቁና እና 10ኛ ክፍል ከ2:00 ነጥብ በላይ የያዘ ተማሪ ተልኮ ተመልሶ አያውቅም። ይህ ደረቅ ውንጀላ ነው፡፡

የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስን የሁሉ አባትነት የምሥራቅ ሸዋ ምድርና የገዳሙ ልጆች ይመስክሩ። እኔን ባታምኑ በሥራዬ እመኑ ብሏል ጌታ። ሠርቶ ማሳየት እየተቻለ በተሠራው ላይ ጥላሸት መቀባት ግን ቤተክርስቲያናዊ ምግባር አይደለም። አንድ ሰው ትልቅ ነው፥ አስተ ዋይ ነው የሚባለው ለሚናገረው ሁሉ በመረጃና በማስረጃ ሲያደርግ ነው። ካልሆነ ግን ለጊዜው እንጂ ነገሩ ውሃ አይቋጥርም። ዝዋይ ገዳም ለማን ተመሠረተ? ለቤተ ክርስቲያን ልጆች። ኮሌጁስ ለማን ተመሠረተ? የቤተክርስቲያንን ችግር መፍታት ለሚችሉ፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንን ወርቃማ ውሳኔ የወሰነው በኦሮሚያና በደቡብ ክልል ያለውን የምዕመናን ፍል ሰት ለመታደግ ነው። ሌላው ኮሌጁ በዝዋይ ገዳም እንዲሆን የተፈለገው ገዳሙ ካሁን ቀደም ካፈራው ፍሬ በመነሣት ነው። ሌሎቹም አባቶች በሀገረ ስብከታቸው የሚገባ ሥራ ሠርተው በምሁራን አስጠንተው ማሠልጠኛንም ኮሌጅንም መክፈት ይችላሉ። በዚህ መንገድ ስንጓዝ ነው ማትረፍ የምንች ለው።

በዝዋይ ገዳም ግን አሁንም ገና ተሠርቶ ያላለቀ ሥራ አለብን። ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ባለ ራዕይ ናቸው። ሌላ የትምህርት ማዕከል ለመመሥረት እንቅስቃሴ ላይ ናቸው። የመሠረት ድንጋይም ጥለዋል።

በዝዋይ ከተማም G+3 መንታ ፎቅ ለመሥራት ካቀዱ ቆይተዋል። ይህ ተቅዋም በዝዋይ ከተማ ባለው ሰፊ የገዳሙ ይዞታ ላይ የሚሠራ ሲሆን በሲሚንቶ እጥረት ምክን ያት ነው የዘገየው። በቅርብ ይጀመራል፡፡

——————

ማስታወሻ፡- ጸሐፊው መጋቤ ብሉይ ቆሞስ አባ አትናቴዎስ የገዳሙ ርዕሰ መምህርና የኮሌጁ የቦርድ አባል ናቸው፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...

“ሎዛ ዘፀአት”እና “የሎዛ ድርሳናት”ተከታታይ ረጅም ልቦለድ መጻሕፍት ተመረቁ

በጋዜጠኛና ደራሲ መርዕድ እስጢፋኖስ የተጻፉት ሎዛ ዘፀአት(2014 ዓ.ም) እና...