‹‹በተቋማችን ድጋፍ በርካታ ትምህርት ቤቶች ውጤታማ ኾነዋል›› ዜናዬነህ ግርማ

Date:

ዜናዬነህ ግርማ ይባላሉ፡፡ ከተመሠረተ ከ10 ዓመታት በላይ የኾነው የ‹‹ዩዝ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ካልቸራል ፋውንዴሽን›› መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ወጣቶችን በባሕልና በማንነት አንጾ፣ የለውጥ አራማጅ እንዲኾኑ በማብቃት ረገድ ውጤታማ ተግባራትን ያከናወኑ ሰው ናቸው፡፡ የሥራቸውን አድማስ ወደ ተለያዩ ክልሎች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በማስፋትም፣ ወጣቶች በአካዳሚም ኾነ በኢኮኖሚ ብቁ ኾነው የሚወጡባቸው ድጋፎች በተቋማቸው በኩል አከናውነዋል፡፡ ለዚህ ትጋታቸውም እርሳቸውም ኾኑ ተቋማቸው በርካታ ሽልማቶችና ዕውቅናዎችን አግኝተዋል፡፡ ለመኾኑ ፋውንዴሽናቸው ማን ነው? ያለፉት ዓመታት ጉዞውና ውጤታማነቱስ እንዴት ይገለጻል ስንል የሚከተለውን ቆይታ ከእርሳቸው ጋር አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ!

ግዮን፡- በቅድሚያ ራስዎን ለአንባቢያን በማስተዋወቅና በተቋሙ ውስጥ ያለዎትን የኃላፊነት ድርሻም በመግለጽ ቢጀምሩ?

ዜናዬነህ፡- ዜናዬነህ ግርማ እባላለሁ፡፡ የ‹‹ዩዝ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ካልቸራል ፋውንዴሽን›› መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ነኝ፡፡ ድርጅታችንን በዋና ዳሬክተርነት ላለፉት 10 ዓመታት ሳገለግል ነበር፡፡

ግዮን፡- ድርጅቱ ከተመሠረተ ምን ያህል ዓመት ኾነው? ሥያሜውስ ምንን የሚገልጽ ነው? ራዕይና ተልዕኳችሁስ?

ዜናዬነህ፡- ድርጅታችን የተመሠረተው ከ10 ዓመታት በፊት ነው፡፡ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ ለወጣቶች የተለያዩ ችግሮችን በመፍታት ይታወቃል፡፡ በተለይም ክልላዊና ሀገር አቀፋዊ በኾነ ደረጃ የወጣቶች ችግሮችን ለመፍታት አደረጃጅቱን አስተካክሎ ሲንቀሳቀስ ነበር፡፡ ሥያሜው ‹‹ወጣቶች እና ልማት የባሕል ፋውንዴሽን›› የሚል ትርጉም አለው፡፡ ወጣቶች በባሕላቸው እና በማንነታቸው ታንፀው ለሀገር ጥሩ አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ የሚሠራ ተቋም መኾኑን ለመግለጽ ነው፡፡ ሎጎውና ሥሙ የወጣበት መንገድ የአብዛኛውን ወጣት ትኩረት ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ወጣቶች ባሕል፣ ማንነትና የራሳቸው መግለጫ አላቸው፡፡ ተቋማችንም ወጣቶች ወደፊት ሁለንተናዊ ስብዕና ተላብሰው ራሳቸውንም ሀገራቸውንም እንዲያገለግሉ የሚቀረፁበት ነው፡፡ ራዕያችንም በማኅበረሰባችን ውስጥ የለውጥ አራማጅ የኾኑ፣ አቅም ያላቸውና የበቁ ወጣቶችን ማየት ሲኾን ፤ ተልዕኳችን ደግሞ ወጣቶች በትምህርት፣ በባሕል ልውውጥ እና በማኅበራዊ ተሳትፎ ላይ ያላቸው ሚና እንዲዳብር በማድረግ፣ ከሕብረተሰባቸው ጋር የመተሳሰር አቅም እንዲኖራቸው መርዳት ነው፡፡

ግዮን፡- ድርጅታችሁ የሚያከናውቸው ሥራዎች በዝርዝር እንዴት ይገለጻሉ?

