ባሳለፍነው ሳምንት በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ መካከል የተኩስ ልውውጦች ሲካሔዱ እንደሰነበቱ እና ብዙዎችም ሙት እና ቁስለኛ መኾናቸው ተሰምቷል፡፡ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ደንቢያ ወረዳ ጯሂት ከተማ ሠመረቻ በተባለ አካባቢ በመከላከያ ሠራዊት አባላት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ሐምሌ 19/2015 ከአምስት ሰአት ጀምሮ የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድ እንደነበር የምዕራብ ደንቢያ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ገልጿል።
የገበታ ለአገር ፕሮጀክት አንዱ በሆነው የጎርጎራ ፕሮጀክትን ለመጎብኘት የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ረቡዕ ሐምሌ 19/2015 ወደ አካባቢው መጓዛቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህም ለአመራሮቹ በሬ መታደረዱን ተከትሎ “በዕሮብ ቀን ለምን በሬ ይታረዳል፤ ኃይማኖታችንስ ለምን ይረክሳል?” በሚል በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታ መፈጠሩ ተጠቁሟል። በዚህ የተነሳም በአካባቢው በሚገኙ የፋኖ ታጣቂዎችና በመከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል በተፈጠረ የተኩስ ልውውጥ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ሕይወት አልፏል ነው የተባለው።
የተኩስ ልውውጡ እየተካሄደ ያለው ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጀምሮ መሆኑን የገለጸው የወረዳው የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት፤ ከጎርጎራ በቅርብ እርቀት በሚገኘውና ሠመረቻ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ እስከ ጯሂት ከተማ ደረስ የተኩስ ልውውጡ ተሰፋፍቶ እንደነበር ጠቁሟል። ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የጽህፈት ቤቱ ሠራተኛ “ረፋድ አራት ሰዓት አካካባቢ በጯሂት ከተማ አድርጎ ወደ ጎርጎራ የባለሥልጣን መኪኖች ሄደዋል። የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት መኖራቸውንም ሰምተናል” ሲሉ ተናግረዋል። እስከ ረቡዕ ማታ 12 ሰዓት ድረስ በአካባቢው የተኩስ ልውውጡ መካሄዱን በመጠቆምም፤ በተኩሱ የተገደሉ ሰዎች አስክሬን ወደ ጯሂት ከተማ እየገባ መሆኑን ገልጿል፡፡
በተኩሱ ልውውጡ ከመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ ከፋኖ ታጣቂዎች እና የነዋሪዎች ህይወት መጥፋቱን የጠቆመው ጽህፈት ቤቱ፤ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውንም አክሏል። በተጨማሪም የመከላከያ ሠራዊት አባላት “ቤታችን ድረስ ገብተው ደብድበውናል” በሚል የአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሟቸውን እያሰሙ እንደነበርም ተመላክቷል።
በተመሳሳይ በደቡብ ወሎ ዞን መካነሰላም ከተማ እሁድ ሐምሌ 16/2015 የከተማው ወጣት ከመከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር በተፈጠረ ግጭት ኹለት ሰዎች መገደላቸውን፤ የመካነ ሰላም ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡ የመካነ ሰላም ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት የሚዲያና ሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አረጋ አህመድ፤ “እሁድ ሐምሌ 16/2015 ከቀኑ አምስት ሰዓት ላይ በከተማው የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የቤተክርስቲያን የጥበቃ ሠራተኛ የነበረን አንድ ሰው “የፋኖ አባል ነው” በማለት በቁጥጥር ሥር ለማዋል ሙከራ ማድረጋቸውን ተከትሎ፤ በከተማው ከሚገኙ ወጣቶች ጋር ግጭት ተፈጥሮ ነበር፡፡” ብለዋል፡፡
አክለውም፤ መከላከያ ሠራዊት አባላት “የፋኖ አባል ነው” ብለው የጠረጠሩትን ግለሰብ በከተማው አቅራቢያ ወደሚገኝ የመከላከያ ካምፕ በሚወሰዱበት ወቅት፤ የከተማዋ ወጣቶች ከመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ ደንጋይ መወርወራቸውን ገልጸው፣ የቆሰሉ የሠራዊቱ አባላት መኖራቸውንም ተናግረዋል።
ከአንድ ሳምንት በፊት ደግሞ በዚያው በደቡብ ወሎ ዞን በወገዲ ወረዳ በመከላከያ ሠራዊት አባላትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ተኩስ ተከፈቶ እንደነበር ገልጸው፤ በዚያም አንዳንድ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ተዘግተው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ አግሪት ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ሰኞ ሐምሌ 17/2015 ምሽት አንድ ሰዓት አካባቢ በመከላከያ ሠራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ወጊያ ሲካሄድ ማደሩንና ስድስት የሚሊሻ አባላት መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ከተደረገው ውጊያ በኋላ በወረዳው እና አካባቢው በርካታ የመከላከያ ሠራዊት አባላት መግባታቸው ተጠቁሟል።
