አዳነ ጥላሁን ዳኜ (ወልዲያ)
መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም በተካሄደው የፓርላማ ስብሰባ ወቅት ጠ/ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከፓርላማ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ እየሰጡ በነበረበት ወቅት እንቅልፍ ላይ የነበረ አንድ አባል ጎትቶ የወሰደኝ በዐፄ ኃ/ሥላሴ ዘመነ አገዛዝ በነበረ የአንድ ዕለት የፓርላማ ስብሰባ ላይ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ላይ የነበረ አንድ አባል ስብሰባው ተጠናቆና ተሰብሳቢዎቹ አዳራሹን ለቀው ከወጡ በኋላ አዳራሹን በማፅዳት ላይ የነበረች የፅዳት ሠራተኛ ባሰማቸው የወንበር ኳኳታ በመባነን ውሳኔ እየተሰጠ መስሎት ተስማምቻለሁ የሚል ድምፅ በማሰማት ቀኝ እጁን አወጣ እየተባለ ይነገር የነበረው ተረብ ሲሆን የዶ/ር ዐቢይን መልስ አሰጣጥ እያዳመጡ በሳቅ ይፍነከነኩ የነበሩት አባላት ድርጊት ያስታወሰኝ ደግሞ ሟቹ ጠ/ሚ/ር መለስ ዚናዊ በዕውቀትም በሥራ ልምድም ያስከነዷቸው የነበሩትን እነአቶ ቡልቻ ደመቅሳና አቶ ተመስገን ዘውዴን የመሳሰሉ ታዋቂ ምሁራንን ሆን ብለው ለማዋረድ ይሰጡት በነበረው ዕብሪት አዘል የሽሙጥ መልስ ስበብ ቀሪው ተሰብሳቢ ያሰማ የነበረው የሳቅ ሁካታ ነው፡፡
የዚህ መጣጥፍ ዓላማ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም በነበረው የፓርላማ ውሎ ከተሰብሳቢዎች በቀረቡ ጥያቄዎችም ሆነ በዶ/ር ዐቢይ መልስ ዙሪያ ትዝብት ጫሪ ነጥቦችን በመጠኑ ማየት ነው፡፡
ከትዝብቴ አንዱ በዕለቱ ጥያቄ ያቀረቡት ሁሉም ጠያቂዎች ያነሱት ችግር የመጡበትን አካባቢ ችግር ብቻ እንጂ ከተመረጡበት ወረዳ ውጭ በሚገኙ ሀገራዊ ችግሮች ዙሪያ ጥያቄ የጠየቀ የፓርላማ አባል አልነበረም፡፡ የሀመሯ ተወካይ የጠየቁት ሀመር ላይ ስላለ ችግር ነው፡፡ በዚህ መልክ የወልዲያው፣ የእስቴው፣ የመሀል ሜዳውም ሆነ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያው ተወካዮች ያቀረቡት የየምርጫ ወረዳዎቻቸውን ችግር ነው፡፡
በበኩሌ ጠያቂዎቹ በመጠየቃቸውም ሆነ ጥያቄዎቹ በመጠየቃቸው ላይ ፍፁም ቅሬታ የለኝም፡፡ እንዳውም በዚህ መልኩ ሌሎች የማናውቃቸው ችግሮች ይፋ መውጣታቸው አንድም ለዕውቅና በሌላ በኩልም ፈጣን መፍትሄ ለማስገኘት ስለሚጠቅም ሊበረታታ የሚገባው ጉዳይ መሆኑን አምናለሁ፡፡ ያ ማለት ግን ከመላ ኢትዮጵያ ተውጣጥቶ በሀገር ደረጃ በሚከሰቱ ማንኛውም ድርጊቶች ዙሪያ አንድ ላይ ተሰባስቦ በሀገር ደረጃ በሚነሱ አጀንዳዎች ዙሪያ ይመክራል ተብሎ በሚታሰብ ተቋም ውስጥ የተካተተ አባል ባገር ደረጃ የሚከሰት ችግር የሚመለከታቸው መሆኑን ግምት ውስጥ አስገብተው ሀገራዊ ችግሮች ላይ ትኩረት በማድረግ ፈንታ ሁሉም ለየመጣበት አካባቢ ብቻ የሚያዘነብል ከሆነ በአስተሳሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በድርጊት ጭምር ፋፍቶ የሚጎለምሰው ኢትዮጵያዊነት ሳይሆን መንደረተኝነት መሆኑን ነው ላተኩርበት የፈለግሁት፡፡
