የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሎስ አንጀለስ የጎልፍ ክለብ ግቢ ውስጥ መሳሪያ ታጥቆ ሲንቀሳቀስ የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ።
ክስተቱ የተከሰተው ዶናልድ ትራምፕ ለሪፐብሊካን ብሔራዊ ኮሚቴ የገንዘብ ማሰባሰቢያ እራት ፕሮግራም ወደ ስፍራው ለማቅናት ሁለት ቀናት ሲቀሯቸው ነው።
የፀጥታ አካላት ተጠርጣሪውን እድሜው 38 ዓመት የሆነው ጃኒን ጆን ታኤሌ እንደሆነ የለዩት ሲሆን፣ በሲቪል ልብስ የለበሱ የፌደራል ወኪሎች ግለሰቡ የጎልፍ ክለቡን የደህንነት እንቅስቃሴዎች በፎቶ እና በቪዲዮ ሲቀርፅና ሲከታተል ካዩት በኋላ በቁጥጥር ስር አውለውታል።
ፖሊስ በተደረገው ፍተሻ ከተጠርጣሪው ተሽከርካሪ ውስጥ የተጫነ ሽጉጥ፣ 16 ጥይቶች የያዘ ተጨማሪ ካዝና እና የመምታት አቅማቸው ከፍተኛ የሆነ ጥይቶችን አግኝቷል።
በተጨማሪም የኤፍ.ቢ.አይ (FBI) የፀረ-ሽብር ግብረ-ኃይል በተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት ባካሄደው ብርበራ ኤአር-ስታይል (AR-style) ዘመናዊ የጦር መሳሪያ፣ የጥይት መከላከያ ጃኬት፣ ባለከፍተኛ አቅም የጥይት ካዝናዎች፣ የመገናኛ ሬዲዮዎች፣ በርካታ ጥይቶች እና አጠራጣሪ መልዕክቶች የተጻፉባቸው ማስታወሻ ደብተሮችን ሊያገኝ ችሏል።
በ2024 በዶናልድ ትራምፕ ላይ ከተካሄዱት ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራዎች በኋላ የተከሰተውን ይህን አጋጣሚ የምርመራ ቡድኖች በጥብቅ እየመረመሩት የሚገኝ ሲሆን፣ የሎስ አንጀለስ ካውንቲ ዓቃቤ ሕግ በቁጥጥር ስር በዋለው ግለሰብ ላይ ክስ ለመመስረት የክስ መዝገቡን እየመረመረው ይገኛል።
