ኢትዮ ቴሌኮም
ኢትዮ ቴሌኮም የ2016 በጀት አመት እቅዱን ለሚዲያዎች ይፋ አድርጓል። በዚህም ኩባንያው በ2016 ከያዛቸው ዕቅዶች መካከል የገቢ መጠኑን 90.5 ቢሊየን ብር ማድረስ አንዱ መሆኑን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገልፀዋል። የገቢ መጠኑ ከ2015 በጀት አመት የ19.4 በመቶ እድገት የሚያስመዘግብ መሆኑንም አንስተዋል። በ2016 በጀት አመት ከተያዙ ዕቅዶች መካከል ሌላው የደንበኞችን ብዛት መጨመር መሆኑን የገለፁት ስራ አስፈፃሚዋ፣ ካለፈው በጀት አመት የ8.3 በመቶ ጭማሪ በማድረግ 78 ሚሊየን ለማድረስ መታቀዱን ተናግረዋል። የቴሌኮም ስርፀት መጠንንም ወደ 71 በመቶ ከፍ ለማድረግ መታቀዱንም ነው የገለፁት። የቴሌብር ደንበኞችን ቁጥር በ28.5 በመቶ በመጨመር ወደ 44.1 ሚሊየን ለማድረስ እየተሰራ መሆኑንም ስራ አስፈፃሚዋ ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም የሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ እንደሚደረግ የተናገሩት ስራ አስፈፃሚዋ በ2016 በጀት አመት ተጨማሪ 13 ሚሊየን ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችል ኔትወርክ በመገንባት ለ92 ሚሊየን ደንበኞች አገልግሎት ለመስጠት መታቀዱን አንስተዋል። 998 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎችን በመክፈት የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ የሚደረግ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን 140 የሚሆነው በገጠር የሚከፈቱ ጣቢያዎች መሆናቸው ተገልጿል። ይህም በአጠቃላይ ያሉትን የሞባይል ጣቢያዎች ወደ 9 ሺህ 78 ከፍ ያደርገዋል። ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ለ2016 በጀት አመት ዕቅድ አፈፃፀም መልካም አጋጣሚ ብለው ከገለጿቸው ጉዳዮች መካከል ደግሞ የውድድር ገበያው ተስማሚ መሆን፣ 3ኛ ኦፕሬተር ወደ ስራ ይገባል መባሉ፣ የሳፋሪኮም የሞባይል መኒ ወደ ስራ ሊገባ መሆኑ፣ የውጭ ምንዛሪ ይረጋጋል የሚል ተስፋ እንዲሁም ደግሞ የሰላም እና የፀጥታ ሁኔታ ይሻሻላል የሚል ጉዳይ ታሳቢ መደረጉን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ከ6ሺሕ በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸው ተገለጸ
በበጀት ዓመቱ 6ሺሕ 959 የሳይበር ጥቃቶች መደረጋቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቋል፡፡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የ2015 በጀት አመት አፈጻጸምን አስመልክቶ መግለጫ ሠጥቷል። የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ሠለሞን ሶካ በ2015 የበጀት ዓመት በኢትዮጵያ 6ሺሕ 959 የሣይበር ጥቃት መመዝገቡንና ከዚህ ውስጥ 6ሺሕ 768ቱ የጥቃት ሙከራዎች መሆናቸውን ገልፀው የተቀሩት 191 ግን የተሣኩ የሳይበር ጥቃት መሆናቸውን ተናግረዋል። ከነዚህ ጥቃቶች ውስጥም 96.02 በመቶው ምላሽ ተሰጥቶባቸው የተጠናቀቁ ሲሆን 3.98 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል። እነዚህ የሳይበር ጥቃቶች ቢደርሱ ኖሮ ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች ለተወሠኑ ጊዜያት በማስተጓጎል ስራዎች እንዳይሠሩ በማድረግ አገልግሎት አሠጣጡ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ መሆናቸው ተመላክቷል። ከዚህ በተጨማሪም የዳታዎች መሠረቅና መጥፋት እንዲሁም ሌሎች ጉዳቶችን ሊያደርስ ይችል እንደነበር ገልጸዋል። በጥቃቱ ኢላማ የተደረጉ ተቋማት አብዛኞቹ ባንኮችና ፋይናንስ ተቋማት፣ የሚዲያ ተቋማት፣ የጸጥታና ደህንነት ተቋማት፣ ሚኒሰትር መሥሪያ ቤቶች፣ የክልል ቢሮዎች፣ የህክምና እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደነበሩ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው የቡና ምርት መጠን መቀነሱ ተገለጸ
ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው የቡና ምርት መጠን ከዓመት ዓመት ማሽቆልቆሉን የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ገልጿል፡፡ የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ግዛት ወርቁ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ለዓለም ገበያ ያቀረበችው የቡና መጠን 302 ሺሕ ቶን መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘንድሮ ዓመት ግን 240 ሺሕ ቶን ብቻ ማቅረቧን እና ይህም ከባለፈው ዓመት ለዓለም ገበያ ከቀረበው የቡና ምርት ጋር ሲንጻጸር በ62 ሺሕ ቶን መቀነሱን ተናግረዋል። ሥራ አስኪያጁ አክለውም፤ ኢትዮጵያ በዘንድሮው ዓመት ለዓለም ገበያ ካቀረበችው ቡና 1 ነጥብ 33 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማግኘቷን እና ይህም ከባለፈው ዓመት ገቢ ጋር ሲነጻጸር በ90 ሚሊዮን ዶላር መቀነሱን ገልጸዋል። ቡናን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ግንባር ቀደም የሆነችው ብራዚል ባለፈው ዓመት በተከሰተ ውርጭ እና ድርቅ ምክንያት የቡና አቅርቦቷ ቀንሶ እንደነበር በመጠቆም፤ ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው የቡና መጠን ከፍ ብሎ እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡ ዘገባው የአዲስ ማለዳ ነው፡፡
