የፓን አፍሪካን የንግድ እና ኢንዱስትሪ ም/ቤት አመሠራረት፣ ዓላማና አጠቃላይ እንቅስቃሴ አስመልክቶ ከአቶ እሸቱ ደስታ ጋር የም/ቤቱ ከፍተኛ ፕሮግራም ኃላፊ ከሆኑት ከወይዘሪት ዊንኬት ሙቲኒ ጋር የተደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው ተቀናብሮ ቀርቧል፡፡ መልካም ንባብ!
ለምክር ቤቱ የአፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ከሚለው ስያሜ “ፓን” የሚለው ለምን ተመረጠ? የምክር ቤቱ መቋቋም ቁልፉ ጉዳይስ ምንድነው ይላሉ?
ዊንኬት፡- የንግድ ምክር ቤቱ ስም “ፓን” የሚለው የተመረጠው ታሪክን ለማስታወስ አይደለም፡፡ ስሙ የአፍሪካ አህጉርን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አፍሪካውያንን ሁሉ የሚያጠቃልል በመሆኑ ነው ይህ ሥያሜ የተሰጠው፡፡
ምክር ቤቱ መቼና በስንት አባላት ተመሰረተ? አሁንስ ያሉት የአባላት ቁጥርስ?
ዊንኬት፡- አባላቱን የምናየው በሀገራት ደረጃ ነው፡፡ ሲመሠረት ከነበሩት 36 አባል ሀገራት በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ 54ቱን የአፍሪካ ሀገራት አካትቶ አባል አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
የምክር ቤቱ ዓላማዎችና ግቦቹ ምንድን ናቸው?
ዊንኬት፡- ዋናው በአፍሪካውያን መካከል ንግድ እና ኢንዱስትሪን ለማስተሳሰር እና የተሻለ የንግድ ልውውጥ ለማድረግ የሚያመች ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ ከዛ ባሻገር እንደ ንግድ ድርጅት የም/ቤት አባላቶቹ አህጉሩን በሚመለከት ድምጻቸውን ማሰማት የሚችሉት በዚሁ አማካኝነት ስለሆነ የንግድ ሕብረተሰቡ ድምጽ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሌላው አፍሪካ ሰፊ እንደመኾኗ መጠን በውስጡ 54 ሀገራትም ስላሉ በእነዚህ ሀገራት ውስጥ ያሉ የንግድ ተቋማት እርስ በርሳቸው ለመገናኘትና መረጃ ለመለዋወጥ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፤ ዋነኛዎቹ ዓላማዎች ናቸው፡፡ ግቡ ደግሞ እነዚህን ዓላማዎች ማስፈጸም ነው፡፡
ምክር ቤቱ ከተቋቋመ 13 ዓመታት ሆኖታል፤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ካከናወናችኋቸው ተግባራት ጥቂቱን ቢገልጹልን?
ዊንኬት፡- ምክር ቤቱ የተቋቋመው እ.አ.አ በ2009 ቢሆንም ሥራ የጀመረው ግን በ2014 ነው፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ም/ቤቱ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ እንደ ድርጅት ፈቃድ ተሰጥቶት መቋቋሙ የመጀመሪያው ነገር ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ድርጅቱ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ስብሰባዎችን በማካሄድ፤ የንግድ ተሳታፊዎችን በማቀራረብና አልፎም የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ለጉብኝት እንዲሄዱ በማድረግ እና እርስ በእርስ እንዲግባቡ የማድረግ፤ በተለይም በዘርፉ የተለያዩ ጥናቶችን በማካሄድ አህጉራቱን የሚመለከት በዩክሬንና በራሽያ መካከል በተነሳው ጦርነት ሳቢያ አፍሪካ በምን መልኩ ልትጎዳ ትችላለች? የሚለውን በማጥናት እና ችግሮችን ለመፍታት የሚያስፈልጉ አማራጭ ፖሊሲዎችን አጥተናል፡፡ የተለያዩ መረጃዎችን በማውጣትም የአሀጉራቱን የንግድ እንቅስቃሴ በኢንተርኔትና በጽሑፍ ለማቅረብ ሞክረናል፡፡ የአፍሪካ ሀገራትን በአጭር ጽሑፍ የኢኮኖሚ ሁኔታቸውን በአጫጭር የሚገልፅ መጽሔት በየዓመቱ አሳትመናል፡፡ የዚህ ዓመትም ታትሞ ወጥቷል፡፡
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት በአባላቶቻችሁ ላይ ምን ያህል ሰርጿል?
