ጌታቸው ስሜ፣ ኢንግላንድ
“ህይወቴ ከቆቆ እስከ ከርቸሌ” በሚል ርዕስ ታትሞ ለንባብ የበቃው ግለ ታሪክ መፅሀፍ በይዘቱ የደራሲውን ከውልደት እስከ ከርቸሌ እስር ቤት ያለውን ህይወት ያካተተ ነው፡፡ መፅሀፉ በውስጡ ሳቢና አዲስ ነገር ይዟል፡፡ በተለይ የደራሲውን የትውልድ ቦታ ሰሜን ሸዋን ባህል፣ አኗኗር፣ ወግና ስርዓት በጥልቀትና ስዕላዊ በሆነ መንገድ በመግለፅ ረገድ በደንብ የተደራጀና በጥልቀት ያብራራ መጽሐፍ ነው፡፡
ደራሲው ተድላ ድረሴ የመፅሀፋቸውን ታሪክ ያሟሹት በታጠቁ ኦሮሞዎች በ1930 ዓ.ም አካባቢ በሰሜን ሸዋ ህዝብ ላይ የተፈፀመ ወረራ ብለው የጠቃቀሱት አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም፡፡ እሳቸው ምክንያት የሚያደርጉት “በዚያኛው ጎራ ሲነገር እኛ ዝም አልን፤ ዝም በማለታችን ተጎድተናል” ባይ ናቸው፡፡ ይህ ማለት በዚያኛው ጎራ ተፈፀመ የተባለው ትክክል ነው ብለው አምነዋል፡፡ ይህ የቁርሾ ሀተታ በየዘመኑ እየቆሰቆሱ ማንሳት ሁሉም ነገር በጎሳ በሚመዘንበትና ውጥረት በነገሰበት አገር ውጥረቱን ያንረዋል እንጂ ፋይዳ የለውም፡፡ አንዳርጋቸው ፅጌ “ትውልድ አይደናገር፤ እኛም እንናገር” በሚል ባሳተሙት መፅሀፍ ከፋሺስት ጣሊያን ጋር በተደረገው ጦርነት የሙስሊም ሬሳ በሰሜን አልተቀበረም ነበር ብለው ያሰፈሩት በሰፊው ተተችቷል፡፡
ደራሲው ተድላ ድረሴ በትረካቸው የእናታቸውንና የእሳቸውን ጥብቅ መፈላለግና ናፍቆት ልብ በሚነካ መንገድ ገልፀውታል፡፡ በሁላችንም ወላጆች ላይ የምናየውን የእናትና ልጅ ናፍቆት ፍንትው አድርገው አሳይተዋል፡፡ ደራሲው የኢህአፓ አባል በነበሩበት ጊዜ በደረሰባቸው ውጣ ውረድ በወቅቱ ወላጆች እንዴት ይጨነቁና ይሰቃዩ እንደነበር በትረካቸው አሳይተውናል፡፡ የተፈፀመው ጭካኔ በወላጆች ላይ መጥፎ ጠባሳ አሳርፎ አልፏል፡፡ ለዚህም አንደ አብነት ተራኪው ስለ አንድ ጓደኛቸው አሟሟት የገለፁበት እጅግ ልብ ይነካል፡፡ የአቶ ተድላ እናትና የሟቹ የአለማየሁ እናት እጅግ የሚዋደዱ ወዳጆች ናቸው፡፡ አቃቂ አካባቢ ጉረቤታሞች ናቸው፡፡ አይለያዩም፡፡ ደራሲው ለእናታቸው አንድ ናቸው፤ አለማየሁም ለእናቱ አንድ ነው፡፡ አለማየሁ ከተደበቀበት ድንገት ወደ እናቱ ቤት አቃቂ እየሄደ ሳለ በአብዮት ጠባቂዎች ይያዛል፡፡ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እየወሰዱት እያለ፤ ከያዙት አብዮት ጠባቂዎች ተፈናጥሮ በመሮጥ ዘሎ ዋናው መንገድ በሚሄድ ከባድ መኪና ጎማ ስር ራሱን ወርውሮ እሬሳው ለመለየት እስኪያስቸግር ድረስ አሟሟቱ አሳዛኝ እንደነበር የተረኩበት ክፍል ልብ ይሰብራል፡፡ የሚገርመው የሟቹ የአለማየሁ እናት ልጃቸው በእንደዛ ሁኔታ መሞቱን አያቁም፤ ያወቁ ሰዎችም ይጎዳሉ በሚል ሳይነግሩአቸው፤ ልጃቸው አንድ ቀን ይመጣ ይሆን በሚል ተስፋ በሀዘን እንደተቆራመዱ መሞታቸውን ስናነብ እናዝናለን፡፡ ይህ በብዙ ወላጆች ላይ እንደደረሰ መገመት አያዳግትም፡፡
