“በኢትዮጵያ ምድር ላይ ሠርተው አሳይተዋል”
እንግዳችን ልጅ ኤልያስ ግዮን መጽሔት ላይ በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹የአማርኛ ሳይንስ ኮሌጅ›› በመክፈት አጋዥ ለመኾን እንቅስቃሴ መጀመራቸውንም ገልጸው ነበር፡፡ ለመኾኑ ይኽንን ፕሮጀክታቸውን በምን መልክ ወደ መሬት ለማውረድ ዐቅደዋል? አጠቃላይ ሒደቱስ ምንን ይጠይቃል? ዐማርኛ ቋንቋ የተመረጠበት አግባብስ እንዴት ነው የሚሉትንና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ የመጨረሻውን ክፍል ከጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ!
ግዮን፡- ‹‹አኮሳ›› ማለት ምን ማለት ነው?
ልጅ ኤልያስ፡- ‹‹አኮሳ›› ማለት ‹‹አምሀሪክ ኮሌጅ ኦፍ ሳይንስ›› (Amharic College of science) ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም ‹‹አኮሳ›› የሚለው ቃል ‹‹አኮስትሪክ›› ከሚል የአማርኛ ቃል የተወሰደም ነው፡፡ ‹‹አኮስቲክ›› ማለት ደግሞ ‹‹ወይም›› ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ቃላትን ወስዶ መጠቀም አግባብነት ያለው አሠራር ነው፡፡ ምክንያቱም የቃላት ውርርስን እያሰፋ ስለሚመጣ ነው፡፡ ሳይንስ በአማርኛ ስንጽፍ ሰዋሰው የሚባል ነገር የለውም፡፡ አንድ ቋንቋ የሳይንስ ቋንቋ ሲኾን የቴክኒክ ቋንቋ ይኾናል፡፡
ሳይንሳዊ የኾኑ ቃላትን ወደ አማርኛ ማምጣት ማለት ቀደም ሲል እንደገለጽኩት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በ1989 ዓ.ም እንዳዘጋጀው ዓይነት ማለት ነው፡፡ ቃላትን ከቀዳሚ ስማቸው ወደ ትርጓሜ ማምጣት ከባድ ሥራ ነው፡፡ በየዘርፉ የተማሩ ሊሂቃንና መተርጉማንም ያስፈልጉታል፡፡
ለምሳሌ ‹‹አይረን›› የሚለውን ቃል በአማርኛ ‹‹ብረት›› ብለን ስንጠራው ቃል በቃል ተተርጉሞ አይደለም የሚመጣው፡፡ እኛ በ1989 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ መተርጉማን የተከተሉትን መንገድ ተከትለን ነው የምንሠራው፡፡ በዌብ ሳይታችንና ፌስቡካችን ላይ ፎርም አስቀምጠን ለብዙ ሰው ነግረናል፡፡ ሙያ ላይ ያሉ ሰዎች ቃላት እንዲያዋጡ ጠይቀናል፡፡ ኮሚቴ አዋቅረን በጣም ብዙ የተማሩ ኃይሎችን ሰብስበን ለመረዳት ይቀርባሉ ብለን ያፀደቅነውን ተግባር ላይ እናውላለን፡፡ ከ1989 ዓ.ም በኋላም የተሠራ ትልቅ መዝገበ ቃላት አግኝተናል፡፡ ገና ያልታተመ ነው፡፡
እሱንም አካተን ነው የምንሠራው፡፡ የተለያየ ሙያ ያላቸው ሰዎች በመምህርነትና በፕሮፌሰርነት በየዩኒቨሲርቲው የሚሠሩ ሰዎች የዕለት ተዕለት ቋንቋቸው ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ኬሚካል ውስጥ የሚሠራ ሰው ሥራ ካቆመ በኋላ መጽሐፉን አይከፍትም፡፡ መምህር ግን ሁልጊዜ ሲያስተምር የተሻለ ነገር ይዞ ለመገኘት በሚያደርገው ጥረት በአእምሮው ብዙ የቃላት ክምችት አለ፡፡ ስለዚህ በዚህ ዙሪያ ሰዎች እንዲሳተፉ ለማድረግ ፎርም አዘጋጅተናል፡፡ ከአንድ ሺህ ቃላት በላይ ላበረከቱ ሽልማትና ሰርተፊኬት እንሰጣለን፡፡
ግዮን፡- በ1989 ዓ.ም ሳይንስ አካዳሚ ያዘጋጀው የመድብለ ቃላት ክምችት ጥቅም ላይ ሳይውል እስካሁን መቆየቱን ሲያዩ ምን ተሰማዎት?
