ከቀናት በፊት በሰሞነኛዉ የጤና ባለሙያዎች እንቅስቃሴ ምክንያት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሪሄንሲቭ ሪፈራል ሆስፒታል ሬዝደንትና ኢንተርን ሐኪሞች በከፊል ስራ ማቆማቸዉን ተከትሎ ዩኒቨርሲቲዉ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ አዘል ማስታወቂያዎችን ያወጣ ቢሆንም የወጡ ሐኪሞች አለመመለሳቸዉን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
” ማስጠንቀቂያዉ የሙያ ክብራችንንና አገልግሎታችንን የማይመጥን ከመሆኑም በላይ ዛቻና ማስፈራሪያ የታከለበትና የሬዝደንት እስር ያስከተለ ስለነበር ካሳለፍነዉ ሐሙስ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ስራ ለማቆም ተገደናል ” ብለዋል።
” እስከ ትናንት ድረስ አንድ ፅኑ ሕሙማን ክፍል ታካሚን ከሚከታተል ሬዝደንት ሐኪም በስተቀር ሁሉም ኢንተርንና ሬዝደንት ሐኪሞች ሆስፒታሉን ለቀዉ መወጣታቸውን የሚያስረዱት ሐኪሞቹ በአካዳሚክና ብቃት ማነስ የተባረሩ ሬዝደንት ሐኪሞችን ለመመለስ የመሞከር አዝማሚያዎችን ዉስጥ ካሉ ተማሪዎች ሰምተናል ” ሲሉ ገልፀዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሀዋሳ ዩንቨርሲቲ የሴኔት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በትምህርት / በስራ ገበታቸው ላይ ያልተገኙ ኢንተርንና ሬዚደንቶች ዛሬ ሰኞ ወደ ትምህርታቸውን እማ ስራቸው በመመለስ በየትምህርት ክፍሎቻቸው ሪፖርት እንዲያደርጉ በጥብቅ አሳስቧል።
ወደ ትምህርት/ስራ ገበታቸው የማይመለሱ ከሆነ ከግንቦት 12/2017 ዓ/ም እስከ ሀሙስ ግንቦት 14/2017 ዓ/ም ድረስ ብቻ የይቅርታ ደብዳቤ በማስገባት ወደ ትምህርታቸው /ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ ፈቅዷል።
በተጠቀሱት ቀናት ወደ ትምህርታቸው/ስራ ገበታቸው በማይመሱ ተማሪዎች ላይ የሴኔት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የመጨረሻውን ህጋዊ አርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ማኔጅንግ ዳይሬክተር ዝናዉ ሳርምሶ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል፥ የጤና ባለሙያዎች ጥያቄዎች ሀገራዊ እንደምታ እንዳላቸዉና በፌዴራል መንግስት የሚመለሱ እንዳሉ ሆነዉ በዩኒቨርሲቲው ደረጃ መመለስ የሚችሉ ጉዳዮችን ለመመለስ ዩኒቨርሲቲው ስራዎችን እየሰራ ስለመሆኑ ገልፀዋል።
ካሳለፍነዉ ሐሙስ ጀምሮ በሆስፒታሉ የሬዚደንት እና ኢንተርን ሀኪሞች ስራ ማቆማቸውን ያረጋገጡት አቶ ዝናዉ ” ይቅርታ ጠይቀዉ እንዲመለሱ የወሰነው ሴኔት ነው ” ሲሉ ተናግረዋል።