ፀሀፊው በሰሜን ሸዋ ሞላሌ ተብሎ በሚጠራው ገጠራማ ቀበሌ ትምህርታቸውን የተከታተሉበትን አካባቢ እንዲሁም ተወልደው ያደጉበትን ቆቆ የምትባል ቦታ እጅግ በሚመስጥ ሁኔታ ተርከውታል፡፡ በወቅቱ ከውጪ አገር የሚመጡ በተለይ ህንዳውያን መምህራን መኪና በማይደርስበት እጅግ አስቸጋሪ ጉዞ ተጉዘው ከከተማ እጅግ በራቁ የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ያስተምሩ እንደነበር ስንገነዘብ ጥንካሬያቸውንና ፍላጎታቸውን ሳናደንቅ አናልፍም፡፡ ደራሲው ቦታንና ስፍራን በስዕላዊ መንገድ የመቅረፅና የማሳየት ችሎታቸው ይደነቃል፡፡ በመፅሀፋቸው የተወሰኑ ገጾችም ፎቶግራፎች ተጠቅመዋል፡፡ በተለይ በሰሜን ሸዋ እሳቸው ያደጉበትን ማህበረሰብ በመግለፅ ረገድ መፅሀፋቸው የሚያጠግብ መረጃ ዘርግፏል፡፡ ለአንትሮፖሎጂና ለማህበራዊ ሳይንስ አጥኚዎች ዳጎስ ያለ መረጃ ያጨቀ መፅሀፍ ነው፡፡
በዚሁ ማህበረሰብ ብቀላና ደም መመላለስ ምን ያህል ስር ሰዶ የባህሉ አካል እንደሆነ እናያለን፡፡ ቀደም ሲል በደራሲ አንዳርጌ መስፍን የተፃፈው “ጥቁር ደም” የበርካታ አንባቢዎችን ቀልብ የሳበው በሰሜን ሸዋ ባሉ ማህበረሰቦች ብቀላ እስከምን ድረስ እንደሆነ በዝርዝር ተርኮ ስላሳየ ነው፡፡ አቶ ተድላም ብቀላና ደም መመላለስ የማህበረሰብ ወግና ጀግንነት ተደርጎ የተወሰደበትን አስተሳሰብ፣ ባህላዊ ግዴታ፣ የስነ ልቦና ሁኔታ በራሳቸው ቤተሰብ ውስጥ የተከናወነውን ብቀላ በዝርዝር እየተረኩ ያሳዩናል፡፡ ለብቀላ ቤተሰብ በእንቅልፍ ወድቆ ቤቱን እስከማቃጠል ይደርሳል፡፡ ደምን በደም ለመመለስ ከወገንና ከቤተሰብ ራስን ነጥሎ በረሀ ለበረሀ በገደላ ገደል መኖር እንደ ወግና ጀግንነት የሚቆጠርበት ማህበረሰብ ውስጥ ልጅ ያለ አባት፣ ሚስት ያለባል፣ ቤተሰብ ያለመረጋጋት ኑሮ ሲገፋ ማህበረሰባዊ ቀውሱ የብዙዎችን ህይወት አንዳመሰቃቀለ መረዳት ይቻላል፡፡ ብዙዎቹ ይህንን የብቀላ ግድያ ሽሽት ወደ ሩቅ አገር ወይም አዲስ አበባ ይሄዱና በጥበቃ ስራ ወይም በቀን ስራ ተቀጥረው ኑሮአቸውን እንደሚጀምሩ ይተርክልናል፡፡ ካገራቸው ሸፍተው የወጡ ሰዎች የት እንደሚኖሩ ለዘመዶቻቸው እንኳ አይናገሩም፡፡ እንጠቃለን የሚል ስጋት አላቸው፡፡
ደራሲው ትምህርታቸውን ለመማር ያዩትን መከራ ስናይ በወቅቱ ብዙዎቹ ተማሪዎች በዚህ መንገድ እንደተማሩ እንረዳለን፡፡ ፀሀፊው መምህር ሆነው ጋሞጎፋ ጨንቻ ሲያስተምሩ እነ ቀኝዝማች ኤልታሞንና ቀኝዝማች ሳሌን የገለፁበት መንገድ ይስባል፡፡ ጋሞዎች ፀብ እንደማይወዱ የገለፁበትን መንገድና እሳቸው ካደጉበት ፀብና ብቀላ የእለት ተእለት ህይወት ከሆነበት ማህበረሰብ ጋር ሲነፃፀር በአንድ አገር በሁለት ተቃራኒ የአስተሳሰብና የአኗኗር ዘይቤ ያለው ማህበረሰብ ያሳዩናል፡፡ በወቅቱ መምህራን የነበሩ ትምህርት ለመማር አቅም የሌላቸውን ለማስተማር ያላቸው ፍላጎት ያስደንቃል፡፡ ትምህርት የስኬት መንገድ መሆኑን በአብዛኛው ህዝብ የመረዳት ግንዛቤ ነበር፡፡ መምህርነትም እጅግ የተከበረ ሙያ አንደነበርና በህብረተሰቡም ውስጥ ያላቸወን ከበሬታ በትረካው ውስጥ ያሳዩናል፡፡