ልጅ ኤልያስ፡- አንድ ትምህርት ባለቤት ይፈልጋል፡፡ ብዙ ሰዎች የደከሙበት ነገር ቀጣይነት ከሌለው የኾነ ቦታ ላይ ቆሞ ይቀራል፡፡ እኛም እንደዚያ እንዳይኾንብን ነው የምንሠራው፡፡ እኔ ኃላፊነት ወስጄ ይሄን ሥራ ስሠራ የኾነ ቦታ ላይ እንዳይቋረጥ የተለያዩ አካላት በባለቤትነት እንዲሳተፉበት እያደረግን እንገኛለን፡፡ ያ ጥናት ብዙ ገንዘብ የወጣበት ነው፡፡ 13 ሙያዎች ናቸው የተካተቱበት፡፡ ከ13 ሙያዎች ውስጥ 15 ሺህ ቃላት ብቻ ነው የተሰበሰበው፡፡ ስለዚህ ይሄ ሥራ ገና ብዙ ይፈልጋል፡፡ ጥናቱ ሳይሠራበት ለረጅም ዓመታት የተቀመጠ ነው፡፡ የእኛ ትልቁ ሥራ ግን ይህን ነገር መሬት ላይ አውርደን መሥራት ነው፡፡
ግዮን፡- እንደ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ጃፓንና የመሳሰሉት ሀገራት በራስ ቋንቋ ከመማር ጋር በተያያዘ ተደጋግመው የሚነሱ ሀገራት ናቸው፡፡ በዚያ ዙሪያ ምን ይሉናል?
ልጅ ኤልያስ፡- የኢንዱስትሪው አብዮት የተጀመረው ከዛሬ 300 ዓመታት በፊት ነው፡፡ እንግሊዞች በወቅቱ በነበራቸው ዓለም ዓቀፋዊ የበላይነት የዓለምን የሀብት ምንጭ ለመጠቀም ትልልቅ ሀገራትን ጭምር ቅኝ ግዛት አድርገዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ሳይመጣ በፊት ግን ብዙ ነገር ተቋማዊ ቅርፅ አልነበረውም፡፡ ትልልቅ ነገሮች መሥራት የጀመሩት እንደመኪና፣ አውሮፕላንና መሰል በርካታ ትልልቅ ማሽኖች የሳይንሱ እውቀት ስለነበራቸው ነው፡፡ ያ ዕውቀት በቀላሉ የሚገኝ ነገር አይደለም፤ በጽሑፍ የተቀመጠ ስለኾነ ነው፡፡
እንደ አልሙኒየምና ብረት ያሉ ንጥረ ነገሮች በምድር ላይ ብቻቸውን አይገኙም፡፡ ከተለያዩ ሌሎች ንጥረ ነገሮች ጋር ተጣምረው ነው የሚገኙት፡፡ ይህን ጥምረት ለማላቀቅ እውቀት ያስፈልጋል፡፡ ይህን ሂደት ለትውልዱ ለማስተማር ደግሞ የመጀመሪያው በተግባር በሥራው ላይ ተሠማርቶ ማሳየት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ስለሂደቱ በገለጻ የታጀበ ሰፊ መረጃ መስጠት ነው፡፡ አንድ ግዜ በራሳችን ቋንቋ የተማርነው ነገር መቼም አይጠፋም፡፡
ዘላቂ እውቀት ይዘን እስከመጨረሻው እንቀጥላለን፡፡ በባዕድ ቋንቋዎች በተለይም በእንግሊዘኛ የምንሸምተው እውቀት ግን ሽምደዳ ነው፡፡ የሚጠናውም ፈተና ለማለፍ ነው ፤ ፈተናው ሲያልፍ እውቀቱም ይጠፋል፡፡ ለዚህም ነው ምንም ነገር መሥራት ያልተቻለው፡፡ ሩሲያዎች ስለእንግሊዝኛ የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ በራሳቸው ቋንቋ ነው ማንዋል የሚያዘጋጁት፡፡ እስፔስ ሳይንስ ላይ ጎበዞች ናቸው፡፡ አሜሪካኖች በአንጻሩ ስለራሺያ የስፔስ ሳይንስ ለማወቅ የሩሲያ ቋንቋ ያጠናሉ፡፡ ሳይንስ የሚመክረው ድግግሞሽን ነው እንጅ አንድን ነገር በሽምደዳ ብቻ ይዞ ደግመው መሥራት የማይችሉት ላይ መቆምን አይደለም፡፡ እኛም በኮሌጅ ደረጃ ማስተማር የፈለግነው ሳይንስ ይሄንን ነው፡፡
ግዮን፡- ከእናንተ ጋር የሚሠሩት ሰዎች እነማን ናቸው? እንዴትስ ተመረጡ?