በተመሳሳይ በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ ዕሁድ ሐምሌ 16/2015 ከምሽት ኹለት ሰዓት ገደማ የፖሊስና ሚሊሻ አባላት ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ የጸጥታ አካላት እና ንጹሃን መገደላቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ በከተማው ፒያሳ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የምሽት ተረኛ በነበሩ የፖሊስና ሚሊሻ አባላት ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ መንገድ ዳር በቆሎ ስትጠብስ የነበረች የኹለት ልጆች እናት እና ኹለት ወጣቶች መገደላቸው ተጠቅሷል። ለሰዓታት በቆየው የተኩስ ልውውጥ ከሟቾች ባለፈ የጸጥታ አካላት ላይም የአካል ጉዳት መድረሱን ለማወቅ ተችሏል ስትል የዘገበችው አዲስ ማለዳ ናት።
የዐማራ ክልል የሰላም እና ጸጥታ አመራሮች ከኃላፊነታቸው ተነሱ
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ የጸጥታ ጉዳዮች አማካሪያቸውን እና የክልሉን ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊን ከስልጣናቸው አነሱ። ዶ/ር ይልቃል የጸጥታ ጉዳዮች አማካሪያቸውን ከኃላፊነት ያነሱት የተሰጣቸውን “ተግባር እና ኃላፊነት በአግባቡ አልተወጡም” በሚል ነው። ዶ/ር ይልቃል ሁለቱን ኃላፊዎች ከስልጣናቸው ያነሱት ከትላንት ሐምሌ 17 ቀን 2015 ዓ.ም በጻፉት ደብዳቤ ነው። በአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ በምክትል ኃላፊነት ደረጃ የርዕሰ መስተዳድሩ የጸጥታ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ከፋለ እሱባለው እና የቢሮው ምክትል ኃላፊ ኮማንደር መንገሻ አውራሪስ፤ ውሳኔውን የሚገልጽ ደብዳቤ እንደደረሳቸው አረጋግጠዋል።
ከአማካሪነታቸው የተነሱት አቶ ከፋለ፤ በዚህ የኃላፊነት ቦታ ለአምስት ዓመት ገደማ ቆይተዋል። አቶ ከፋለ ይህንን ኃላፊነት ያገኙት በቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአመራርነት ጊዜ ሲሆን፤ የአሁኑን ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃልን ጨምሮ ባለፉት ዓመታት ክልሉን የመሩትን አምስት ርዕሰ መስተዳድሮች በአማካሪነት አገልግለዋል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሶሲዮሎጂ እንዲሁም በሰላም እና ደህንነት ጥናት የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው የቀድሞው አማካሪ፤ አሁን በስራ ላይ ያለውን የአማራ ክልልን የጸጥታ ተቋም “ካደራጁ ሰዎች መካከል አንዱ” መሆናቸው ይነገርላቸዋል። በርዕሰ መስተዳድሩ ዶ/ር ይልቃል ፊርማ የወጣ እና ለአማካሪው የደረሰው የስንብት ደብዳቤ፤ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር የጸጥታ ጉዳዮች አማካሪነት “የተሰጠዎትን ተግባር እና ኃላፊነት በአግባቡ ያልተወጡ በመሆኑ ከኃላፊነት የተነሱ መሆኑን አሳውቃለሁ” ሲል የውሳኔውን ምክንያት ይጠቅሳል።
ይህ ውሳኔ ከመተላለፉ አንድ ቀን አስቀድሞ በተካሄደ “የድርጅት ግምገማ” ጥሩ አፈጻጸም ማሳየታቸው ተገልጾ እንደነበር የተናገሩት አቶ ከፋለ፤ ውሳኔው “ያልተጠበቀ” እንደሆነባቸው ገልጸዋል። የቀድሞው የጸጥታ ጉዳዮች አማካሪ ከኃላፊነት የተነሱት በአሁኑ ጊዜ ካለው የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ይሆን እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “አዎ፤ ጊዜው ባይሆንም ቀስ ብዬ የምገልጻቸው ነገሮች ይኖራሉ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። በአማራ ክልል በቅርቡ የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች፤ በክልሉ “የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ” ላይ “ተጽዕኖ” ማሳደራቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የአማራ ክልል ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተናግረው ነበር። ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከኃላፊነት ያነሷቸው የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮማንደር መንገሻም በተመሳሳይ ውሳኔው ድንገተኛ እንደሆነባቸው ገልጸዋል። ከኃላፊነት የተነሱበት ውሳኔ በተላለፈበት ቀን “በስምሪት ላይ” እንደነበሩ የጠቀሱት ኮማንደር መንገሻ፤ “የተነገረኝ ምክንያት የለም” ሲሉ ከምክትል ቢሮ ኃላፊነት የተነሱበትን ምክንያት እንደማያውቁ ተናግረዋል።
ኮማንደር መንገሻ የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሆነው የተሾሙት በቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ አማካኝነት ነበር። ተሰናባቹ ምክትል የቢሮ ኃላፊ በዚህ ቦታ ከመሾማቸው አስቀድሞ፤ በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር እና የሰው ልማት ዳይሬክተር በመሆን ሰርተዋል። በሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ለሶስት ዓመት ከአራት ወር ገደማ የሰሩት ኮማንደር መንገሻ፤ በአማራ ክልል የጸጥታ መዋቅር ውስጥ በአጠቃላይ ለ20 ዓመታት ገደማ አገልግለዋል ሲል የዘገበው ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ነው፡፡