ዊንኬት፡- ብዙ ሥራ የሚጠበቅብን ቢሆንም የተቻለንን ያህል ሄደናል፡፡ ድርጅቱ ገና ስምንትና ዘጠኝ ዓመቱ ቢሆነውም በአፍሪካ ደረጃ በደንብ ታውቋል፡፡ አፍሪካ ትልቅ አሀጉር ከመኾኑ አንፃር ለመንቀሳቀስ ቀላል አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ኮቪድ ከተጀመረ ጀምሮ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ኾኖም ግን ምክር ቤቱ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል ማለት ባይቻልም አሁን ላይ በድፍን አፍሪካ የታወቀና በተለየዩ መድረኮች እራሱን ያስተዋወቀ ተቋም ኾኗል፡፡ በተለያዩ ስብሰባዎችና መድረኮች እየተጋበዘ የንግድና ኢንደስትሪ ዘርፍ ተዋንያንን ያማሳተፍ እንቅስቃሴ በማድረገ ላይ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ደግሞ የተለያዩ ጽሑፎችን በየሀገራቱ ያሰራጫል፡፡ በርካታ አጋር ድርጅቶችንም ማምጣት ችሏል፡፡ ከእነዚህ መካከል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስርና በግል የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍና በአህጉር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋር አብሮ ይሠራል፡፡ ለምሳሌ የአፍሪካ አሀጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና እና ከፋይናሽያል ተቋማት እንዲሁም በአፍሪካ ሕብረት ውስጥ ከሚገኙ ትላልቅ የንግድ ተቋማትም ጋር አብሮ በመሥራት የንግድ ትስስሩ የበለጠ እንዲጠናከር በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
የግል/የንግዱ ዘርፍ በአጉሪቱ ሁለንተናዊ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በአንዳንድ አባል ሀገራት እዚህም እዚያም የሚታዩ የሰላም መደፍረሶች ደግሞ በንግዱና ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከባድ ፈተና ሆነዋል፡፡ በእርስዎ እይታ ይህን እንዴት ይመለከቱታል?
ዊንኬት፡- እነዚህ የጸጥታ ችግር በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ያሉ ቢኾንም አብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት ሰላም ናቸው፡፡ ጥቂቶች ግን በሀገራቸው ውስጥ ችግሮች ሊኖርባቸው ይችላሉ እንጂ በጎረቤት ደረጃ ጦርነት የለም፡፡ ከዚህ አንፃር በእነኚህም ሀገራት ውስጥ በንግድ መሳለጡ ሂደት ላይ እንቅፋት ሊፈጠር ይችላል፡፡ ነገር ግን ከአጠቃላይ ሃምሳ አራቱ ሀገራት አንፃር ችግሩ ያን ያህል የከፋ አይደለም፡፡ ያሉትም ችግሮች በአጭር ጊዜ ይፈታሉ ብለን እንገምታለን፡፡ በዚህ ችግር በአጠቃላይ እንደሀገር መጠነኛ የእድገት መጓተት ቢኖርም ያን ያህል የምክር ቤቱን እንቅስቃሴ ያደናቅፈዋል፤ ወይም የሀገራቱን የወደፊት አቅጣጫ ያስቀይራል ማለት ያስቸግራል፡፡ በአህጉር ደረጃ ብዙ ተስፋ አለ፡፡ ከሌሎች አህጉራት አንፃር አፍሪካ ሲታይ የኢኮኖሚ እድገቱ በማይተናነስ ሁኔታ እየጨመረና እያደገ ነው፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ በአንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት የሰላም መደፍረስ ይታያል፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ ተቋሙ ምን ሚና ይጫወታል?
ዊንኬት፡- ከምክር ቤቱ ዓላማ አንፃር ትኩረት አድርገን እንሠራለን፡፡ የተለያዩ ድርጅቶች ደግሞ የተለያዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚንቀሳቀሱ አሉ፡፡ በመሠረቱ የፓን አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት የኣባል ሀገራትን የንግድ እንቅስቃሴ ለማጠናከር ትስስሩንም በንግድ በኩል የበለጠ ለማሻሻል እና ለማሳደግ የሚጥር ድርጅት ነው፡፡ ሌሎች ድርጅቶችም በእነዚህ ችግሮች ላይ መሥራታቸው አይቀርም፡፡ ይህም ኾኖ ለምሳሌ ኢትዮጵያን በምንወስድበት ጊዜ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ይዘን እንንቀሳቀሳለን፡፡ ለምሳሌ ከመንግሥት እና ከንግዱ ኅብረተሰቡ ጋር የሚያስተሳስር “የፐብሊክ ፕራይቬት ዲያሎግ” የሚባል ፕሮግራም በያዝነው ዓመት እነሠራለን ብለን እንጠብቃለን፡፡ ስለዚህ በእኛ በኩል ያለው ሥራ አይቆምም፡፡
ምክር ቤቱ እ.ኤ.አ ከ2022-2025 የሚቆይ ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅቷል፡፡ እቅዶቹ ምን ምን ላይ እንዳተኮሩ ቢነግሩን?