ልጅ ኤልያስ፡- በመጀመሪያ እኔ ስለሥራው ሳስተዋውቅ በጣም በርካታ ሰዎች የትምህርት ማስረጃዎችን ልከውልኛል፡፡ ኢንጅነር አምቦሎ እንዳለው በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ እንዲሠራልን የተመደበ ነው፡፡ የጎንደር ዩኒቨርስቲ ኢንጂነር ነው፡፡ በነገሩ ላይ ጥልቅ የኾነ መረዳት አለው፡፡ እኔ መጀመሪያ ቃለመጠይቅ ካደረግኩት በኋላ በሳምንት አንድ ቀን ውይይት እናደርግ ነበር፡፡ ሁለተኛዋ ሰው ሙሉዓለም ታምሬ የምትባል እህታችን ነች፡፡ የራሷ መንግሥታዊ ያልኾነ የእርዳታ ድርጅት አላት፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብዙ ዓመት ሠርታለች፡፡
የላከችልን ሲቪም ከሚገባው በላይ ብቁ መኾኗን የሚያሳይ ነው፡፡ እሷ በአፍሪካ ላይ የሾምናት ዳይሬክተር ነች፡፡ ምክንያቱም ከኢትዮጵያ ውጪ በሌሎች የአፍሪካ ከተሞችም አሠራራችንን እናስተምራለን ፤ እናስተዋውቃለን፡፡ ዕቅዳችንም ብዙ ኢንዱስትሪዎች ሊቋቋሙ የሚችሉበት የሳይንስና ምህንድስና ትምህርት እናስተምራለን የሚል ነው፡፡ ይኼ ደግሞ፣ ወደፊት በአፍሪካ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ሊያመጣ የሚችል ነገር ነው፡፡
ግዮን፡- የድርጅታችሁ አርማ የሚገልጸው ምንን ነው?
ልጅ ኤልያስ፡- በድርጅታችን አርማ ላይ ግልጽ ነገሮች ናቸው የተቀመጡት፡፡ አክሱም፣ ላሊበላና የፋሲል ግንብ አሉበት፡፡ እነዚህ ነገሮች የሚያሳዩት የኢትዮጵያን የሥልጣኔ ዘመናት ነው፡፡ የሥልጣኔ ዘመናችንን ለማስቀጠል የምንሠራው ነገር መኾኑን ለመጠቆም ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ከ700 ዓመት በፊት የተሠሩ ነገሮች ናቸው፡፡ በዚያን ጊዜ ማሽነሪ የለም፡፡ አክሱምም ኾነ ላሊበላ ወይም ፋሲለደስ ግንብ የተሠራው በሰው ኃይል እንጅ በማሽን እገዛና የቴክኖሎጂ ድጋፍ አይደለም፡፡
ጣሊያኖች የአክሱም ሐውልትን ሀገራቸው ድረስ የወሰዱት ድንጋይ ስለሚጠቀማቸው አይደለም፡፡ አባቶቻችን ምን ዓይነት ነገር ተጠቅመው እንደሠሩት ለማየት ነው፡፡ የአርክቴክትና የሥነ ሕንጻ ጥበባችን ለመረዳት ነው ያንን ያደረጉት፤ የእኛ አባቶች ጥበበኞች ስለኾኑ በዘመኑ ዓለም ያልቻለውን ነገር በኢትዮጵያ ምድር ላይ ሠርተው አሳይተዋል፡፡ ይህ ትውልድም የአባቶቹን ፈለግ ማስቀጠል የሚችለው አንድም በእኛ በኩል የቀረበለትን የእውቀት ማዕድ ጥሪ ተቀብሎ መቋደስ ሲችል ነው፡፡ አርማችን የሚያሳየውም የምንኮራባቸውን በዕውቀት የተሠሩ ዘላቂ የአባቶቻችንን ቅርሶች ነው፡፡
ግዮን፡- ወደ አሜሪካ ከሄዱ ምን ያህል ጊዜ ኾኖት? ከወጡ በኋላ ወደ ሀገርዎ ተመልሰውስ ያውቃሉ? በአሜሪካን ሀገር ቤተሰብስ መሥርተዋል?