ፀሀፊው የኢህአፓ አባል ነበርኩ ባሉበት ጊዜ በመንዝ አካባቢ በድርጅቱ እንቅስቃሴ ያደረጉትን ተሳትፎም ይተርካሉ፡፡ ከመንዝ አዲስ አበባ እየተመላለሱ ከጓደኞቻቸው ጋር ለድርጅቱ የከፈሉትን መስዋዕትነት ገልፀውታል፡፡ የማርክሲዝማና ሌኒኒዝም ፅንሰ ሀሳብ ከተቀበሉና ካጠኑ በኋላ፣ በጥራዝ ነጠቅነት እንዴት የሌላውን ሀሳብ እንደማይቀበሉ በዩኒቨርስቲ አስማሪያቸውን እንዴት ይቃወሙ እንደነበር እየጠቀሱ ይነግሩናል፡፡ ይህ በወቅቱ የብዙዎቹ ወጣቶች ስሜት እንደነበር እንረዳለን፡፡ ፀሀፊው በሰሜን ሸዋ ትግል በሚያደርጉበት ወቅት በተመሳሳይ ጊዜ ከኢህአፓ ከፍተኛ አመራር አንዱ የነበረው ብርሀነመስቀል ረዳና ጓዶቹ ድርጅቱ አንጃ በሚል ከተከፈለ በኋላ ከደርግ ግድያ ሽሽት የተደበቁት ሰሜን ሸዋ ነበር፡፡ ይህንንም የብርሀነመስቀል ባለቤት ታደለች ኃ/ሚካኤል በቅርቡ ባሳተመችው “ዳኛው ማነው” በሚለው መፅሀፏ ገልፃለች፡፡ በዚህ መፅሀፏ በሰሜን ሸዋ መርሀቤቴና መንዝ ያደረጉት ውጣውረድና ትግል እልህ አስጨራሽ ነበር፡፡
አቶ ድረሴ በወቅቱ በሰሜን ሸዋ በእነብርሃነመሰቀል የተደረገውን እንቅስቃሴ በመፅሀፋቸው በአንድ ቦታ ገፅ 451 መንግስቱ ደፋር ተዋግቶ እንደሞተና ብሩኬ እጁን ለደርግ እንደሰጠ እንዲሁም ብርሃነመስቀል ተይዞ ደርግ በሄሊኮፕተር ወደ አዲስ አበባ እንደወሰደው ጠቅሰዋል፡፡ ታደለች ስለሁለቱም ታጋዮች በመፅሀፏ ምዕራፍ 18 በዝርዝር ተርካዋለች፡፡ ነገር ግን አቶ ተድላ የእነ ብርሃነ መስቀልን ትግል ሌላ ቦታ አልጠቀሱም፡፡ በአንድ አካባቢ የተለያየ ጎራ ሆነው ምንአልባትም በጠላትነት እየተያዩ ደርግን ይታገሉ እንደነበር መረዳት ይቻላል፡፡ ደራሲው የእነብርሀነ መስቀል ደጋፊ እንዳልሆኑ በትረካቸው መረዳት ይቻላል፡፡ ስለድርጅቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ሲተርኩ የእነብርሀነመስቀልንና ጓዶቹ የሰሜን ሸዋ እንቅስቃሴ ለምን በዝርዝር ሊሄዱበት አልፈለጉም የሚል ጥያቄ ያጭራል፡፡ ምክንያቱም ብርሃነመስቀል የኢህአፓ አመራር ነበር፡፡ እሳቸው ራሳቸው እንደሚነግሩን የድርጅቱ ተራ አባል ናቸው፡፡ መሪያቸው በተመሳሳይ አካባቢ እንደነበር ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን በመፅሀፉ አንድ ገፅ ውስጥ ከማውሳት ሌላ በየትም የሰሜን ሸዋ ትግል በሚያነሱበት ቦታ ሳያነሱ አልፈውታል፡፡
