የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፣ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ቁጥጥር የለሽ እድገት በአስቸኳይ እንዲገደብና ዓለም አቀፍ የስነ-ምግባር ደንብ እንዲወጣለት ጥሪ አቀረቡ።
ጳጳሱ “ማግኒፊካ ሁማኒታስ” በተሰኘውና በዛሬው ዕለት ይፋ በተደረገው ባለ 130 ገጽ መመሪያቸው (Encyclical) ላይ እንዳመለከቱት፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች እና ስልተ-ቀመሮች (Algorithms) በራሳቸው ከሞራል ገለልተኛ ሊሆኑ እንደማይችሉ ገልጸዋል።
የቴክኖሎጂው ፈጣን እድገት በማህበረሰቡ መካከል ያለውን የዲጂታል ተጠቃሚነት ልዩነት እያሰፋው መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም መመሪያው በከፍተኛ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ሰብአዊ እና አካባቢያዊ ተፅዕኖዎችን የዳሰሰ ሲሆን፣ ለቴክኖሎጂ ምርቶች የሚሆኑ ብርቅዬ ማዕድናትን ለማውጣት በሚደረገው ሂደት ውስጥ የሚስተዋሉ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛዎችን እና የተለያዩ የወንጀል ድርጅቶች ቴክኖሎጂውን ለሰው ዝውውር መቆጣጠሪያነት የሚጠቀሙበትን መንገድ አውግዟል።
በሌላ በኩል የቴክኖሎጂው ዘርፍ ደጋፊዎች እና የኢንዱስትሪው መሪዎች አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ለህክምና፣ ለትምህርት እና ለኢኮኖሚ እድገት ያለውን ከፍተኛ አስተዋፅዖ የሚገልጹ ሲሆን፣ ቫቲካንም የቴክኖሎጂውን ጥቅም ሙሉ በሙሉ ከመቃወም ይልቅ ሰብአዊ መብትን እና ስነ-ምግባርን ባስጠበቀ መልኩ ዓለም አቀፍ የህግ ማዕቀፍ እንዲበጅለት ማሳሰቧ ተገልጿል።
ምንጭ: Agence France-Presse