ልጅ ኤልያስ፡- ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካን ሀገር ከሄድኩ 17 ዓመታት ኾኖኛል፡፡ የሁለት ሴት ልጆች አባት ነኝ፡፡ ልጆቼ የ9 እና የ16 ዓመት ናቸው፡፡ አሜሪካ ከመጣሁ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ መጥቻለሁ፡፡ በእነዚህ ሁለት ጊዜያት የቆየሁት ለአጭር ጊዜ ነው፡፡ አንዴ ሦስት ሳምንት ሌላ ግዜ ደግሞ አራት ሳምንት ነው የቆየሁት፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ሀገሬ ደርሼ ከመጣሁ አምስት ዓመት ኾኖኛል፡፡ የአሜሪካ መሥሪያ ቤቶች ለሠራተኞቻቸው ብዙ የእረፍት ፈቃድ ቀኖችን አይሰጡም፡፡ ቢበዛ ሁለትና ሦስት ሳምንት ቢፈቅዱ ነው፡፡
የግል ሥራ ከኾነ ግን ከ3-6 ወር ድረስ ሥራውን አቁሞ ሀገር ቤት መቆየት ይቻላል፡፡ ነገር ግን አንድ ሥራ ለረጅም ጊዜ ከተዘጋ ይህ ሰው የሥራ ፍላጎት የለውም? ምን እያደረገ ነው? የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ የቅጥር ሠራተኛ ከኾነ ግን በዓመት ውስጥ ከ 3 ሳምንት የዘለለ ፈቃድ አይኖረውም፡፡ ለ15 ቀን ኢትዮጵያ መሔድ ደግሞ በጣም ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም 17 ሰዓት በረራ ነው፡፡ ሁለቱ ቀን ድካም ነው፡፡ ቀሪው ቀን ደግሞ ጥቂት በመኾኑ ምንም ሳያደርጉ መመለስ ግዴታ ይኾናል፡፡ እኔ ከዚህ በኋላ አዲስ አበባ ከመጣሁ ቢሮ ነው የምከፍተው፡፡ ብዙ ጊዜዬን እያጠፋሁበት ያለ ሥራ በመኾኑ ከዚህ በኋላ ወደ ሌላ ሥራ አልመለስም፡፡
ግዮን፡- አሳክተው ማየት የሚፈልጉት ሕልምዎ ምንድን ነው?
ልጅ ኤልያስ፡- ሰዎች የአንድ ሰው ተነሳሽነት ብዙ ለውጥ የሚያመጣ አይመስላቸውም፡፡ ዋናው ግን ለለውጥ የሚኾን ተነሳሽነት የኾነ ቦታ ላይ መፈጠሩ ነው፡፡ እኔን በየጊዜው የሚያንገበግበኝ የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መምጣት ነው፡፡ በተጨማሪም በየዓመቱ በርካታ ተማሪዎች ከዩኒቨስርቲው ተመርቀው ሥራ አለማግኘታቸው በጣም ያሳዝናል፡፡
እኔ እራሴ እዚህ ነገር ውስጥ መግባት የፈለግሁበት ትልቁ ነገር ሳይንስን አውቀው ሥራ ፈጣሪ መኾን የሚችሉ የሀገሬን ልጆች ለማብቃት ነው፡፡ ሳይንስን በቅጡ የተረዳ ትውልድ ሥራ ፈጣሪና የኢንደስትሪ ባለቤት ነው የሚኾነው፡፡ ሳይንስ ከተስፋፋ ከሌላው ዓለም ጋር ተወዳዳሪ የኾነ ትውልድ ይመጣል፡፡
ይህን ጉጉቴን በሚቀጥሉት 20 እና 30 ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ እውን ኾኖ ማየት እሻለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ብዙ ውድ የኾኑ ማዕድናት አሉ፡፡ ይህን ሀብት አውጥቶ ለመጠቀም የግድ የሳይንስ እውቀት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ሀብታችንን እየተጠቀሙበት ያሉት የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች ናቸው፡፡ መስታወት ለብዙ ዓመታት ሲመረት ኖሯል፡፡ የሚመረተው አውሮፓ ነው፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የመስታወት ጥሬ ዕቃ በገፍ ይገኛል፡፡ ግን ማን ያምርተው ሲባል የሳይንስ እውቀት ያላቸው ናቸው፡፡
መስታወት የሚሠራው እንደፖታሲየም ያሉ ንጥረ ነገሮችን ከመሰል ማዕድኖች ጋር በማንጠርና በማቅለጥ የተለያየ ቅርጽ በመጠቀም ነው፡፡ የትምህርት መስካችን በጥበብ የተሞላ ቴክኖሎጂ ያስፈልገዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች በተቻለ መጠን የራሳቸው የኾነ ቤትና መኪና ሊኖራቸው ይገባል፡፡