ከዚህ ውጭ ጠ/ሚ/ር ዐቢይ መልስ ለመስጠት እስከሚቸገሩ ድረስ በሀሳብ የጠነከሩ መድረክ ፈታኝ ጥያቄዎች እንደሚቀርብላቸው ከዚያ ፓርላማ ጠብቄ ነበር፡፡ በዚያ የፓርላማ ውሎ በመላ ሀገሪቱ በግፍ እየተጨፈጨፉ ስለሚገኙ ዜጎቻችን ጥያቄ እንደሚቀርብ ግምቱ ነበረኝ፡፡
በህገወጥነት ሽፋን ዘር እየተለየ በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ቤት እየፈረሰባቸው ለጎዳና ተዳዳሪነት ተዳርገው የመንግሥት ያለህ እያሉ እየጮሁና የደም አንባ እያነቡ ስለሚገኙ ወገኖቻችን ምሬት ለመንግሥት ጥያቄ የሚያቀርብላቸው ወኪል ጠብቄ ነበር፡፡
ከየዩኒቨርስቲው ተመርቀዉና ሥራ አጥተው ያለሥራ የሚንገላወዱና በቤተሰባቸው ላይ በወጣት ጡረተኝነት ታዝለው አፍላ የወጣትነት ጉልበታቸው እየባከነ ስለሚገኙ ወጣቶች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ጥያቄ እንደሚቀርብ ጠብቄ ነበር፡፡
በክፍት የሥራ መደብ ላይ የሚፈፀም ቅጥር ዕውቀትንና ክህሎትን ሳይሆን በጉቦና በዘመድ አዝማድ ሰለመፈፀሙ በቅርብ ወራት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፈፀመውን ቅጥር በዋቢ መረጃነት አቅርበው በብዙኃን መገናኛ ጭምር ይፋ ያደረጉትን ተበደልን ባይ ተፈታኝ ሥራ ፈላጊዎች ለቴሌቪዥን የሰጡትን ጥቆማ መሠረት በማድረግ በንግድ ባንኩ አካባቢም ሆነ በሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተሰግስገው በሚገኙ ወስላታና ዋልጌዎች ላይ ርምጃ እየተወሰደ ስለመሆን አለመሆኑ መንግሥትን የሚጠይቁ የፓርላማ አባላት እንደሚኖሩ ጠብቄ ነበር፡፡
በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ በባጃጅ አሽከርካሪነት የሚሰሩ ሾፌሮች ስለሚያሰሙት ሮሮም ሆነ በአዲስ አበባ በጠራራ ፀሐይ ስለሚታፈኑ፣ የእምነት ተቋማትን ስለሚያፈርሱ ብቻ ሳይሆን በጠራራ ፀሐይ ሰው ያውም የቤተክርሰቲያን አገልጋይ ካህን በድንጋይ ቀጥቅጠው የሚገድሉና አማንያንን የሚያስሩ የሚያንገላቱ ወዘተ የከተማ ሽፍታዎች ላይ መንግሥት ርምጃ ሰለመውሰድ አለመውሰዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ እንደሚቀርብላቸው አስቤ ነበር፡፡
ለ2 ዓመታት በዘለቀው የፌደራልና የትግራይ አማፅያን መካከል ፕሪቶሪያ በተደረገው ስምምነት ላይ የወልቃይትና የራያ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ግልፅ መፍትሄ ለምን እንዳልተቀመጠለትና በነዚህ ማንነቶች ስበብ ዳግም ወደግጭት ላለመግባታችን በመንግሥት በኩል ምን ዋስትና እንደተቀመጠለን የሚጠይቅ የፓርላማ አባል ይኖራል የሚል ግምት ነበረኝ፡፡
ሳቅና እንቅልፍ ባስተናገደው በዚያ የፓርላማ አባላት የጥያቄና መልስ ሥርዓተ ስብሰባ ላይ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) አባልና የፓርላማ ተወካይ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ ካቀረቡት የዶ/ር ዐቢይን ቀልብ የሳበ ጥያቄ ውጭ ከሌሎች የፓርላማ አባላት የቀረበ ፈታኝ ጥያቄ አልነበረም፡፡
