ቪዛ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ (ፊንቴክ) ፈጠራን ለማበረታታት፣ የክፍያ እና የግብይት ተግዳሮቶችን ለመፍታት እንዲሁም አዳዲስ መፍትሄዎችን ለማምጣት ያስችላል ያለውን “ቪዛ በየትኛውም ቦታ (VEI)” የተሰኘ የፊንቴክ ውድድር በይፋ አስጀምሯል፡፡ የቪዛ መካከለኛው እና የምስራቅ አውሮፓ፣ የመካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ ቢሮ ፕሬዝዳንት አንድሪው ቶሬ፤ በሰኔ ወር በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት ቪዛ የዲጂታል ክፍያዎችን ለማስፋፋት ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ፤ የፊንቴክ ፈጠራን ለማስፋፋት እና በሴቶች የሚመሩ አነስተኛ እና መካከለኛ ቢዝነሶችን ለማገዝ አዳዲስ ውጥኖች መያዙን ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡ ይህም እቅድ በአገር ውስጥ ለኹለተኛ ጊዜ የቪዛ ለኹሉም ፊንቴክ ውድድርን ለማዘጋጀት እና የቪዛን ‘ቀጣይ እሷ ናት’ የሴቶችን ማጎልበት ፕሮጀክት ማስጀመርን እንደሚያካትት ገልጸዋል።
“የ”ቪዛ በየትኛውም ቦታ” (Visa Everywhere Initiative) ለፊንቴክ እና ለሥራ ፈጣሪዎች በክፍያ እና በንግድ ዓለም ላይ ተጨባጭ እና ውጤታማ መፍትሄዎችን እንዲያስገኙ የሚያስችል መድረክ ነው” ሲሉ የቪዛ የኢትዮጵያ ቢሮ ኃላፊ ያሬድ እንዳለ ተናግረዋል። ፊንቴክ እና ሌሎች የክፍያ ስርዓት ፈጣሪዎች፣ ሸማቾች እና ነጋዴዎች ክፍያ የሚፈጽሙበትን መንገድ በመቀየር ብዙ ሰዎች የሚፈልጉትን ገንዘብ በሚፈልጉበት ጊዜ በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ ማድረጉንም አስረድተዋል። የዘንድሮው “ቪዛ በየትኛውም ቦታ (VEI)” ኢትዮጵያ የፍፃሜ ውድድር በመስከረም ወር የሚካሄድ ሲሆን፤ በድምሩ 50 ሺሕ ዶላር በተለያየ ደረጃ ለሚያሸንፉ ተወዳዳሪዎች እንደሚሰጥ ተነግሯል። ይህም 1ኛ ደረጃ 25 ሺሕ ዶላር፣ 2ኛ ደረጃ 15 ሺሕ ዶላር እና 3ኛ ደረጃ 10 ሺሕ ዶላር ተሸላሚ ያደርጋል ተብሏል፡፡
ከሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ከ61 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኘ
በ2015 በጀት ዓመት ከሀገር ውስጥ ጎብኚዎች 61 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ገቢ መገኘቱን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ የሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ አለማየሁ ጌታቸው እንደገለጹት÷ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ በተለይም አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን ከማልማት እንዲሁም ነባሮችን ከማደስ እና ከመጠገን አንጻር ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል፡፡ የጮቄ ተራራ እና ወንጪ የኢኮ ቱሪዝም መዳረሻዎች በዓለም ቱሪዝም ድርጅት እውቅና እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉንም አስታውሰዋል። በተለያዩ አካባቢዎች ተጨማሪ የኢኮ ቱሪዝም መዳረሻ ሊሆኑ የሚችሉ ቦታዎችን በጥናት የመለየት እና መረጃ የማሰባሰብ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡
የ84 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር የልማት ድጋፍ ስምምነት ተፈረመ
ኢትዮጵያና የአፍሪካ ልማት ፈንድ ለስንዴ ምርትና ምርታማነት ማሻሻያ የሚውል የ84 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር ወይም የ4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የልማት ድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡ ስምምነቱን በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የገንዘብ ሚነስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ እንዲሁም የአፍሪካ ልማት ፈንድን በመወከል በምስራቅ አፍሪካ የአፍሪካ ልማት ባንክ ምክትል ዳይሬክተር አብዱል ካማራ (ዶ/ር) ፈርመውታል፡፡ ከልማት ድጋፉ ውስጥ 54 ሚሊየን ዶላር ከአፍሪካ ልማት ፈንድ፣ 20 ሚሊየን ዶላር ከኔዘርላንድስ መንግስት፣ 10 ሚሊየን ዶላር ኦ ሲ ፒ አፍሪካ ከተባለ ድርጅት እንዲሁም ቀሪውን 300 ሺህ ዶላር ግሎባል ሴንተር ፎር አዳብቴሽን ከተባለ ተቋም የተገኘ መሆኑ ታውቋል፡፡ የልማት ድጋፉ በአነስተኛ እርሻ የስንዴ አምራች አርሶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል የሚውል እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ድጋፉ ይህንን ዕውን ለማድረግ ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የስንዴ ምርት ለማምረት፣ የገበያ መሰረተ ልማቶችንና ትስስርን ለማሳደግ እንዲሁም በዘርፉ ያሉ ፕሮጀክቶችን ለማስተዳደር የሚውል ነው ተብሏል፡፡ ይህ ድጋፍ በተለይ የሀገር ውስጥ የስንዴ ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ምርት ለማሟላት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ሲሆን÷ በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ የሚተገበር እንደሚሆን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለኢንቨስተሮች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የዲጂታል ሥርዓት ተዘረጋ