ሌላው ፀሀፊው የሚተቹት የጎሳ ክፍፍልን ነው፡፡ ለአገራችን በጎ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ያነሳሉ፡፡ በጣምም እንደሚጠየፉት ይናገራሉ፡፡ በመፅሀፋቸው ገፅ 285 “ዋለልኝ መኮንን የብሄር ጥያቄን ከነጆሴፍ ስታሊን ቀድቶ አገራችን ላይ ተከለ” ይሉና “እሱ (ዋለልኝ) ይህንን ያደረገው እኩልነትን ለማስፈን አስቦ ነው” በማለት ይከራከሩለታል፡፡ አንድ ሀሳብ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ አደገኛ ከሆነ ተግባራዊ ሲሆንም አደገኛ ይሆናል፡፡ የብሔር ጥያቄ የተነሳበት መንገድ ትክክል ነው ቢባል እንኳ፤ ውሎ አድሮ በማህበረሰባችን ውስጥ ተግባራዊ ሲሆን ምን ያስከትል ይሆን የሚለውን ለመፈተሸ አለመሞከር የሀሳቡን ትክክለኛነት አያረጋግጥም፡፡ የብሄር ጥያቄ የተነሳበት መንገድ ትክክል ነበር ካሉ በኋላ በጎሳና በቋንቋ መስፈርት የተሰራው የፖለቲካ አደረጃጀት ይዞት የመጣውን ጣጣና የእርስ በእርስ ፍጅት ማወገዝ እርስ በእርሱ ይቃረናል፡፡ይልቁንም “ሲጀመርም ትክክል አልነበረም፤ መጨረሻውም አላማረም” በሚል በሚያስተምር መልኩ ቢያነሱት ይበጃል ባይ ነኝ፡፡ ጎሳና ቋንቋ የሁሉም ነገር መጀመርያና መጨረሻ ነው ሲሉ የዚህኑ አደረጃጀት የነደፉት እነ መለስ ዜናዊና በወቅቱ የነበሩ ፅንፈኛ የግራ ሃይሎች ህይወትም መንገድም እሱ ነው ብለው ይገዘታሉ፡፡ የዚሁ ልዩነትን ማዕከል ያደረገው አደረጃጀት አሁንም እያጫረሰን ፅንፈኞቹ ብሄረተኞች ትክክል ነው ብለው ይከራከራሉ፡፡ አንድ ሰው ሌላውን ሰው ከጎዳ በኃላ ወይም ከገደለ በኋላ “የሚያስከትለው መዘዝ አልታወቀኝም” ቢል ከህግ ተጠያቂነት አያስጥለውም፡፡
ፀሀፊው አክለውም “ዋለልኝ ብሔር ብሔረሰቦች እስከመገንጠል ሲል ያወጀው ዛሬ በአገራችን ያመጣውን ችግር ቢያይ ይፀፀት ነበር” ይሉናል፡፡ አሁንም ብሄሮች ክልል በመሆን ወደ መነጣጠል እየተጓዙ መሆኑን ስናይ በእርግጥ ሊፀፀት ይችል ይሆናል፡፡ ላይፀፀትም ይችላል፡፡ በርካታ የሱ ዘመን ታጋዮች እስከአሁንም ስለትክክለኝነቱ ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኞዎቹ ከዋለልኝ ጋር ሲታገሉ የነበሩ በህይወት ያሉ ተማሪዎች አንድም ጊዜ ያነሳነው ሃሳብ ትክክል አልነበረም ሲሉ ተፀፅተው ሲናገሩ አይሰማም፡፡ ያኔም አሁንም ትክክል እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ያደረሰውን ጉዳት ለመገምገምና ለማጥናት ፍላጎት የለም፡፡ ለዚህም ይመስለኛል አሁን ላለንበት የሰከነ የፖለቲካ ሙግት ለመብቃት ያዳገተን፡፡በወቅቱ ተማሪዎች በየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ያመኑበትን ለአገራቸው ለማራመድ የሄዱበት መንግድ እጅግ ያስደንቃል፡፡ የከፈሉትም መስዋዕትነት ያስገርማል፡፡ በእርግጥም ብዙኃኑ ለስልጣንና ለራስ ፍላጎት ብለው እንዳልታገሉ እንረዳለን፡፡ ነገር ግን በአሁን መነፅር አይቶ ትውልድን የማነፅና እየተገነባ የሚመጣ ጥርት ያለ ከጥላቻ ነፃ የሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዲገነባ (Constructed political ideas) የዛው ትውልድ እንዲሀም ከእነሱ በኋላ የመጣነው ትውልዶች እዳም ነው፡፡