ዊንኬት፡- አራት ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ነጻ የአፍሪካ የንግድ ቀጣና ስምምነቱ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ይህንንም የአፍሪካ የንግድ ተቋማትን በመረጃ የበለጠ ማጎልበትና ስምምነቱን በመጠቀም የንግድ ሂደቱን ማስፋፋት ላይ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ስምምነቱ ሥራ ላይ እንዲውል ማደረግ ሲሆን ይህም ምርቶች ሥራ ላይ መዋል እና የሚፈለገው አካል ጋ መድረስ ይኖርባቸዋል፡፡ በተጨማሪም የአንድ ሀገር የማምረት አቅም እንዲጨምር የተለያዩ ሥራዎችን እንሠራለን፡፡ በሦስተኛ ደረጃ በግሪን ኢንቨስትመንት ኅብረተሰቡ ከአካባቢው ጋር በተጣጣመ መልኩ የንግድ እንቅስቃሴ ማሳለጥ የሚያስችሉ ፖሊሲዎች ወጥተው በሥራ ላይ እንዲውሉ እንሠራለን፡፡ በአራተኛ ደረጃ ደግሞ የዓለም የምዕተ ዓመቱ ግብ የሚባለውን ለማሟላት በተቻለ መጠን የንግዱና ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሚና ከፍተኛ ነው ብለን ስለምናምን ትኩረት አድርገን እንንቀሳቀሳለን፡፡ በዚሁ የምዕተ ዓመቱ ግብ ሴቶችን፣ ወጣቶችን፣ አቅመ ደካሞችን እንዲሁም ከልማት ጋር የተያያዙ ሥራዎች ላይ የንግድ እና ኢንዱስትሪው ተዋንያን የራሳቸውን ልምድና አቅም እንዲጠቀሙ የሚያስችሉበትን ሁኔታዎችን የማመቻቸት ተግባራትን መፍጠርን ያካትታል፡፡
በየሀገሩ የሚገኙ ሕጋዊ ያልኾኑ ነጋዴዎችን ወደ ሕጋዊነት በማምጣት ለሀገራት ኢኮኖሚ እድገት እንዲያመጡ ለወደፊቱ ም/ቤቱ ሊሠራው ያሰበው እቅድ አለ?
ዊንኬት፡- እንደተባለው በአባል ሀገራት በርካታ ሕጋዊ ያልኾኑ ነጋዴዎች እንዳሉ ይታመናል፡፡ እነዚህን እንደ ትልቅ ችግር እናያቸዋለን፡፡ ችግሮቹን በቅደም ተከተል ስንመለከታቸው ዋናው እኛ ትኩረት የሰጠነው በአባል ሀገራት የተደረጉትን ስምምነቶች በተግባር ማዋል ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ እንደሙስና እና የሰላም ሁኔታ መሻሻል ላይ የንግድና ኢንዱስትሪው ማኅበረሰብ የራስን አስተዋጵኦ እንዲወጣ እንሠራለን፤ ከዚህ ውጪ የተለየ ነገር ሰጥተን የምንሄድበት ሁኔታ የለም፡፡ ለወደፊት ግን ይህን ጉዳይ ትኩረት ሰጥተን እንሄድበታለን፡፡
ምክርቤቱ ዓላማውን ለማሳካት ካጋጠሙት ጉልህ ተግዳሮቶች መካከል ዋና ዋናዎቹን ቢነግሩን? ያጋጠሟችሁን ችግሮችስ እንዴት ተቋቁማችሁ አለፋችሁ?