ዜናዬነህ፡- ከድርጅታችን ዋና ዋና ሥራዎች መካከል ቀዳሚው ዘላቂ አካባቢያዊ ሥነ ምሕዳር መፍጠር ነው፡፡ ሁለተኛው፣ ለወጣቶች ሠፊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን መፍጠር ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ መሠረታዊ የኾኑ ማኅበራዊ ግልጋሎቶችን ማድረስ ነው፡፡ ለምሳሌ እንደ ትምህርት፣ ጤናና የመሳሰሉት ነገሮች ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም የወጣቶች የአመራር ብቃት ማለትም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን የሚያጎላ ወይም የሚያበቃ ሥራ መሥራት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተቋማችን በሰብዓዊ መብትና በሰላም ዙሪያም ይሠራል፡፡ ማኅበራዊ ኢንተርፕራይዞችንም ለማስፋፋት እንጥራለን፡፡ በተለይም አካባቢያዊ እና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ሊያመጡ የሚችሉ ሁኔታዎች ላይ በትኩረት እንሠራለን፡፡

ግዮን፡- የድርጅታችሁ የገቢ ምንጭ ምንድነው?

ዜናዬነህ፡- አብዛኛው የገቢ ምንጫችን በአጋሮች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በተለይ ውጭ የሚገኙና የእኛን ሐሳብ የሚደግፉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ይደግፉናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የአባላት መዋጮም አለ፡፡ በቅርቡ የጀመርናቸው የገቢ ማስገኛ ሥራዎችም አሉ፡፡ አንዳንድ አገልግሎቶችን በመስጠት ገቢ የምናገኝበትን መንገድም እያመቻቸን ነው፡፡ ለምሳሌ ከአረንጓዴ ልማት ጋር በተያያዘ ወጣቶች የአትክልት ሥራ ይሠራሉ ፤ ችግኞችን ያፈላሉ፡፡ ያንን ሲሸጡ የተወሰነ የመገልገያ ግብዓት እናቀርብላቸዋለን፡፡ እነርሱም በተገኘው ገቢ ራሳቸውን ደጉመው ድርጅቱንም ይረዳሉ፡፡ ይህን ሥራ እኛም ወደ ፊት በሥፋት የምንገፋበት ይኾናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በ2020 አካባቢ ጥበቃ ላይ በሠራናቸው ጉልህ አስተዋፅዖዎች ከእንግሊዝ ሀገር ሽልማት አግኝተናል፡፡ ወጣቶቹ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ላበረከቱት አስተዋፅዖ እንደ ተቋም እውቅና አግኝተናል፡፡

ግዮን፡- መንግሥት ለሲቪል ማኅበራት ያወጣው ሕግ ውስጥ ‹‹አለ›› የምትሉት ጉድለት ምንድ ነው? መልካም ጎኖቹስ?

ዜናዬነህ፡- የሲቪል ማኅበረሰብ ሕግ ጉድለቶቹ ውስን ናቸው፡፡ ሕጉ ተሸሽሎ ከወጣ በኋላ በተለይ ክልል ላይ ያሉ የሲቪል ማኅበራት በርካታ ስለኾኑ ተገቢ የኾነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት አልተሰጣቸውም፡፡ የሕጉ ጠንካራና መልካም ጎን የሚባለው በሰብዓዊ መብቶች እና በሰላም ላይ የሰጠው መብት መልካም የሚባል ነው፡፡ የሲቪል ካውንስል መቋቋሙና በሱ በኩል ድምጻችን እንዲሰማ መደረጉም በጎ ነው፡፡ የካውንስሉ መቋቋም በደንብ እንድንሠራ ረድቶናል ብዬም አስባለሁ፡፡

ግዮን፡- ድርጅታችሁ በሚሠጣቸው ሥልጠናዎችና እገዛዎች ምን ያህል ውጤታማ ነው ማለት ይቻላል?