400 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር በቁጥጥር ስር ዋለ
መነሻውን ከጅቡቲ ወደብ አድርጎ መዳረሻውን ወረታ ከተማ ለማድረግ የተንቀሳቀሰው 400 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ የጫነ ተሳቢ ተሽከርካሪ ከታሰበው ቦታ ሳይደርስ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ። ህገ ወጥ ድርጊቱ የተፈፀመው በባህርዳር ከተማ ሰባታሚት ቀበሌ ሐምሌ 16 ቀን 2015 ዓ.ም ሲሆን ከሌሊቱ 6 ሰዓት የአፈር ማዳበሪያ በህገ ወጥ መንገድ ለግለሰቦች ሲያከፋፍል በህብረተሰቡ ጥቆማ መያዙን የሰባታሚት ቀበሌ ፖሊስ ኦፊሰር ኮንስታብል ዮሐንስ ጥላሁን ተናግረዋል። አብዛኛው ማዳበሪያ ሳይራገፍ ከነተሽከርካሪው መያዝ ቢቻልም ከ140 ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለግለሰቦች በህገ ወጥ መንገድ መሰራጨቱን ፖሊስ ባደረገው ክትትል ደርሶበታል። ፖሊስ ባደረገው ቤተ ለቤት ፍተሻ ከተሽከርካሪው ተራግፎ በግለሰቦች ቤት የተከማቸ በርካታ የአፈር ማዳበሪያ አግኝቷል። 89 ኩንታል ማዳበሪያ በአንድ ግለሰብ ቤት ተከማችቶ የተገኘ ሲሆን 24 ኩንታል ማዳበሪያ ደግሞ በአንድ ግለሰብ ቤት በአልጋ ስር እና በኩሽና ተከዝኖ መገኘቱን ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ አሽከርካሪው ግለሰብ በህግ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራ መሆኑን ፖሊስ የገለፀ ሲሆን ህብረተሰቡ እንደዚህ አይነት ህገ ወጥ ተግባርን እንዲያወግዝም ጠይቋል።
ንግድ ባንክ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 20.6 ቢሊዮን ብር አተረፈ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጠናቀቀው የ2015 ሒሳብ ዓመት የሥራ ክንውኑ 20.6 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ አገኘ፡፡ ባንኩ በበጀት ዓመቱ ያገኘው አጠቃላይ ገቢ 119.2 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ አጠቃላይ ወጪው ደግሞ 98.6 ቢሊዮን ብር መሆኑን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በዚህም መሠረት የባንኩ አጠቃላይ ዓመታዊ ትርፍ 20.6 ቢሊዮን ብር ሆኗል። ባንኩ በበጀት ዓመቱ ያገኘው አጠቃላይ ትርፍ ከዕቅዱም ሆነ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው አንፃር ሲመዘን ቅናሽ የታየበት ነው። ባንኩ በ2014 ዓ.ም. የሒሳብ ዓመት ያገኘው ያልተጣራ ትርፍ 27.5 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በተጠናቀቀው የ2015 ዓ.ም. ሒሳብ ዓመት ካገኘው 20.6 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ጋር ሲነፃፀር በሰባት ቢሊዮን ብር ወይም በ25 በመቶ ዝቅ ብሏል።
የዋጋ ንረትን በአጭር ጊዜ ማረጋጋት ቀዳሚ ትኩረቱ መሆኑን አስታወቀ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዋነኛነት ትኩረት አድርጎ እየሠራ ከሚገኝባቸው ሦስት ጉዳዮች ውስጥ ቀዳሚው፣ የዋጋ ንረትን በአጭር ጊዜ ማረጋገጥ እንደሆነ አስታወቀ፡፡ የብሔራዊ ባንክ ገዥው እንዳስታወቁት፣ ባንኩ እንደ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ካሉ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ሊሠራ ከሚችላቸው የተልዕኮ ሥራዎች አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ማረጋጋት ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ በልዩ ትኩረት እየሠራበት ያለ ጉዳይ ‹‹የዋጋ ንረትን ማረጋጋት ነው፤›› ያሉት አቶ ማሞ፣ ‹‹ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆኑት የገንዘብ ፖሊሲ አቅጣጫዎች በልዩ ትኩረት የሚመለከቱት የዋጋ ንረት መቀነስን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያደርሰው ከባድ ጉዳት በጣም የታወቀ ነው ያሉት የብሔራዊ ባንክ ገዥው፣ ይህም ቋሚ ገቢ ባላቸው ላይ ከሚያሳድረው ተፅዕኖ ባሻገር በኅብረተሰቡ ውስጥ በጣም ተጋላጭ የሆኑትን እንደሚጎዳ፣ እንዲሁም በከፍተኛ ሁኔታ የኢኮኖሚ ውሳኔዎችን እንደሚያዛባ አስረድተዋል፡፡