ዊንኬት፡- በአብዛኛው የአሀጉሩ ስፋት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው የመንቀሳቀስ ሁኔታውን የበለጠ አክብዶታል፡፡ በተለይ ግን ከኮቪድ በኋላ የመጣው በዙም የመገናኘት አሠራር ምቹ ሁኔታን ስለፈጠረልን በጣም ጠቅሞናል ማለት ይቻላል፡፡ ሌላው ከአቅም ጋር ተያይዞ የሚገጥመን ተግዳሮት ነው፡፡ አቅም የሚገኘው ከአባለቱ ነው፡፡ አባላቱ ደግሞ በአብዛኛው ለድርጅቱ የሚሰጡት የመዋጮ መጠን በጣም ውስን ነው፡፡ ይህን ለማስተካከል አሁን ላይ የተለያዩ አቅጣጫዎችን እየመረጥን ነው፡፡ የአገልግሎት አድማሳችንን ለማስፋት፣ የአጋር ድርጅቶችን ቁጥር ለመጨመርና አብሮ ለመሥራት፤ ሁኔታዎችን እያመቻቸን እንገኛለን፡፡ በየቦታው ቀርቦ ከግል ድርጅቶች ጋር ለመሥራት እየጣርን ነው፡፡ በዚህም የምክር ቤቱን አቅም ለማጠናከርና ገቢዎችን ለማምጣት በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡ በዚህ ዙሪያ ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል፡፡
ከአጋር ድርጅቶችና ከአባል ሀገራትስ ምን ይጠበቃል?
ዊንኬት፡- በመጀመሪያ የንግድና ኢንዱስትሪው ኅብረተሰብ ዋና ችግሩ ምንድነው የሚለውን ለመለየት ወይም ለማወቅ እየሞከርን ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ድርጅቱ ራሱ ለንግድ ኅብረተሰቡ ጠቃሚ ነው አይደለም የሚለውን በሥራው ለማሳወቅ እየሠራን ነው፡፡ እነዚህ ሥራዎች ላይ ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ የንግድና ኢንዱስትሪው ኅብረተሰብ በተለይ እቃዎችን ከአንዱ ሀገር ወደሌላው ሀገር የመላክ ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩ ድርጅቶች ምክር ቤቱን የበለጠ ያውቃሉ፡፡ ግን በስፋት አባል እሆኑም፡፡ እነዚህም አካላት ሥራቸውን ለማቀላጠፍ አባል ቢሆኑ የተሸለ ተጠቃሚ ይሆናሉ የሚል እምነት አለን፡፡
ከእነዚህ አካላት ጋር ለመሥራት ምን ዓይነት ስትራቴጂ ለመከተል አስባችኋል?
ዊንኬት፡- የስትራቴጂ ሁኔታው በመጀመሪያ ከመቅረብ ነው የሚነሳው፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ልንሠራ የምንችላቸውን ተግባራት ከማሳወቅ እና ከማሳየት ነው የሚጀምረው፡፡ የምክር ቤቱ አንዱ ትልቁ አቅም 54ቱም የአፍሪካ ሀገር ወኪል እንዳለው ማሳወቅ ነው፡፡ አንድ መልዕክት እንኳን ለ54ቱ ሀገሮች ማስተላለፍ ቢፈልግ ከምክር ቤቱ የተሻለ የግል ድርጅት የለም፡፡ ስለዚህ በዚህ መልኩ ሲታይ ይህ ድርጅት ለንግድና ኢንዱስትሪው ኅብረተሰብ ትልቅ ነገር ሊያቀርብ ይችላል ብለን እናስባለን፡፡ ማስታወቂያም እንኳን ቢፈለግ ለ54ቱም ሀገራት በአንድ ሳምንት ውስጥ መረጃዎችን ሊበተን የሚችል ድርጅት ስለሆነ በየአባል ሀገራቱ ባሉት የምክር ቤት አባል ድርጅቶች አማካኝነት በርካታ ነገሮችን መከወን ይቻላል ብለን እንገምታለን፡፡ የድርጅቱንም የወደፊት እድል የበለጠ ያሻሽለዋል ብለን እናምናለን፡፡
በመጨረሻም የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ ቢነግሩን?
ዊንኬት፡- ማስተላለፍ የምፈልገው ድርጅቱን ለማወቅና ከድርጅቱ የሚገኙ አገልግሎቶችን ለመጠቀም የሚፈልግ ሁሉ info@pacci.org | +251 11 691 0011 | www.pacci.org | Gulf Aziz Building (402), Addis Ababa, Ethiopia ላይ በቂ መረጃ አግኝቶ አብሮኝ መሥራት ይችላል የሚለውን ነው፡፡
