ቢጂአይ ኢትዮጵያ 30ሺህ የከተማዋ ነዋሪዎች ቀጥተኛ በሆነ እና ባልሆነ መንገድ እንደሚጠቀሙበት የተገመተውን የቀዶ ህክምና መስጫ (ኦፕራሲዮን) ክፍል በ10 ሚልዮን ብር ገንብቶ አጠናቆ ማስረከቡን አስታውቋል፡፡
ሀዋሳ ከተማ የሚገኘው የጨፌ ኮቲጀቤሳ ጤና ጣቢያ ግንባታው የተጠናቀቀውን የቀዶ ህክምና መስጫ ክፍል መረከቡን ተቋሙ በመግለጫዉ አስታውቋል፡፡
በጤና ጣቢያው ውስጥ የተገነባቸው የቀዶ ህክምና መስጫ ክፍል በተለይም ገቢው አነስተኛ የሆነ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ባለበት አካባቢ ለሚገኙ እናቶች እና ህጻናት ጥራት ያለው የጤና እንክብካቤ አገልግሎት እንዲያገኙ እድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡
በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የቢጂአይ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኤሚሊዮ ጋርሲያ “ቢጂአይ ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ ከንግድ ስራ ያለፈ መሆኑን ያምናል›› ብለዋል።
ጤና ጣቢያውን ለማገዝ ሱ ማህበረሰቡ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ እና በረጅም ጊዜ ደህንነቱ ላይ ኢንቨስት እያደረግን ነው ይህም የንግድ ተቋማት ትርጉም ላለው እና ዘላቂ ለሆነ ልማት እንዴት አስተዋፅዖ ማድረግ እንደሚችሉ ማሳያ ነው” ሲሉ ብለዋል።
የኦፕራሲዮን ክፍሉ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የተጠናቀቀ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ቀልጣፋ የጤና አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ተጠቁሟል።
ፕሮጀክቱ ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር፣ ከጤና ጽ/ቤት ኃላፊዎች እና ከማህበረሰብ ተወካዮች ጋር በቅርበት በመተባበር የተሰራ መሆኑ ተገልጿል።
ቢ ጂ አይ ኢትዮጵያ በቀጣይም በጤና፣ በትምህርት፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በዘላቂ የማህበረሰብ ልማት ላይ ያተኮሩ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጫው አስታውቋል።
