በአፍሪቃ ዝኆኖች የሳይንስ ጥናት አባት የሚለውን ስም የያዙት ታላቅ ተመራማሪ ኢየን ዳግላስ Sir Iain Douglas-Hamilton በተወለዱ በ83 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።
በወርሐ ነሐሴ እ.ኤ.አ በ1942 ኢንግላንድ የተወለዱት ዳግላስ-ሃሚልተን በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የስኮትላንድ የእንስሳት ተመራማሪ እና በአፍሪካ ዝኆን ጥናት ላይ በዓለም ትልቁን ስፍራ የሚይዙ ናቸው። የዛሬ ሰላሳ ሁለት ዓመት የመሠረቱት Save The Elephant የአፍሪቃን ዝኆኖች ከጥፋት ታድጓል።
ኢየን ዳግላስ-ሃሚልተን በአፍሪካ የዝሆኖች ሕገ-ወጥ ግድያን በመከታተል የCITES የቴክኒክ አማካሪ ቡድን አባል፣ የኬንያ የዝኆኖች ምርምር ፈንድ ባለአደራ፣ ከ1982 የIUCN የአፍሪካ የዝኆኖች ስፔሻሊስት ቡድን አባል እና ከ1993 እስከ 2004 የአውሮፓ ህብረት የዱር እንስሳት እና የአካባቢ አማካሪ ሆነው ሰርተዋል።
የፒኤችዲ ጥናታቸውን On the ecology and behaviour of the African elephant: The elephants of Lake Manyara በሚል ርዕስ ላይ የሰሩት ኢየን ዳግላስ-ሃሚልተን በታንዛኒያ የማንያራ ሐይቅ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ የዝኆን ማህበራዊ ባህሪን በተመለከተ የመጀመሪያውን ጥልቅ ሳይንሳዊ ጥናት አድርገዋል። ስለ ዝኆን ጥርስ አደን እልቂት ዓለምን ያሳወቁ የመጀመሪያው ሰው ሲሆኑ ውጤቱም በ1989 የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ የዝኆን ንግድ እገዳ አስከትሏል።
በ23 ዓመት ዕድሜያቸው ወደ ታንዛኒያ አቅንተው ዱር ውስጥ የገቡት ኢየን ዳግላስ-ሃሚልተን በአፍሪካ ዝኆኖች ማህበራዊ መስተጋብር ዙሪያ የመጀመሪያውን ሳይንሳዊ ጥናት ያካሄዱ ናቸው።
ስለ ዝኆን ቦታዎች እና ፍልሰቶች ከፍተኛ መጠን ያለው መረጃ መሰብሰብ እና መተንተን ስለ ምርጫዎቻቸው ግንዛቤ እንዲያገኙ እና በዚህም ምክንያት አደን እና የሰውና-ዱር እንስሳት ግጭትን ጨምሮ እየጨመረ ከሚሄደው ስጋት ለመጠበቅ የሚረዳ የክርክር ሀሳብ ይዘው ወጡ።
ይህ ሀሳብ ከባለቤታቸው ኦሪያ ጋር በመተባበር የፃፉት “Among the Elephants” በተሰኘው መጽሐፍ እና በፒተር ማቲሴን “The Tree Man Was Born” መጽሐፋቸው ላይ ተገልጿል።
በተለይም በኡጋንዳ፣ ኬንያና ታንዛኒያ ስለ አፍሪካ ዝኆኖች እራሳቸውን ሰጥተው ኖረዋል። ለዚህ ነው The economist ህልፈታቸውን አስመልክቶ በሰራው ዘገባ “ጠንካራውን ተከላካያቸውን አጥተዋል።” ሲል የገለፀው። ለዚህ አበርክቷቸውም አያሌ ሽልማቶችን ወስደዋል።
የ2010 የኢንዲያናፖሊስ ሽልማትን ጨምሮ የአፍሪካን ዝሆኖች ለመጠበቅ ላደረጉት ምርምር እና ለሰሩት ስራ በ2014 የቺካጎ ዞኦሎጂካል ሶሳይቲ የጆርጅ ቢ ራብ ጥበቃ ሜዳሊያ እና በ2006 የዲስኒ የዱር እንስሳት ጥበቃ ፈንድ ሽልማትን አግኝተዋል።
በ2025 ዳግላስ-ሃሚልተን እና ዶ/ር ጄክ ዎል የኤስሞንድ ቢ ማርቲን ሮያል ጂኦግራፊካል ሶሳይቲ ሽልማት፣ የሳንዲያጎ ዞኦሎጂካል ሶሳይቲ የህይወት ዘመን ስኬት ሽልማት ተሸልመዋል።
ከትናንት ወዲያ ህልፈታቸው ይፋ የሆነው ኢየን ዳግላስ-ሃሚልተን በሙያ ዘመናቸው ሁሉ ከጥናት ያልተለዩ የአካዳሚክ ምርምር ወረቀቶችን ያሳተሙ ናቸው።
ከባለቤታቸው ኦሪያ ጋር “Battle for the Elephants” (Viking, 1992) እና “Among the Elephants” (DoubleDay 1975) የተባሉ ተወዳጅ መጻሕፍትን አሳትመዋል። በተጨማሪም “A Life Among Elephants” የተባለውን ገናና ፊልም ጨምሮ ጨምሮ”The Family that Lives with Elephants” (Narrated by David Niven), “Ivory Wars” , “Africa’s Elephant Kingdom” , “The Secret Life of Elephants”, “This Wild Life” የተሰኙ ዘጋቢ ፊልሞችን ሰርተዋል። በእርግጥም ኢየን ዳግላስ-ሃሚልተን የአፍሪካ ዝኆኖች ሳይንስ አባት ነበሩ።
ለዚህም ነው ህልፈታቸውን አስመልክቶ The Telegraph በዘገባው “If any elephants survive in Africa today, it’s thanks to this man” ያለው።
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም – ለድሬ ቲዩብ)
