ግዮን መጽሔት :- የምዝገባ ሂደቱ ተጠናቆ ዕጩዎችና የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ፖሊሲዎቻቸውንና የነገ ተስፋዎቻቸውን ለሕዝብ የሚያቀርቡበት የቅስቀሳ ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡
ይህ ወቅት የሐሳቦች ገበያ የሚከፈትበት፣ የተለያየ ቀለምና ይዘት ያላቸው ፖለቲካዊ አጀንዳዎች የሚስተናገዱበት የዴሞክራሲ ማሳያ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ የአገራችን ትልቁ ኃይል የሆናችሁ ወጣቶች ሚና ከምንም በላይ ጎልቶ ይታያል፡፡
ወጣትነት ጉልበት፣ ስሜትና ተነሳሽነት ነው፡፡ ይህ ጉልበት ደግሞ ከዕውቀትና ከሰላማዊ ጨዋነት ጋር ሲቀናጅ አገርን የሚገነባ ታላቅ መሣሪያ ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ፣ የፖለቲካ ፉክክር በሚፋፋምበት በዚህ ወቅት፣ ስሜትን በመግታት ለሰላምና ለዴሞክራሲያዊ እሴቶች ቅድሚያ መስጠት ከእያንዳንዱ ወጣት የሚጠበቅ የዜግነት ግዴታ ነው፡፡
1. ልዩነት የጥል ሳይሆን የዕድገት መነሻ ነው
በምርጫ ወቅት የተለያዩ ሐሳቦች መቅረባቸው ግድ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ማለት ደግሞ ሁሉም ሰው እንደ አንድ ዓይነት እንዲያስብ ማስገደድ ሳይሆን፣ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ መቻል ነው።
አንድ ዕጩ የሚያቀርበው ሐሳብ ከእርስዎ እምነት፣ ፍላጎት ወይንም አመለካከት ጋር ፍጹም ሊቃረን ይችላል፡፡ ይህ ግን የጠብ መነሻ መሆን የለበትም፡፡
- ሐሳብን በሐሳብ መመከት፦ የማይስማሙበትን ሐሳብ በጩኸት፣ በስድብ ወይንም በኃይል ለማደናቀፍ መሞከር የሽንፈት እንጂ የጥንካሬ ምልክት አይደለም፡፡ የሰለጠነ ወጣት የማይስማማበትን ሐሳብ በምክንያትና የተሻለ አማራጭ በማቅረብ ይሞግታል፡፡
- የመስማት ባሕልን ማዳበር፦ ተቃራኒ ሐሳብን በትዕግሥት ማዳመጥ ያንን ሐሳብ መቀበል ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም የሌላውን ወገን ስጋትና ፍላጎት ለመረዳትና የራስን አቋም በንፅፅር ለመመዘን የሚረዳ ብልህነት ነው፡፡
2. ስሜትን ለሥነ–ምግባር ማስገዛት
በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት መድረኮች ሊሞቁ፣ ንግግሮች ሊፋለሙ ይችላሉ፡፡ በዚህ መሃል ወጣቶች ስሜታቸውን ተቆጣጥረው ለሰላማዊ ድባብ ዘብ ሊቆሙ ይገባል፡፡
- ከትንኮሳዎች መራቅ፦ አንዳንድ ጊዜ ሆን ተብለው የሚሰነዘሩ ትንኮሳዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ወቅት በሰከነ መንፈስ ማለፍና ለሕግ የበላይነት ቅድሚያ መስጠት ከወጣቱ የሚጠበቅ ታላቅነት ነው።
- የቃላት አጠቃቀም ጥንቃቄ፦ በንግግርም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያ በሚደረጉ ክርክሮች የሰውን ክብር የሚነኩ፣ ጥላቻን የሚዘሩ ወይንም ብሔርና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ስድቦችን ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲ የሚገነባው በመከባበር ላይ ነው፡፡
ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀው በወጣቶች እና ባህል ልማት ፋውንዴሽን (Youth and Cultural Development Foundation – YCDF) ከ UNDP ጋር በመተባበር ነው።
የወጣቶች እና ባህል ልማት ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ውስጥ የወጣቶችን ሁለንተናዊ አቅም በመገንባት፣ ባህላዊ እሴቶችን በማሳደግ፣ የሰላም
ግንባታ ሥራዎችን በማስፋፋት እና የወጣቶችን ንቁ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ በማጎልበት ላይ በትኩረት የሚሠራ ገለልተኛ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ነው።
ድርጅቱ ወጣቶች በሀገር ግንባታ ሒደት ውስጥ ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ግንዛቤ በመፍጠርና አቅማቸውን በማጎልበት የላቀ አስተዋጽዖ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 233 ግንቦት 2018 ዓ.ም