ዜናዬነህ፡- በርካታ ውጤታማ ድሎችን አስመዝግበናል፡፡ ባለፉት 10 ዓመታት የኢትዮጵያ ወጣቶች የለውጥ ሐዋሪያ ኾነው በተለይ በሥልጠና እና በባሕል ለውውጥ መርሐ ግብሮች የማኅበራዊ ተሳትፎና የዕድገት ልውውጦች እንዲያዳብሩ በርካታ ሥራዎች ሠርተናል፡፡ ይሄ ተልዕኮውን በአግባቡ ያሳካ ነው፡፡ ይህ ውጤት በቁጥር ይቀመጥ ቢባል ባለፉት 10 ዓመታት ከ100ሺህ ያላነሱ ወጣቶች በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በበጎ ፈቃደኝነት ለመሳተፋቸው አስረጂ ይኾናል፡፡ እነዚህ ወጣቶች ለችግር የማይንበረከኩና ለሀገራቸው ልማትን የሚያመጡ ንቁ ዜጎች ናቸው፡፡ ይሄ ለሀገሪቱ ሰላም፣ ልማትና ብልፅግና የራሱን ሚና ተጫውቷል፡፡ ድርጅታችን በጎ ፈቃደኞችን ጨምሮ በአሁኑ ጊዜ ከ70 በላይ ቋሚ ሠራተኞች አሉት፡፡ ከኮንትራት ሠራተኞች ጋር ሲደመር ደግሞ ከ100 በላይ ይኾናሉ፡፡

ግዮን፡- አድራሻችሁ የት ይገኛል?

ዜናዬነህ፡- በሀገሪቱ 4 ንዑሳን ከተሞች ላይ የቅርንጫፍ ቢሮዎች አሉን፡፡ ሀዋሳ ላይ የደቡብን ቅርንጫፍ የሚመራ አለን፡፡ በተጨማሪም ዲላ፣ ወሊሶ እና ሻሸመኔ ከተሞችም ላይ ቢሮዎች አሉን፡፡ በስድስት ክልሎች ደግሞ የፕሮጀክት ስምምነት ውሎች አሉን፡፡ ከ10 በላይ ዩኒቨርሲቲዎችና ከ13 በላይ የመምህራን ኮሌጆች ጋር በአጋርነት እንሠራለን፡፡ ላለፉት 10 ዓመታት ወደ 50 የሚጠጉ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ በተለይ በሳይንስ ዘርፍ ሴቶች ጎልተው እንዲወጡ የበኩላችንን ሠርተናል፡፡ በሥርዓተ ፆታ እኩልነት ላይ በርከት ያሉ ጥናቶችንም አድርገናል፡፡ በሰላም ዙሪያም ሠርተናል፡፡ በርከት ያሉ ወጣቶች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚኾኑበት ብድር በመሥጠት እንዲሠሩም አድርገናል፡፡

ግዮን፡- በድርጅታችሁ ድጋፍ ምክንያት የተሻለ ቦታ ላይ የደረሰ ግለሰብ ወይም ተቋም ካለ ቢነግሩን?

ዜናዬነህ፡- በእኛ ተቋም ድጋፍ በርካታ ትምህርት ቤቶች ውጤታማ ኾነዋል፡፡ ለምሳሌ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በሰፊው ደግፈናል፡፡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ ትምህርት ቤቶች በተለይም እንደበር፣ ወልቂጤና መሰል አካባቢዎች፣ በተጨማሪም በአዲስ አበባም 5 ክፍለ ከተሞች ውስጥ ባሉ 20 ትምህርት ቤቶች፣ በሐዋሳ 8 ትምህርት ቤቶች፣ በኦሮሚያ ክልልም እንዲሁ ከ20 በላይ ትምህርት ቤቶች ጋር በመሥራት ውጤታማ እንዲኾኑ ደግፈናል፡፡

ግዮን፡- ድርጅታችሁ በሲቪክ ማኅበራት ሥር ተመዝግቧል? ተጠሪነታችሁስ ለማን ነው?

ዜናዬነህ፡- እኛ የተመዘገብነው በፌደራል የሲቪክ ማኅበራት ባለሥልጣን ሥር ነው፡፡ በ2019 እንደ አውሮፓውያን ዳግም ምዝገባ ሲደረግ ተመዝግበናል፡፡ ከ2020 ጀምሮም የሚመራበትን ሕግ ተከትለን እየሠራን ነው፡፡

ግዮን፡- ድጋፍ የሚያደርጉላችሁ ዓለም አቀፍ ተቋማት ምን ዘርፍ ላይ የሚሠሩና የት የት የሚገኙ ናቸው?