የዕውቀት አድማሴ ፈቅዶ ለኔ በገባኝ መጠን የአቶ ክርስቲያን ታደለ ስልጣን ለመልቀቅ ምን ያህል ዝግጁ ነዎት እና ኢትዮጵያን እያፈረሳት ያለው ራሱ ብልፅግና ነው የሚለውን አስተያየት በ2 መልኩ ነው የመዘንኩት፡፡ ባንድ በኩል በሰለጠነው ዓለም እንደሚደረገው አንድ የሀገር መሪ ሀገር ባግባቡ መምራት ካልቻለ ሥልጣን እንዲለቅ መጠየቁ ወይም ራሱ በፈቃዱ መልቀቁ የተለመደ ነውና ጠያቂው ከዚያ ተሞክሮ ተነስተው ጥያቄውን ጠይቀውት ከሆነ አግባብነት ያለው ጥያቄ ነው፡፡ ግን እዚህ ላይ የሚያነጋግረን ዶ/ር ዐቢይ ሀገር ለመምራት ብቃት አንሷቸዋል ወይስ በአግባቡ እየመሩ ነው የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በዚህ ጥያቄ ዙሪያ መላው ህዝብ አንድ ዓይነት መልስ ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቅ አይመስለኝም፡፡ የራሴን አቋም ግልፅ ለማድረግ ግን እርሳቸው ሀገሪቱን በአግባቡ እየመሯት ነው ከሚሉት ወገን አይደለሁም፡፡
በሌላ በኩል አቶ ክርስቲያን ያን ጥያቄ ያቀረቡት እንደ አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ዶ/ር ዐቢይ ሥልጣን ቢለቁ የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ችግር ይፈታል ብለው አስበው ከሆነ ግን ስሌታቸው የተሳሳተ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ችግር የሚፈታው ግለሰብ መሪ ሥልጣን ለቆ በሌላ ግለሰብ በመተካቱ ሳይሆን ባገር ደረጃ የሥርዓት ለውጥ ከመጣ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያውም አቶ ኀ/ማርያም ስልጣን ለቀው ዶ/ር ዐቢይ በምኒልክ ዙፋን ላይ ሲወጡ የኢትዮጵያ ህዝብ በጉጉት ብዙ ማሻሻያ የጠበቀ ቢሆንምና እርሳቸውም በወረት ለአንድ ሰሞን ብዙ ተስፋ በመስጠት የተስፋ ዳቦ ሲያገምጡን ቢቆዩም የቀድሞው ሥርዓተ አገዛዝ እንዳለ በማስቀጠላቸው አሁን ላይ ያገሪቱ ዘርፈብዙ ችግር ካለፈው በበለጠ ተጠናክሮ ቀጠለ እንጂ ሲቀንስ አልታየም፡፡ ጉልቻ ቢቀየር ወጥ አያጣፍጥም የተባለው ነው በኛ ላይ የደረሰው፡፡
ዶ/ር ዐቢይ አወዛጋቢውን ሕገመንግሥት አልቀየሩም ወይም አላሻሻሉም እንዲሻሻልም ፍላጎት ያላቸው መሆኑን እጠረጥራለሁ፡፡
ቀደም ሲል ጀምሮ ሲሰራበት የነበረው አንድ ለአምስት ኮሚኒስታዊ አደረጃጀት ይበልጥ ተጠናክሮ ወደ አንድ ለአስር አድጎና ሰፍቶ በ2013 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ ወቅት ብልፅግናን እንደት ባለ አሠራር እንደታደገው የምናውቅ ብዙዎች ነን፡፡ የፀረ ሽብር ህጉ፣ የወጣትና ሴት ሊጉ፣ የወጣት፣ ሴትና የሙያ ማህበራት ያው ቀድሞ በተደራጁበት መሰመር ቀጠሉ እንጂ ማሻሻያ አልተደረገላቸውም፡፡ በዚህ ላይ የለውጥ ፋና ወጊ ነኝ በሚል በ2010 ወደ አደባባይ የወጣው ቡድን ውስጥ ብዙዎቹ በአስተሳሰብም ሆነ በአመለካከት አሁንም ወያኔ ኢህአዴግን የሚናፍቁ እንዳሉ ለመናገር ነቢይ ያለበለዚያም መፅሐፍ ገላጭ መሆንን አይጠይቅም፡፡