በአማራ ክልል መዋዕለ ንዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለሃብቶች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የዲጂታል ሥርዓት መዘርጋቱን የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ይሄነው ዓለም፥ በአማራ ክልል በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ የሚያስችል እምቅ አቅም መኖሩን ተናግረዋል። በክልሉ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በ2015 በጀት ዓመት 483 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 4 ሺህ 724 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን በአብነት አንስተዋል። አልሚዎቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡም ለ957 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል። አልሚዎች ቀልጣፋ አገልግሎት ከአስፈላጊ መረጃ ጋር እንዲያገኙም ተደራሽ እና ዲጂታላይዝ አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።
ዓለም ባንክ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ገበያ ትስስር ድጋፍ ሊያደርግ መሆኑ ተገለጸ
ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች የሥራ ዕድል ፈጠራና የገበያ ትስስር እንዲኖራቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል መግባቱን የኢንዱስትሪያል ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የጽሕፈት ቤትና የትራንስፎርሜሽን ኃላፊ አቶ ፍፁም ከተማ እንደተናገሩት፣ በዓለም ባንክ ድጋፍ የተገነባው የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ምዕራፍ ሁለት ፕሮጀክት መጠናቀቁንም ገልጿል፡፡ በቅርቡ ለልማት የገቡ ድርጅቶች እየሠሩት ያሉትን ሥራዎችና ዘርፉ የፈጠረውን የሥራ ዕድል የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋ በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ እንደሚገኙና ትናንት ሐምሌ 25 ቀን 2015 ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ጉብኝት ይገኝበታል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ‹‹ከዓለም ባንክ ጋር ያለው ግንኙነት መሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ያተኮረ ብቻ አይደለም›› ያሉት አቶ ፍፁም፣ ቴክኒካል እገዛ ከማድረግ በተጨማሪ ዘለቄታዊ የልማት ሥራዎችም ላይ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በጉብኝታቸው የተነሱት ዋና ሐሳቦችም በፓርኮቹ የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎችና የገበያ ትስስር ላይ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ በየደረጃው ክትትል እንደሚያደርጉ ፕሬዚዳንቱ ቃል መግባታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ሳፋሪኮም የኤም-ፔሳ አገልግሎትን ለማቅረብ ስምምነት ተፈራረመ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት ለመስጠት በቅርቡ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ያገኘው ሳፋሪኮም ኤም-ፔሳ ሞባይል ፋይናንሻል ሰርቪስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የዲጂታል የባንክ አገልግሎቱን ከኅብረት ባንክ ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ፡፡ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በኬንያና በሌሎች ስምንት አገሮች ያስፋፋውን ኤም-ፔሳ የተባለውን የዲጂታል የባንክ አገልግሎቱን ኢትዮጵያ ውስጥ ከኅብረት ባንክ ጋር በመተባበር ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት የተፈራረመው ሐምሌ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ነው፡፡ በዚህም ስምምነት መሠረት የሳፋሪኮም የሚያፈራቸው የኤም-ፔሳ አገልግሎት ደንበኞቹ የኅብረት ባንክ ቅርንጫፎችን በመጠቀም ገንዘብ ለማውጣትና ለማስገባት የሚያስችላቸው ይሆናል፡፡