ዜናዬነህ፡- ከእኛ ድርጅት ጋር የሚሠሩ ተቋማት ዓለም አቀፍ ብቻ ሳይኾኑ ሀገር አቀፍም ጭምር ናቸው፡፡ ለምሳሌ ከአውስትራሊያ እና ከፊላንድ ኤንባሲዎች ጋር እንሰራለን፡፡ የአውስትራሊያው ኢንባሲ የገንዘብ ምንጭ ‹‹ካምቤላ›› ይሠኛል፡፡ የፊላንዱ ደግሞ ‹‹ፊንሽ›› የሚባል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የዩኑስኮ ተቋማትም አብረውን ይሠራሉ፡፡ ዩኒሴፍ፣ ዩኤንዲፕ፣ ዩኤስኤአይዲ፣ አምሬት ኢንተርናሽናል፣ አዋሽ ባንክ፣ ወጋገን ባንክ፣ ጆንኤፍ ዩንቨርሲቲ፣ አሊያንስ፣ ኢኒሼቲቭ አፍሪካ፣ ኢምሪ እና የመሣሠሉት በሙሉ አጋሮቻችን ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ በላይ ግን የእኛ ዋናዎቹ አጋሮች ወጣቶች ናቸው፡፡ ወጣቶች ያላቸውን አቅም፣ ሀብትና ችሎታ በነፃነት ይዘው አብረውን ይሠራሉ፡፡ ወጣቶች ጠንካራ አዕምሯዊ ብቃት ሲኖራቸው በራስ መተማመናቸውን ጨምረው ለመብቶቻቸው የሚታገሉ ለሀገር የሚጠቅሙ ይኾናሉ፡፡ በሌላ በኩል ወጣቶችን አብቅተው የሚያወጡ ተቋማትና ድርጅቶችም በሀገራችን ውስጥ መኖራቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ ለምሳሌ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት፣ ዩንቨርሲቲዎች እና መሰል ሥፍራዎች ወጣቶችን በማብቃት በኩል የሚሰሩ ናቸው፡፡

ግዮን፡- ለተቋማችሁ ከመንግሥት የሚደረግ ድጋፍ አለ?

ዜናዬነህ፡- ከፍ ሲል እንደጠቀስኩት ስድስት ክልሎች ላይ የመሥራት የውል ስምምነት አለን፡፡ የሥራ ፈቃድም አግኘተናል፡፡ ይህን ከመሳሰሉ ሁኔታዎች አንፃር እስካሁን ከመንግሥት እያገኘን ያለነው ድጋፍ በጣም ጠንካራ ነው፡፡ እኛ በየሩብ ዓመቱ ሥራዎቻችንን እናስጎበኛለን ፤ እናስገመግማለን፡፡ የተለያየ የመወያያ መድረክ እናመቻቻለን፡፡ የጎደለንን ነገር ይሞሉልናል፡፡ እኛም የምንፈልገውን ነገር እንጠይቃለን፡፡ ስለዚህ እስካሁን ከመንግሥት በኩል ያጋጠመን የከፋ ችግር የለም፡፡ መንግሥትም ይህ እንዳይገጥመን በየጊዜው ክትትል ያደርጋል፡፡፡ በአጠቃላይ ሥራዎቻችን በመንግሥት በኩል ቅቡልነት አግኝተው ድጋፍ እየተሠጠን ነው፡፡ ለምሳሌ የመንግሥት የወጣት ማዕከለት ከእኛ ጋር አብረው ይሠራሉ፡፡ የጤናው ዘርፍ ከጤናው፤ የትምህርቱ ዘርፍ ከትምህርት ጋር፤ የሥራ እድል ፈጠራ ከሥራ እድል ፈጠራ ጋር በቀጥታ በመገናኘት እንሠራለን፡፡ በየአገልግሎት ማዕከላችን እየመጡም ሥራዎቻችንን ይጎበኛሉ፡፡

ግዮን፡- የድርጅታችሁ የአጭርና ረጅም ጊዜ እቅድ ምንድነው?