ፀሀፊው ለኢህአፓ ያላቸውን ፍቅር የሚገልጹበት መንገድ የፅድቅ መንገድ አድርገው ይስሉታል፡፡ ለዚህም የሚጠቅሱት አንድ ጓደኛቸው ሲከተላቸው እየሸሹት ታክሲ ውስጥ ገብተው እንዳመለጡ ይናገራሉ፡፡ ለሽሽታቸው መንስኤው ጓደኛቸው የኢህአፓ አባል እንዲያደርጋቸው ስለሚከታተላቸው እንደነበርም ይናገራሉ፡፡ በጣም የተጋነነ ነው፡፡ በወቅቱ በአብዛኛው የከተማ ወጣት ለኢህአፓ ፍቅር ነበረው፡፡ በርካቶችም አባል ሆነው ታግለዋል፡፡ ነገር ግን ያን ያህል አባል ካላረጋችሁኝ ብሎ ሰው የሚያሳድድ አለ ብሎ ለማመን ያስቸግራል፡፡ ይህንን ሳነብ ትዝ ያለኝ የአስማማው ኃይሉ “የኢህአሰ ትግል” በሚል ባሳታመው መፅሀፍ አሲምባ ያሉ የደርጅቱ ታጋዮች ለድርጅቱ የነበረው አምልኮ ከልክ ያለፈ ስለነበር ጥፋተኛ በተባሉ የድርጅቱ ታጋዮች ላይ በገዛ ጓዶቻቸው ላይ የሚወስዱትን ርምጃ ለድርጅቱ ሲሉ አንደሚያደርጉት ይነግረናል፡፡ አንድ አባላቸው ይህንን አምልኮ ከሊዎናርዶ ዳቪንቺ ሞናሊዛን ካመለከበት ጋር እንዳመሳሰለው ፅፈዋል፡፡
ህይወቴ ከቆቆ እስከ ከርቸሌ መጽሐፍ የደራሲውን የኢህአፓ ተሳትፎ ብቻ ሳይሆን በከርቸሌ ያሳለፉትን ጊዜም የሚተርክ ነው፡፡ ከርቸሌን አለም በቃኝን የገለፁበት ስዕላዊ ምስል ከሳች ትረካ እጅግ የሚደነቅ ነው፡፡ በርካታ ፀሀፍት ስለ ከርቸሌ ፅፈዋል፡፡ የአቶ ተድላ ተጨማሪ መረጃ ያከሉበት ስለሆነ የበለጠ እንድረዳው ያደርገናል፡፡ ስለዚሁ እስር ቤት ሲያነሱ በትረካው መሀል ስለአንድ እስረኛ የገለፁት አስቆኛል፡፡ እስረኛው በእስረኛ መጠየቂያ ሰዓት ሚስቱ ልትጠይቀው ስጥመጣ ካዋራችው በኋላ፤ እስረኛው ሚስቱን አንዴ ፊቷን አዙራ ራመድ እንደትል ይጠይቃታል፡፡ ጀርባዋን ወደ ባሏ አዙራ ስትራመድ ከኋላዋ ካያት በኋላ፤ በንዴት የያዘውን እቃ ወደ መሬት ይፈጠፍጠዋል፡፡ የሚስቱ ናፍቆት ከቁጥጥሩ በላይ ሆኖበት ነው፡፡ ፀሐፊው መጽሐፉን ለማዘጋጀት የተጠቀሙባቸው ዋቢ መጽሐፍት የተነሱበትን ዓላማ ለማሳካት በጥንቃቄ የተመረጡ ናቸው፡፡ መፅሀፉ በቅርፅ ረገድ በሚገባ የተሰናዳ ነው፡፡ በተለይ እኔን ያስደመመኝ ስለአደጉበት መንዝ የገለፁበት የትረካ ክፍል ለዘጋቢ ፊልም ግብዓት የሚሆን ነው፡፡ የትረካ ችሎታቸውን በሚገባ ያሳያል፡፡ አቶ ተድላ የስነ ልቦና ባለሙያ ስለሆኑ ማህበረሰቡን ከስነ ልቦናናና ባህል አንፃር ምርምር አድርገው ሌላ ጠለቅ ያለ መረጃ የያዘ መፅሀፍ እንደሚያስነብቡን ተስፋ አለኝ፡፡ የአተራረክ ችሎታቸው እጅግ የሚመስጥ ነው፡፡ መፅሀፉን አሰፋ ጨቦ እንደሚለው (Mandatory Reading) ማንም ሰው ሊያነበው የሚገባ መጽሐፍ ነው፡፡