ትውልዱ ነቅቶ ሥራ ፈጣሪ ሊኾን ይገባዋል፡፡ ንግድ ላይ የተመሠረተ ሕይወትን በመሻገር አምራች የኢንዱስትሪ ተቋማትን ማፍራት ይገባል፡፡ የሀገራችን ነጋዴዎች ከተለያዩ ዓለማት ቁሳቁሶችን በማምጣት በሀገራቸው ሕዝብ ላይ ይነግዳሉ፡፡
ይኼ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ሸክም ይጥላል፡፡ ነጋዴዎቻችን ብዙ የትምህርት እውቀት የላቸውም፡፡ ይኼ መቀረፍ ይኖርበታል፡፡ የለውጥ መጀመሪያው ትምህርት ሊኾን ይገባል፡፡ በትምህርት ማደግና መቀየር እንዳለ ማወቅ ያሻል፡፡ በእርግጥ ትምህርት ጊዜ ፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን ወጣቱ ዐይኑ ተገልጦለት የሚፈልገውን ዕውቀት በትምህርት አግኝቶ በመጭዎቹ 20 እና 30 ዓመታት ትልቅ ለውጥ መጥቶ ፈጣሪ እድሜ ከሰጠን የምናስበው እውን ይኾናል ብዬ አምናለሁ፡፡
ግዮን፡- በመጨረሻም ማለት የሚፈልጉትና የቀረ የሚሉት ሐሳብ ካለ ያንሱ?
ልጅ ኤልያስ፡- አዲስ ነገር ለማወቅ አዕምሮን መክፈት መቻል ያስፈልጋል፡፡ ከተወሰኑ ነገሮች ውጭ ሌላ ሐሳብ ላለመቀበል የሚደረግ ትግል መቆም አለበት፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች የሚሰለጥኑት ነገሮችን የመቀበል ችሎታቸው እየሰፋ ሲመጣ ነው፡፡ ስለዚህ በሕግና በትውፊት የታሠሩ የግትርነት አባዜዎችን መላቀቅና መገላገል ያስፈልጋል፡፡ ምሁራን በተቻለ መጠን ጽሑፎቻቸውንና ሥራዎቻቸውን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
ለምሳሌ አንድ የኬሚስትሪ መምህር ብዙ ነገሮችን በራሱ መሥራት ካልቻለ ዝም ብሎ ማስተማር የለበትም፡፡ ምክንያቱም የማይተገብረውን ነገር ማስተማር ፍሬ አልባ ስለሚኾን ነው፡፡ መምህሩ ያልገባውን ወይም የማይተገብረውን ኮርስ ማስተማር የተማሪዎች አዕምሮን ግራ ማጋባት እንጂ የሚያመጣው ለውጥ አጥጋቢ አይደለም፡፡ መምህራን ለምርምር እራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ ተማሪዎችም የተማሩት ነገር ትክክለኛ መኾኑን ለማሳየት ለማኅበረሰቡ ግልጋሎት በመሥጠት ተግብረው ማሳየት ይኖርባቸዋል፡፡
የተማሩ ሰዎች መፈራራት የለባቸውም፡፡ ሕብረት ፈጥረው አንድ ትልቅ ነገር መሥራት እንደሚችሉ ማወቅ መቻል አለባቸው፡፡ ከፖለቲካም ከምንም ነገር ጋር ሳያያይዙ እውቀትን ብቻ መሠረት አድርገው ለአንድ ዓላማ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ሲስተሙ የሚጠይቀውም ይኼን ነው፡፡ በጋራ እንቅስቃሴ ሲጀምሩ ነው የኢንዱስትሪ ሥርዓት ሕጉ የሚታወቀው፡፡
ስለዚህ አሁን ያለው ነገር በሙሉ የሚጠቅመው ለኢትዮጵያውያን ሳይኾን ለውጭ ኃይሎች ነው፡፡ ይህን ነገር መስበር የሚቻለው ደግሞ በመተባበርና በቅንነት ዕውቀትን መሠረት አድርጎ ሳይንስን አንድ ላይ ተግባራዊ በማድረግ ነው፡፡ በታሪክ ላይ ከመመሥረት ዛሬን የታሪክ ማዕከል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የተማረው ማኅበረሰብ ያለውን ነገር መለወጥ በሚያስችል መልኩ መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡ ሳይንስን በዕውቀት ተጉዞ በፖሊሲ የታነቀውን የሀገሪቱ የማዕድን ሀብት ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ፣ የተማረው ዜጋ ሀገሩን በመቀየር ውስጥ ትልቅ ባለሚና ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ግዮን፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም ከልብ እናመሠግናለን፡፡