ዜናዬነህ፡- በየዓመቱ የምናቅደውን ለሲቪል ማኅበራት ባለሥልጣን እናስገባለን፡፡ በዚያ መሠረት ነው ሥራዎቻችንን የምናከናውነው፡፡ ሥራዎቻችን ከፍ ሲል እንደ ዘረዘርኩት በሰላም፣ በልማት፣ በሰብዓዊ መብት እና በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ነው፡፡ በቅርቡ ግን ለቀጣዩ 10 ዓመት የምንመራበትን ራዕይ ቀርፀን ጨርሰናል፡፡ አዳዲስና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን አካተን ለመሥራት ተዘጋጅተናል፡፡ ድርጅታችን የራሱ የኾነ ቢሮ ከፍቶ ከዚህ በፊት ተደራሽ ያልኾነባቸው አካባቢዎች ላይ ለመሥራት አቅደናል፡፡ ይህን በቀጣይ 2017 ዓ.ም አጋማሽ ለአጋሮቻችን የምናሳየው ይኾናል፡፡

ግዮን፡- በሥራችሁ ውጤታማነት ያገኛችሁት ሽልማት አለ? ለእናንተ የተለየ የኾነው ሽልማትስ የቱ ነው?

ዜናዬነህ፡- ባለፉት 10 ዓመታት ድርጅታችን በርካታ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡ በቅርብ ያገኘናቸውን ሽልማቶች ለመጥቀስ ያህል፡-    በቅርቡ ትምህርት ጨርሼ የክብር ዲክትሬት አግኝቻለሁ ፤ በቅርቡ በባንኮክ ላይ በተካሄደ የትምህርት ጉባኤ የ‹‹ግሎባል ስቲዚንሺፕ›› ሽልማት አግኝተናል፡፡ ላለፉት 10 ዓመታት በትምህርት ላይ ላመጣናቸው አመርቂ ውጤቶች የተበረከተልን ሽልማት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም በማኅበራዊ ኢንተርፕራይዝ ለሠራነው ሥራ ሽልማት አግኝተናል፡፡ በሲቪል ማኅበረሰቦች በተበረከተ ሽልማትም ላይ እንዲሁ ሽልማት አግኝተናል፡፡

ግዮን፡- ‹‹ከፍታ ለወጣቶች›› የሚባል ፕሮጀክት አላችሁ፡፡ ምን ምን ሥራዎችን ታከናውኑበታላችሁ? ውጤታማነቱስ እንዴት ይገለፃል?

ዜናዬነህ፡- ‹‹ከፍታ ለወጣቶች›› ትልቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ ከዩኤስአይዲ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍና በሌሎች አጋሮች ድጋፍም የሚተገበር ትልቅ ሥራ ነው፡፡ ዓላማው ወጣቶች የራሳቸውን ኢኮኖሚያዊ አቅም በመፍጠር ማኅበራዊ ተሳትፏቸውን ማሳደግ እንዲችሉ ማድረግ ነው፡፡ ወጣቶች በሁሉም መስክ የመሳተፍ እድል ቢያገኙ ሀገራቸውን ወደ ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና መምራት ይችላሉ፡፡ ይህን ሐሳብ መሠረት በማድረግም ወጣቶችን ሁለገብ ለማድረግ እሠራን ነው፡፡ ‹‹ከፍታ ለወጣቶች›› የተቀረፀም ይህን ለማሳካት ነው፡፡ ሥራው የሚሠራው ከተለያዩ ማዕከላት ጋር በመቀናጀት ነው፡፡ ከትምህርት፣ ከጤና፣ ከማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የሚሠራ ነው፡፡ ወጣቶቹ በንቃት ተሳታፊ በመኾን የራሳቸውን መልካም ዕድል የሚፈጥሩበት ሥራ ነው፡፡ በውሳኔ ሰጭነትና አመራርነት ሁሉንም ነገር ተግባራዊ የሚያደርጉበት ፕሮግራም ነው፡፡