በዚህና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ አሁን ላይ ባገሪቱ የሥርዓት ለውጥ እስካልተደረገ ድረስ ዶ/ር ዐቢይ ሥልጣን ለቀው በሌላው ዐቢይ ቢተኩ ውጤቱ ውሀ መውቀጥ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡
ዶ/ር ዐቢይም ሥልጣን በመልቀቅና ባለመልቀቅ ዙሪያ መልስ ሲሰጡ መባል ያለበት ስልጣን ልቀቅ ሳይሆን ስልጣን እንልቀቅ ነው በማለት የሰጡት መልስ በጭራሽ የሚያሳምን መልስ አይደለም፡፡ እንዳውም መልሱ የእርሳቸውን የዕውቀትም የስልጣንም ወርድና ቁመና የሚመጥን ሳይሆን የሚያሳንስ ነው የሆነብኝ፡፡ ምክንያቱም አቶ ክርስቲያን ታደለ ያዙት የተባለው ሥልጣን አንድም ዶ/ር ዐቢይ ከያዙት ሀገራዊ ሥልጣን ጋር በፍፁም ለንፅፅር የሚቀርብ አይደለም፡፡ በሌላ በኩልም አቶ ክርስቲያን የያዙት ሥልጣን ለንፅፅር ይቅረብ የሚባል ቢሆንም እንኳ አቶ ክርስቲያን በያዙት ስልጣን ስበብ መኖሪያ ቤቱ ፈርሶበትና ሜዳ ላይ ተጥሎ የድረሱልኝ ጥሪ እያሰማ የደም እንባ የሚያነባ ግለሰብም ሆነ ቡድን የለም፡፡ የመንግሥት ህግ አስከባሪ በሞላበት ሀገር በጠራራ ፀሐይ ታፍኖ ተወስዶ የሚደበደብ፣ የሚፈናቀል፣ የሚሰደድ፣ ያላግባብ የሚታሰርም ሆነ የሚገደል ወዘተ ዜጋ የለም በዚህና በመሳሰሉት ተጨባጭ ምክንያቶች የተነሳ የዶ/ር ዐቢይ ንፅፅር ሚዛን የሚደፋ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡
ከዚህ ውጭ ዶ/ር ዐቢይ ካለፉት 6 ወራት ጋር ሲነፃፀር ያገሪቱ ሰላም የተሻለ ስለመሆኑ የተናገሩትም ቢሆን አሳማኝነቱ ጥያቄ የሚያጭር ነው፡፡ ምናልባት እርሳቸው አስተማማኝ ሰላም ያሉት ጥይት በመተኮስና በማስተኮስ በኩል የነበረውንና በስምምነት ተፈታ የተባለውን የትግራይ ችግር በመስፈርትነት አስቀምጠው ከሆነ የምለው የለኝም፡፡ ከዚያ ውጭ 2 ኢትዮጵያ አሉ የምንል ካልሆነ በስተቀር ወይም ከላይ በዝርዝር ያሰፈርኳቸውና በዚህ ፅሁፍ ያላሰፈርኳቸው ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ ችግሮች በሰላም ማዕቀፍ ውስጥ እስከተካተቱ ድረስ የኢትዮጵያ የመፍረስ አደጋ ሥጋታችን የመነጨው ክቡር ጠ/ሚ/ር ዐቢይ እንዳሉት በአዕምሯችን ውስጥ ሳይሆን በተጨባጭ መሬት ላይ ከምናየው የመንደር ናፋቂ ጎሳ አፍቃሪ አጥንትና ዘር ቆጣሪ የብሔር ፖለቲከኞች እኩይ ሴራ ተነስተን መሆኑን ግልፅ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ ከዚህ ውጭ የዶ/ር ዐቢይ የመጋቢት 19 ቀን የፓርላማ አዳራሸ ንግግር ከእስከዛሬው የተለየ የሰማሁት አዲስ ነገር ቢኖር በብርጭቆ ስለሚሞላ ውሀና አየር ሙሊት ፎርሙላ ሲሆን እርሱም ቢሆን በሳይንስ ትምህርት በኩል እምብዛም ስለሆንኩ ደረቴን ነፍቼ አስተያየት የምሰጥበት አይደለምና ዝምታን መርጫለሁ፡፡ በተረፈ በዚያ የፓርላማ ውሎ የፓርላማ አባላቱ ሳቅ በሳቅ መሆንም ሆነ ከተቀመጠበት ወንበር ላይ እንቅልፉን ሲለጥጥ የነበረው የህዝብ ተወካይ በመጠኑም ቢሆን ለፈገግታ የዳረጉን መሆኑን አለመናገር ነፉግነት ነው የሚሆንብኝና ፈገግ እንዳሰኙን ይኸውና ተናገርኩ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቃት ይታደጋትም!