ፕሮግራሙ ሲታሰብ ወጣቶችን በማሳተፍ የተቀረፀ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸው ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ አብዛኛው ከ15-19 ዕድሜ ያለ ወጣት እንዴት ማስተናገድ እንደሚቻል እና የወጣቶችን አቅም እንዴት መጠቀም እንደሚገባ፣ የወጣቶቹን የሥነ-ምሕዳር ተጠቃሚነት እንዴት ማመቻቸት ይቻላል? ለሀገሪቱ ዕድገትስ በምን መልኩ ይጠቅማሉ? ተብሎ ነው የአሜሪካን የልማት ተራድኦ ድርጅት በ2018 ጥናቱን ይፋ ያደረገው፡፡ ይህ ጥናት ይፋ ከኾነ በኋላ በ2020 እንዲተገብር ፀደቀ፡፡ ለዚህ ተግባራዊነት ከጎናችን ብዙ ድርጅቶች አሉ፡፡ ወደ ሰባት የሚኾኑ ሀገር በቀል የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች አሉ፡፡ ወደ ሦስት የሚኾኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም አሉ፡፡ በርካታ የግል ተቋማትም አብረው ይሠራሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ‹‹ኤጋ›› የሚባለው ተቋም የእኛን ብቃት በየጊዜው እየለካ የሚረዳን ተቋም አለ፡፡ ተቋሙ ከአመራር አንስቶ እስከ ተቋማዊ ዘላቂነት ይፈትሸናል፡፡ ፕሮግራም አፈፃፀማችንን፣ የፋይናንስ አያያዛችንን፣ የሰው ኃይል ሃብት አስተዳደራችንን፣ የክትትልና የምርምር ሥራችንን፣ የእኛን የአመራር ሁኔታ በሙሉ ይገመግማሉ፡፡

በአጠቃላይ አጋሮቻችን ወጣቶች፣ የግሉ ዘርፍ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት፣ የውጩ ድርጅቶችና የመንግሥት ድርጅቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ በጋራ በመጣመር ነው ‹‹ከፍታ ለወጣቶች›› ፕሮጀክትን እየሠራን ያለነው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት አመርቂ ውጤት አምጥተናል፡፡ በ18 ከተሞች ላይ እየሠራን ነው፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ተጠቃሚ ኾነዋል፡፡

ግዮን፡- ማመስገን የምትፈልገው ተቋም ካለ? እንዲሁም ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥህ?

ዜናሁን፡- ማመስገን የምፈልገው በመጀመሪያ ወጣቶቻችንን ነው፡፡ እኛ በምንሠራቸው እያንዳንዱ ሥራ ውስጥ አጋዦቻችን ኾነው እነርሱም ተጠቃሚ የኾኑበትን ሁኔታ በመፍጠራቸው ላመሠግናቸው እወዳለሁ፡፡ የድርጅቱን ‹‹ለኢትዮጵያ ወጣቶች መልካም ዕድል ማመቻቸት›› የሚል መሪቃል በመቀበል አብረው በመሥራታቸውም እንዲሁ አመሠግናቸዋለሁ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ማመስገን የምፈልገው አጋር ድርጅቶቻችንን ነው፡፡ የመንግሥት ድርጅቶችንም ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ሚዲያዎችም መጥተው ጎብኝተውናል ፤ እነርሱንም ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ በሌላ በኩል አዲሱ ዓመት፣ በአዲስ ራዕይ፣ በአዲስ ጉልበት እና በአዲስ መንፈስ የምንገለጥበት ይሁን ማለት እፈልጋለሁ፡፡ በእውቀት ላይ ተመሥርተን ተቋምን የምንመራበት እንዲኾን እንመኛለሁ፡፡ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የልማትና የብልፅግና ይሁንልን፡፡ ሀገራችን ወደ ላቀ ደረጃ እና ወደሚገባት ከፍታ የምትደርስበት ዓመትም ይሁንልን፡፡ ሀገራችን ዘላቂ ሰላም የምታገኝበት ዓመት እንዲኾንም እመኛለሁ፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የክሪፕቶ ሥራ ፈጣሪው የ15 ዓመት እስር ተፈረደበት

የቀድሞው የክሪፕቶከረንሲ ሥራ ፈጣሪ ተሰውሯል ከተባለ 40 ቢሊየን ዶላር...

5ኛው የኢሰመኮ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ተካሄደ

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት በየዓመቱ በፈረንጆቹ ታኅሣሥ...

የንግድ ሚኒስቴር 13 ምርቶችን በመነሻ ሀገር የጥራት ማረጋገጫ (PVoC) እንዲያገኙ ወሰነ

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባወጣው አዲስ መመሪያ መሠረት፣ በሀገር...

ገዳ ባንክ ከ444 ሚሊየን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡን ገለፀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ ባንኮች የተከፈለ ካፒታላቸውን በ2018 ዓ.ም...